የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ለፍቅር እንኑር

“ፍቅር በማንኛውም ሰው ልብ ውስጥ በተፈጥሮ አለ ። በተቃራኒው ጥላቻ በትምህርት እንጂ በተፈጥሮ አይገኝም ።” /ኔልሰን ማንዴላ/

እግዚአብሔር በፍቅር ፈጠረን ። ከፍቅር ፈጠረን ። ለፍቅር ፈጠረን ። እግዚአብሔር እኛን ለመፍጠር ሲያስብ ይህን አገኛለሁ ብሎ አላሰላም ። እርሱ ብቻው ለዘላለም የኖረ ፣ በፍጥረቱ የማይደገፍ ነው ። የመላእክት ውዳሴ ፣ የሰዎች ምስጋና ፣ የአእዋፋት ዝማሬ ሳይጀመር እርሱ በራሱ ምስጋና ነበረ ። እከብር አይል ክቡር ፣ አገኝ አይል ባለጠጋ ፣ አሸንፍ አይል ድል ነሺ ፣ አልፍ አይል አሳላፊ ነው ። ሰውን ለመፍጠር ሲያስብ መልኩን ቅድስናውን ፣ ምሳሌውን ገዥነቱን ሊያካፍለው ብሎ ነው ። ሰው በመልኩ ሰማይን ሲመስል ፣ በገዥነቱም ምድርን ያስተዳድራል ። መልኩ እስካለ ግዛቱ ይጸናል ። እግዚአብሔር ሰውን በፍቅር ምክንያት ብቻ ፈጠረው ። እግዚአብሔር ፍቅር ባሕርይው ነው ። እግዚአብሔር ዘላለማዊ አካል ብቻ ሳይሆን ከአካሉና ከባሕርይው ጋር የጸና ዘላለማዊ ፍቅር አለው ። ፍቅርን ከእግዚአብሔር ተቀብለናል ፣ እንደ ንጹሕ መስተዋትም የፍቅሩን ብርሃን ለዓለም እንድናስተላልፍ ተጠርተናል ። ይህ ጥሪም በተፈጥሮና በመዳን ነው ። በተፈጥሮ በመልኩ ፈጠረን ፣ ይህ ማለት መልኩ ፍቅር ነውና በፍቅር ፈጠረን ማለት ነው ። ፍቅር ዓለም ሁሉ በጥላቻ ቢያዝ እኔ ግን በመውደዴ እጸናለሁ ብሎ የሚያምን ነው ። ፍቅር እግዚአብሔርን እንጂ ሁኔታዎችን ፣ ብድራትን ፣ ዘመኑን አያይም ። ለማፍቀር ምክንያቱ ፍቅር ብቻ ነው ። ፍቅር ለጥገኝነት የሚቀርብ ደብዳቤ አይደለም ። ፍቅር ራሱ አምባ ነውና ። አፍቃሪ ማለት ፈሪ ፣ ከሌላው የሚከጅልና የሚለማመጥ ሳይሆን የተፈጠረበትን ዓላማ ለማሳካት ቆርጦ የወጣ ነው ። ፍቅር በፍቅር ብቻ ይቆማል ። ፍቅር መቆሚያ ታኮ ፣ መደገፊያ ክራንች ከፈለገ ፍቅር አይደለም ። ክብርን በመፈለግ ባለሥልጣንን ፣ ሀብትን በመፈለግ ባለጠጋን ፣ ግርማን ተፈሪነትን በመፈለግ ጀግናን ፣ መኖርን በመፈለግ ጊዜ የሰጠውን መውደድ ፍቅር አይደለም ።

የሰው ልጅ በተፈጠረበት በፍቅር መልክ እስከ ጸና ድረስ ሁሉም ነገር ይታዘዝለት ነበር ። በዚህ ፍቅር ላይ ሲያምጽና ፍቅርን ገሸሽ ሲል ግን የገዛ ፈቃዱም ዓመጸበት ፣ አራዊት በጠላትነት የሚፈልጉት ፣ ምድርም የምትነፍገው ሆነች ። መብሉ ጣር ያለበት ፣ ልጅንም የሚያገኘው ከምጥ በኋላ ሆነ ። ያለ ጣር የተገኘው በረከት ከሄደ በኋላ በጣር የሚገኝ ቢገኝም የማያጠግብ ሆነ ። አዳም ከመሬት እናቱ ያለ ድካም ፣ ሔዋን ከአዳም እናትዋ ያለ ሕመም ተወለዱ ። አቤል ግን በምጥ ተወለደ ። በነጻ የተሰጠው ነገር ክብር ካላገኘ በዋጋ የሚገኝ ይሆናል ። በዋጋ ቢገኝም የማያስደስት ይሆናል ። ያለ ፍቅር የምንኖርበት ዓመት አይደለም ሰከንድ መኖር የለበትም ። ያለ ፍቅር ሰዎችን መታገሥ ፣ በእምነት መቀራረብ ፣ ይቅርታ ማድረግ አይቻልም ። ፍቅር ሰማይን መውረሻ ብቻ ሳይሆን የምድር ኑሮን ማጣፈጫም ነው ። አክመን መስማት ሲያቅተን አጣመን እንሰማለን ። ፍቅርን ካልዘራን ጠብን እንዘራለን ። እያንዳንዱ ቀን የትላንትን ስናጭድበት ፣ የነገን እንዘራበታለን ። መልካሙን ካልዘራን ክፉውን እንዘራለን ። መልካሙ ነገር ሲዘራ ያደክማል ፣ ሲታጨድ ያስደስታል ፤ ክፉ ነገር ሲዘራ ቀላል ነው ፣ ሲታጨድ የሚያስለቅስ ነው ።

ከፍቅር ተገኝተናል ። እግዚአብሔር በፍቅር ፈጠረን ። ከወላጆቻችንም ከፍቅር ተገኝተናል ። እግዚአብሔር ወንድን የሚያህል ጠንካራ ፣ ሴትን የሚያህል ንቁ አዘጋጀና ልጅን ሰጣቸው ። የሴት ንቃት የወንድ ጥንካሬ ልጁን ልዝብ አድርገው ያሳድጉታል ። በፍቅር የተፈጠረና በፍቅር የተወለደ የሰው ልጅ ያለ ፍቅር መኖር አይችልም ። ያለ አየር ለመኖር የሚያቅድ ካለ ያለ ፍቅር ለመኖር የሚያስብ ሞኝ ሰው ነው ። የሰው ልጅ ለፍቅር ይኖራል ። በፍቅር ተፈጠረ ፣ ከፍቅር ተወለደ ፣ ለፍቅር ይኖራል ። ለፍቅር ሲኖር የእግዚአብሔርንና የሰውን ውለታ እየከፈለ ነው ። እግዚአብሔር በመልኩ በአምሳሉ ፣ በልጅነት ማዕረግ ፈጠረው ። ወላጆቹም በምጥ ወለዱት ። እርሱ ሲወለድም ጎረቤቶች እልል አሉ ። የደስታ ጥይት ተተኮሰ ። ሲያድግም ማሙሽ እያሉ ሰዎች ሳሙት ። ከረሜላ ገዙለት ። ሲኮላተፍ አደመጡት ፣ ሲሳሳት ወደዱት ። እያንዳንዳችን ለእግዚአብሔርና ለሰው ያለብንን ዕዳ የምንከፍለው በፍቅር በመኖር ብቻ ነው ።

ኔልሰን ማንዴላ፡- “ፍቅር በማንኛውም ሰው ልብ ውስጥ በተፈጥሮ አለ ። በተቃራኒው ጥላቻ በትምህርት እንጂ በተፈጥሮ አይገኝም” ያሉት ለዚህ ነው ። ፍቅርን ያለ ልምምድ ይቀበለዋል ። አዲስ ምግብ ለመመገብ የሚታገለው ሕጻን ፍቅርን ግን ያለ ጥናት ይቀበለዋል ። ገና ሲወለድ የእናቱ እቅፍ ውስጥ መግባት ፣ ጡት መለመን ይጀምራል ። ፍቅር በተፈጥሮው ውስጥ አለ ። ጥላቻን ግን በተፈጥሮ ሳይሆን በትምህርት ያዳበረው ነው ። በቂመኞች ፣ በበቀለኞች ፣ በዘረኞች እጅ ሲያድግ ጥላቻን እየተማረ ይመጣል ። ዓለም ለፍቅር ካላት በጀት ለጥላቻ ያላት በጀት ይበልጣል ። እንደውም ለፍቅር ምንም በጀት የላትም ። ለጥላቻ ግን የጦር ኃይሏን በማደራጀት ትባጅታለች ።

ፍቅር በተፈጥሮ በውስጣችን የተቀበረ ነገር ሲሆን ያስቀመጠውም እግዚአብሔር ነው ። ከተቀበረበት ቆፍረን ማውጣት አለብን ። ጥላቻ ግን ሰዎች ያሸከሙን ትብትብ ነው ። መምረጥ ያስፈልገናል ። እግዚአብሔር ከሰጠንና ሰዎች ካሸከሙን ነገር አንዱን መምረጥ ያሻናል ። የእግዚአብሔርን ስንመርጥ አፍቃሪ ፣ የሰዎችን ስንመርጥ የጥላቻ ሰው እንሆናለን ። ማንም ሰው ፍቅራችንን በመጠራጠር መቀበል ይቸገር ይሆናል ። ፍቅር ሰላም እንደሚሰጠው ግን ሁሉም ሰው ይመሰክራል ። ውድ ነገር ሁሉ በጥልቀት የተቀበረ ሲሆን ሲቆፈር ይወጣል ። ፍቅርም በጥልቀት ተቀብሯልና ልናወጣው ይገባል ። መስቀሉን ቀብረው በላዩ ላይ ጉድፍ ቆሻሻ ጥለውበት ተራራ አህሎ እንደ ነበር ፣ ያንንም የተቀበረውን መስቀል ንግሥት ዕሌኒ እንዳወጣችው እናውቃለን ። መስቀሉ ዛሬም ተቀብሯል ። መስቀል ፍቅር ነው ። መቀበር ብቻ ሳይሆን ብዙ ጉድፍ ቆሻሻ ተከምሮበታል ። ዛሬም ቆፍረን እናውጣው ።

ጥላቻ መራራ ዋጋ ያስከፍላል ። ፍቅር ግን ይክሳልና እንፋቀር ።

የብርሃን ጠብታ 17
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ