የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ልከኛ

 “እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ … የአንዲት ሚስት ባል” 1ጢሞ. 3፡2
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ በሚለው መጽሐፋቸው በገጽ 64 የግርጌ ማስታወሻ ላይ፡- “ያን ጊዜ ያገቡ ካህናት ኤጲስ ቆጶሳት ይሾሙ ነበር ። ለምሳሌ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው የጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ አባት ኤጲስ ቆጶስ ነበር ። ለኤጲስ ቆጶስነት ማዕርግ የሚመረጡ ደናግል መነኮሳት ብቻ እንዲሆኑ የተወሰነው በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው” ብለዋል ። ለኤጲስ ቆጶስነት የሚመረጡት ደናግል መነኮሳት ብቻ የሆኑበት ምክንያትም ከሞቱ በኋላ ቤተሰቦቻቸው የውርስ ክርክር ከቤተ ክርስቲያን ጋር በመግጠማቸው እንደሆነ አባቶች ይናገራሉ ። እንዲህ ከሆነ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ፊት ትሟገታለች ። የምትሟገተውም ከገዛ ልጆችዋ ጋር ነው ። ሙግቱም ሚዛን የማይደፋው የንብረት ክርክር በመሆኑ ከሰማያዊ አደራዋ አንሳ እንድትገኝ ያደርጋታል ። በዚህ ምክንያት የክርስቶስ ሙሽራ የሆኑት ደናግልና መነኮሳት ብቻ ኤጲስ ቆጶስነት እንዲሾሙ ተወስኗል ። በዚህም ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ዕረፍት አግኝታለች ። መነኮሳትም ለቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ብቻ ሳይሆን ወታደርም ሁነው ኑረዋል ። ዛሬ የምናያቸው ትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎችም ገዳማት እንደነበሩ ታሪክ ይመሰክራል ። በቀጣዩም ዘመንም ደናግልና መነኮሳት ኤጲስ ቆጶስነትን ይዘው ይቀጥላሉ ።

በዚያ ዘመን አሕዛብ ከአንድ በላይ ትዳር መያዝ ልማዳቸው ነበርና ሐዋርያው የአንዲት ሚስት ባል የሚል መስፈርት አስቀመጠ ። ሐዋርያው የአንዲት ሚስት ባል ስላለ ደናግል አይሁኑ አላለም ። ስለዚህ በዚያም ዘመን ደናግል ኤጲስ ቆጶስነትን ይቀበሉ ነበር ። ከአንድ በላይ ትዳር ያላቸው ኤጲስ ቆጶስ ለመሆን ሲሉ ይፍቱ ማለቱ አይደለም ። በአንድ ሚስት የጸና እርሱ ብቻ ኤጲስ ቆጶስ እንዲሆን ተናገረ እንጂ ። የመጀመሪያው መስፈርት ግላዊ ሕይወቱን የሚመለከት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቤተሰብን የሚመለከት ነው ።በክርስቲያን ልማድ እንኳን በክህነት ያለ ምእመንም ከአንድ ሚስት በላይ ማግባት አይፈቀድለትም ። ይህ የኦሪትም የሐዲስም ሳይሆን የተፈጥሮ ሕግ ነው ። ለአንድ አዳም አንዲት ሔዋን ብቻ ተፈጥራለችና ። ከአንድ በላይ ትዳር መመሥረት በአገራችን የተስፋፋው ከግራኝ መሐመድ ወረራ በኋላ ወይም ከአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ ነው ። ይህም የአሕዛብ ልማድ እንጂ በክርስቲያን ሊሆን የሚገባው አይደለም ። ከአንድ በላይ የሆነ ትዳር የአሳብ ብክነትን ፣ ጠብና ክርክርን ፣ የኢኮኖሚ መናጋትን ፣ የልጆች መጠላላትን ይወልዳል ። ሰውዬውም በሁለት ገመድ በግራና በቀኝ የሚጎተት ይሆናል ። ከቁሙ አልፎ በሞቱም ብዙ ሙግትና ክርክር ያስነሣል ። በሕይወቱ ቀርቶ በሞቱም ሲወቀስ ይኖራል ። ስሙ የማያርፍ ፣ ጠብ አውርሶ የሄደ ይሆናል ። ሐዋርያው የአንዲት ሚስት ባል የሚለውን መስፈርት ቤተ ክርስቲያን ዘመኑን በማየት በስድስተኛው ክፍለ ዘመን በደናግል መነኮሳት እንዲተካ አድርጋለች ። የድንግልና ሕይወት ምርጫ ሲሆን ፣ ምንኩስና ኪዳኑ ነው ፣ ክህነት ደግሞ ሥልጣን ነው ።
በክህነት ያለ ሰው በአንድ ሚስት የጸና መሆን ይገባዋል ። ይህ ለምስክርነቱ ወሳኝ ነው ። ጤናማ የቤተሰብ ሕይወት ከሌለው አገልግሎቱ መታወክ ይጀምራል ። ሌሎች ለቃል ኪዳናቸው እንዲታመኑና በትዕግሥት እንዲጸኑ መምከር ይሳነዋል ። ይልቁንም ቤተሰብ ትንሽዋ ቤተ ክርስቲያን ናትና ጤናማ ትዳር ከአገልጋዮች ይጠበቃል ። ቤተ ክርስቲያን ጉዞ የጀመረችው በምእመናን ቤት ነው ። የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በማርቆስ እናት ቤት ነበረች ። ቤተሰብ ቤተ ክርስቲያንን አስተናግዳለችና ቤተ ክርስቲያንም የትዳርን ክብር ትጠብቃለች ።
“እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ … ልከኛ” 1ጢሞ. 3፡2 ።
ሦስተኛው መስፈርት ልከኛ የሚል ነው ። ኤጲስ ቆጶስ በአነጋገሩ ፣ በአመጋገቡ ፣ በአረማመዱ ፣ በአቀራረቡ ልከኛ መሆን አለበት ። ምክንያቱም ብዙ ዓይኖች በእርሱ ላይ ናቸውና ። የሚናገረው ቃል ሊመነዘር ፣ አመጋገቡ ሊተች ፣ አረማመዱ ሊነቀፍ ፣ አቀራረቡ ክብር የለሽ ሊያሰኘው ይችላል ። ዓለሙ የልክ ዓለም በመሆኑ የምንናገረው በልክ መሆን ያስፈልገዋል ። አንድ ሰው፡- “ዘመኑ የኢኮኖሚ ነውና የምናገረው መጥኜ ነው” በማለት የሁለት ደቂቃ ንግግር አድርገው ቁጭ ብለዋል ። “ብዙ ቢያወጉ ይዘነጉ ፣ ብዙ ቢተቹ ይሰለቹ” ይባላል ። ሐዋርያውም የሹመትን መስፈርት ልከኛ በማለት ይጠቅሰዋል ። በልኩ የማይናገሩ ሹሞች በንግግራቸው ሲጠመዱ ይታያሉ ። የተሾሙ ሰዎች የተጠናና አጠር ያለ ንግግር ያውም በጽሑፍ ቢያቀርቡ ብዙ ፈተናን ይቀንሳሉ ።
በአመጋገብ ልከኛ መሆን ይገባል ። ይህ የሚያየው ሰው እንዳይተች ያደርገዋል ። የተሾሙ ሰዎች በአደባባይ ባይበሉ ይመከራል ። ሰው ቀኑን የሚገፋው እነርሱን እያማ ነውና የሐሜት ምክንያት ላለመሆን ቢጠነቀቁ የተሻለ ነው ። የተሾሙ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ሁላችንም በአመጋገባችን ልከኛ መሆን ይገባናል ። የልጆቻችን ክብደት ጨምሮ ለበሽታና ለስንፍና እንዳይዳረጉ አመጋገባቸውን ልከኛ ማድረግ ይገባል ። የኑሮ ዘይቤአችን እየተለወጠና እንቅስቃሴ እየቀነሰ በመጣበት ዘመን በልኩ አለመመገብ ለሞት ይዳርጋል ። ምግብ ሕይወት እንደሆነ ሁሉ ልከኛ ካልሆንም ገዳይ ነው ። የብዙ ልዕልቶችና ልዑላን ዕድሜአቸው ከሃምሳ አይበልጥም ። ምቾት ዕድሜአቸውን ያሳጥረዋል ። የበላነውን ያህል መንቀሳቀስ ካልቻልን ተፈጥሮውን እያጣ ያለው ምግብ የበለጠ ጤናችንን እየጎዳው ይመጣል ።
በአረማመዳችን ልከኛ መሆን ግድ ነው ። በትዕግሥት የተሸከመችንን ምድር በትዕግሥት መርገጥ ይገባናል ። አረማመድ ራሱን የቻለ ቋንቋ ነው ። በአረማመዳችን ሐኪሞች ፣ የሥነ ልቡና ባለሙያዎች ይገመግሙናል ። ከማኅበረሰቡ ጋር ያለን ግንኙነትም ከአረማመዳችን ይጀምራል ። አንዳንድ ሰዎች ምንም ሳይናገሩ ፣ ቀርበው ሳይታዩ በአረማመዳቸው ብቻ ይፈረጃሉ ።አረማመዳችን ትሕትና ፣ ቅልጥፍና ፣ ትጋት ያለው ሊሆን ይገባዋል ።
አቀራረብም ልከኛ መሆን የበለጠ ለኤጲስ ቆጶሳት ወሳኝ ነው ። ፈተና እንዳይመጣባቸው ፣ እነርሱም ለሌላው ፈተና እንዳይሆኑ በአቀራረብ ልከኛ መሆን ግድ ነው ። ሌላው ሰው ከእነርሱ ጋር ቢሰደብ ክብሩ ነው ። ለእነርሱ ግን አገልግሎታቸውን የሚጎዳ ነውና ልከኛ መሆን ያስፈልጋቸዋል ። ይልቁንም መራቅ እንደ ቅድስና ፣ መቅረብ እንደ ዓለማዊነት በሚታይበት ባሕል ጠንቃቃ መሆን ያስፈልጋል ። እውነተኛ አፍቃሪ ልከኛ ነው ። ስሜታዊ አፍቃሪ ግን ጓዳውንም ልቡንም ለማያውቃቸው ይገልጥና ኋላ መሰብሰብ ያቅተዋል ። ልከኛ ኑሮ ያለው ሰው ጠቡ ትንሽ ነው ። ልከኛ ኑሮ ያለው ሰው ተከብሮ ይኖራል ። ልከኛ ኑሮ ያለው ሰው ማዘዝ ይችላል ። ልከኛ ኑሮ ያለው ሰው ባለጌዎችን ይበልጥ አያባልግም ። ልከኛነት ለሁላችን በተለይ ለአገልጋዮች ያስፈልጋል ። የፈተናው ወረዳ ውስጥ ገብቶ ከመታገል በልክ መኖር ይሻላል ።
አምላክ ይርዳን ።
1ጢሞቴዎስ 35
ጥር 8 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ