የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ልቤ

ልቤ እርጋታ የለውም ። ልቤ የረገጠውን መልሶ ይረግጣል ። ቍርጥ ውሳኔ አጥቶ ከኃጢአት እየዋለ ከጽድቅ ያረፍዳል ። ልቤ ሸካራ ነው ፤ ቂምን አርግዞ በቀልን ይወልዳል ። ልቤ ልፍስፍስ ነው ፣ ከሚሰደብበት ቦታ ቆሻሻ መጣያ ሆኗል ። ልቤ ዓለም ነው ፣ ልቤ የወፍ ጎጆ ነው ። ሰፋ ስለው የሚጠብብ አስጨናቂ ነው ። ልቤ ሁሉን ካልወደድሁ ብሎ በስሜት ይነሣሣል ፣ መልሶ ራሱንም መጥላት ይጀምራል ። ልቤ በልቤ ውስጥ ባይሆን ኖሮ አብዷል ተብሎ በተያዘ ፣ ወፈፌ ተብሎ የተዘለፈ ነበር ። አካሌ ጨምቶ ልቤ ይወራጫል ። ወንበር ላይ ተቀምጬ ልቤ ዓለምን ይዞራል ። ውስንነት ከብዶት ልቤ ምሉዕ በኵለሄ ልሁን ይላል ። አንድ ቀን በልደት የጀመረ ፣ አንድ ቀን በሞት የሚያበቃ መሆኑን ረስቶ ልቤ አልፋ ኦሜጋ ልሁን ይላል ። ልቤን ለልብ አምላክ እከሰዋለሁ ። ስንዴና እንክርዳድን ያበቀለ እርሻ መሆኑን እናገራለሁ ።

ልቤ የሚያሳዝነው ያስቀዋል ፣ የሚያስቀው ያስለቅሰዋል ። ልቤ ሞገደኛ ነው አብዮት ያስነሣል ፣ ልቤ ደካማ ነው በድቃቂ ሳንቲም ይደለላል ። ልቤ ሰማይን ያስሳል ፣ ቁራሽ መሬት ለማግኘት ዘመን ላመጣው ያደገድጋል ። ልቤ ሞቱን በሟቾች መቃብር ላይ ያለቅስለታል ፣ ከቀብር ሲመለስ ወደ ግፍ ተግባሩ ይመለሳል ። ልቤ መቀበልን ሽቶ መስጠትን ይጠላል ። ሌላው እንዲወደው እየተመኘ ፣ ሌላውን ለመውደድ ዳተኛ ይሆናል ። ልቤ ጉራማይሌ ነው ። ወጥ መልክ እያጣ ያናውጠኛል ። አድራሻዬን ተናግሬ እንዳልወጣ ያዘባርቀኛል ። ልቤ እንደ ሰዓቱ ፣ ልቤ እንደ ዜናው ፣ ልቤ እንደ ወቅቱ ነው ። ሰማይ ላይ የሄደው ልቤ በዚያው ቅጽበት ጭቃ ሲያላቁጥ አገኘዋለሁ ። በልቡ ላይ የበላይ የሆነ ይህን አቤቱታ መስማት አይሆንለትም ። ልቡን ልቡ ያደረገ አይቼም አላውቅም ። ልቤ እየቀደሰ ይረክሳል ፣ እየዘመረ ይስታል ፣ እየጸለየ ይባክናል ። ራሱ ከፍቶ ፣ በሌሎች መክፋት ልቤ ይደነቃል ። የእርሱን ምሰሶ ትቶ በሰው ጉድፍ ይሳለቃል ። ልቤ ሞኝ ነው ፣ አያገኘኝም ብሎ የጨው ተራራ ሲናድ ይስቃል ።

ልቤ ራሱ ጠፍቶት የሰውን ልብ አውቃለሁ ይላል ። ልቤ እገሌ ጎሣ ሲነግሥ “ደብቄ ነው እንጂ እኔ እኮ ከዚህ ዘር ነኝ” ለማለት ይከጅላል ። ልቤ ሆዳምነት በልጦበት ካሸነፉት ሰፈር ሲወለድ ይኖራል ። ሁልጊዜ የሚወለድ ማደግ ግን ያቅተዋል ። ልቤ ረቂቁ ፣ ግዙፉን ዓለም የሚንጠው እርሱ ነው ። የሚታየው ከማይታዩት የተሠራ ነው ። የሚታየው ጥፋት ፣ የማይታዩ ልቦች ውጤት ነው ። አካል ያጠፋል እንጂ አይከፋም ፤ ልቤ ይከፋል ፣ አካሌ ያጠፋል ። ልቤ ሰማይ ተቆልፎበት ምነው በሞትኩኝ ይላል ። ልቤ ሰውን ሁሉ እወዳለሁ እያለ አንድን ሰው ማፍቀር አቅቶታል ። ልቤ ስለ ዓለም አቀፋዊነት እያወራ ፣ መንደር አቀፍነት ወጥሮታል ። ልቤ ሩቅ አገር ካለው ጋር እየተወዳጀ ጎረቤቱን አኩርፏል ። ልቤ መንታው ፣ ልቤ ባለማመን የምታሰቃየኝ ፣ ልቤ እስስቱ ፣ ልቤ የጌታ ሳይሆን የቀን ሎሌ ነህ ።

ልቤ ወንዙ ፣ ልቤ ነሆለሉ ፣ ልቤ ባሕር ፣ ልቤ የሚዋልል ፣ ልቤ የውኃ ላይ ኩበት ፣ ልቤ ተቀምጬ የሚሮጥ ፣ ጽሞናን ጠልተህ በጫጫታ የምትደበቅ ፣ ለገዳይም ለሟችም እኩል የምታጨበጭበው እውቀት አልባ የምትሆነው እስከ መቼ ነው ? እግዚአብሔር ሲመራህ እንቢ ብለህ ሰው እንዲነዳህ የፈቀድከው ፣ ባሰመሩልህ ስትቀየስ የምትኖር የመስኖ ውኃ የሆንከው ፣ ልቤ ዕረፍትህን ናፍቄአለሁ ።

ልቤ እርሱ እያሞገሰ ፣ ካህናት ለምን አያወግዙም የሚለው ፣ እውቀትና መረጃን ያምታታው ፣ ሰልጥኛለሁ ብሎ ኃጢአትን የሚያቆነጀው ለሞትም ለምጽአትም ያልተዘጋጀው ልቤ እርሱ ነው ።

ተኝቶ እያደረ ስጸልይ ነጋ የሚለው ልቤ ግብዙ ፣ ሙሴን እየተወ ፈርዖንን የሚጋብዝ ፣ ኢየሱስን ትቶ በርባንን የሚናፍቅ ፣ ሚዛንን ጥሎ የሚደንስ ልቤ እርሱ ነው ።

ከጥንት ጀምሮ የልብ ባለመድኃኒት የሆንከው የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ልቤን ጠብቀው ! አሜን!!!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ተፃፈ ነሐሴ 9 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ