የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ልታነጻኝ ትችላለህ

                     /ማቴ. 8፡2/
በ44 ዓ.ም ገደማ ይመስለኛል ማቴዎስ ወንጌሉን እንደ ጻፈ ሰማሁ ። ከግሪክ ይልቅ የአራማይክ ቋንቋ ለእኔ ይቀለኛልና በአራማይክ ቋንቋ በመጻፉ ደስታዬ ወሰን አልነበረውም ። ቋንቋ መግባቢያ እንጂ መደናገሪያ አይደለም ። ቋንቋ ወደ ሌሎች የምንደርስበት እንጂ ተኮፍሰን የምንቀመጥበት አይደለም ። ቋንቋ የማኅበረሰብ ሀብት እንጂ የፖለቲካ መሳሪያ አይደለም ። ቋንቋ የገባንን የምናስረዳበት እንጂ የምሁርነት መለኪያ አይደለም ። ሁሉም ቋንቋ አለውና ማንም በማንም አይኮራም ። ቋንቋ ሰውን ተጠግቶ የሚኖርና እንደ ሰው በምዕራፎች የተከፋፈለ ዘመን ያለው ነው ። ይወለዳል ፣ ያድጋል ፣ ይደክማል ፣ ይሞታል ። ትንሣኤም ያገኛል ። ታላቁ እስክንድር የሥልጣን ዘመኑ ትንሽ ቢሆንም ዓለም የግሪክን ፍልስፍና ያውቀው ዘንድ ያስፋፋው የፅርዕ ቋንቋ ግን የሥልጣን ዘመኑ ብዙ መቶ ዓመታትን የተሻገረ ነው ። ብቻ በአራማይክ ቋንቋ ማቴዎስ ወንጌሉን እንደ ጻፈ ስሰማ ደስ አለኝ ። በልቤም ሰው ከአሳቡ ጋር እንጂ ከቋንቋው ጋር ለምን ይታገላል ? ብዬ ጠየቅሁ ። በበዓለ ሃምሳም ሰባ ሁለት ቋንቋ ለሐዋርያት የተገለጠው እግዚአብሔር የምሥራቹን ዓለም ሁሉ እንዲሰማው ስለፈለገ ነው ። በሰናዖር ቋንቋ ርግማን ነበረ ፣ በበዓለ ሃምሳ ደግሞ በረከት ሁኖ ተሰጠ ። በበረከት ፍቅር እንጂ ጠብ ሊኖር በፍጹም አይችልም።

ከሁሉ የማረከኝ በስምንተኛው ምዕራፍ የመጀመሪያ አንቀጽ ላይ ቅዱስ ማቴዎስ ስለ እኔ መጻፉን ስሰማ ነው ። እኔ የረሳሁትን ውለታ ቅዱሱ እስከ አሁን ያስታውሰዋል ብዬ ተገረምሁ ። ከመዳኔ በኋላ በመድኃኒትም ፣ እንዲሁም በሽታው አርጅቶ ልድን እችል ነበር እያልኩኝ ምስጋናውን ማቀዝቀዝ ጀምሬ ነበር ። እግዚአብሔር ይቅር ይበለኝ ። ከመዳኔ በፊት ግን ያለኝ ተስፋ እግዚአብሔር ብቻ ነበር ።  ቅዱስ ማቴዎስ ለእኔ ቦታ በመስጠቱ ገረመኝ ። የተራራው ስብከት ተሰብኮ እንዳበቃ ከተራራው ግርጌ እጠባበቅ የነበረውን ጊዜ አስታወስሁ ። የተራራው ስብከት ሲንቆረቆር እኔም ከተራራው ግርጌ ሁኜ እሰማ ነበር ። እኔም ትምህርቱ ትኩሳቱ ሳይደርቅ ከተራራው እየወረደ ባለው ጌታ ፊት ዝቅ ብዬ ሰገድሁ ። ማቴዎስ ይህን ታሪኬን ያነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ላይ ስለ ምጽዋት አስተምሮ ነበርና ጤናን የሚመጸውት እርሱ ብቻ ነው ለማለት ይመስለኛል ። ጤና የአንድ አምላክ ስጦታ ነው ። ጤና ብዙ የችግር ጓዞችን የሚያስከትል ቢሆንም ከችግሮቹ አንዱ መገለል ነው ። እኔ ከብዶኝ የነበረው እኔ ለታመምኩት የሰዉ መፈርጠጥ ነበር ።
ብቻ በእግዚአብሔር መዝገብ ፣ በወንጌል ሰፈር ስፍራ አግኝቼ የእኔ ታሪክ መጠቀሱን ስሰማ አሁን ማመን እስኪያቅተኝ ደስታ በልቤ ይፈስሳል ። ቤት ለሌለኝ የዱር ነዋሪ መንግሥቱን የሰጠኝ ፣ ሁሉ ለሸሸኝ በእጆቹ የዳሰሰኝ ፣ ማረፊያ ላጣሁ ምዕራፍ የሰጠኝ ፣ የተደረገልኝን ለመግለጽ ቋንቋ ላጠረኝ ፣መግለጫ ቃል ላበረደኝ ጌታ ክብር ምስጋና ይሁንለት ። በእኔ ታሪክ አእላፋት ሲያመሰግኑ ፣ እኔ ግን በቀጣዩ ችግር አዝኛለሁ ። ሞትን አልፌ ሕመምን እፈራለሁ ፣ ከገደል ወጥቼ ማጣትን እሰጋለሁ ። ታምሜ የታመምሁበት ዘመን አልፎ ብታመምስ ብዬ የምሰጋበት ዘመን ላይ ደርሻለሁ ፣ አጥቼ ያጣሁበት ያ ቀን ተሽሮ ባጣስ ? ብዬ እደነብራለሁ ። እግዚአብሔር ለእግራችን እንጂ ለስጋታችን መልስ አይሰጠንም ። አልተጨበጠምና ።
መኖሪያዬ ይሁዳ መሰደጃዬ ግን ገሊላ ነበር ። የኖሩበት አላስጠጋ እያለ የማያውቁት አገር ያስጠጋል ። የሚያውቁት እየከፋ ባዕዱ ይራራል ። የተወዳጁት አበሳን እያበዛ ምንነትን የማያውቅ ወዴት ነህ ? ብሎ ይፈልጋል ። ከገሊላም ጥብርያዶስን የመረጥኩት ጭር ያለች ገጠር ፣ የባሕር ዳርቻና ለመደበቂያ የሚሆኑ ብዙ ጉብታዎች ስላሉአት ነው ። የሃይማኖት ሰዎች ያሉባት ይሁዳ ግን ተመጻዳቂዎች በእኔ በሽታ የጤንነት ማስታወቂያቸውን የሚሠሩባት ስለሆነች ከወገኞች ዞር ማለት መልካም ነው ብዬ ስላመንሁ ነው ። ክርስቶስን በኢየሩሳሌም ሲሰቀል የተራራውን ትምህርት ግን በገሊላ አደረገ ። በኢየሩሳሌም ንባብ አለ ፣ ትርጓሜው ያለው በገሊላ ነው ። እግዚአብሔር በማይጠበቅ አርአያ ይገለጻል ፣ በማይጠበቁ ሰዎች ውስጥም እግዚአብሔር ያበራል ። ደህና ሰዎች በሁሉም ጋ አሉ ። እግዚአብሔር የራሱ ሰው አለውና ። ራቅ ፣ ራቅ ብለውም የተቀመጡ ደጋግ ሰዎች ባይኖሩ ኑሮ ዓለም ጨለማ ትሆን ነበር ። በትክክል ለምፅ ነው ብለው ለበሽታዬ ስም ለመስጠት ካህናቱ በቂ ነበሩ ፣ ለማግለልም እነርሱን የሚከተለው ሕዝብ የዘወትር ሥራው ነው ።
ክርስቶስ ግን በዱር አገኘኝ ። ቅዱስ ማቴዎስ ያን ቀን አስታውሶ ከአሥር ዓመታት በኋላ በስምንተኛው ምዕራፍ የመጀመሪያ አንቀጽ ላይ ታሪኬን ማስፈሩ ደስ ብሎኛል ። ለምጻም ስለነበርሁ ሳይሆን ስለተፈወስሁ ተናገረ ። ወንጌል በሽታን የሚያደንቅ ሳይሆን ፈውስን የሚያውጅ ነው ። ብዙ ለምጻሞች ነበሩ ፣ የተፈወስሁት እኔ ግን በቅዱሱ መዝገብ ስፍራ አግኝቻለሁ ። ታሪኬ ሚዛን ባይደፋም የተሠራልኝ ተአምር ግን ሚዛን ይደፋል ። እኔ ዝም ብልም ሥራው ሲናገር ይኖራል ። አዎ ለምጻም ነበርሁ ። ነበርሁ ብሎ ለመናገር አሳላፊውን ጌታ ማግኘት ያስፈልጋል ። ሙት ነበርሁ ለማለት የትንሣኤን አምላክ በትክክል መደገፍ ግድ ይላል ።
ይቀጥላል
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ