የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሕሊናን ለጣሉ

 “እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ ፥ አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው ፥ መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ ፥ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና ፤” 1ጢሞ. 1፡19
እግዚአብሔር ከሰጠን ተፈጥሮአዊ መብራት አንዱ ሕሊና የሚባል ነገር ነው ። በሕሊናችን መጠቀም ሲገባን ሕሊናን የሚተካ ራእይና ሕልም እንዲሁም መገለጥ ብንጠብቅ በከንቱ እንደክማለን እንጂ ምንም አናተርፍም ። በሃይማኖት ስም እየተደረጉ ያሉትን ቅጥፈቶች ፣ እያሳሳቱ ያሉትን አሳቾች ስንመለከት አንዳንዶች ሕሊናን እንደ ጣሉ መረዳት እንችላለን ። የሚታለልለት ካገኘ አታላይ ሁልጊዜ ማታለል ይፈልጋል ። የሚፈረደው ግን ሕሊናቸውን ጥለው በጠፉ ሰዎች ነው ። የሞቀ ትዳራቸውን እየኖሩ በፍቅር እየተሳሰቡ ፣ ልጆችን እያሳደጉ ባለበት ሰዓት “ትዳርሽ የእግዚአብሔር ፈቃድ አልነበረም” ሲባሉ ወዲያው የሚለያዩ ሰዎችን እየሰማን ነው ። ሰው እንዴት ሕሊናውን ጥሎ ይጓዛል ? መድኃትንም ሐኪምንም ያዘጋጀ ፣ ጥበብን ለሰው የሰጠ እግዚአብሔር ነው ። መድኃኒታቸውን እየወሰዱ በሰላም መኖር ሲችሉ ጣሉ ተብለው ለጣር የደረሱ ፣ ለሞት የበቁ አያሌ ናቸው ። ሰው እንዴት ሕሊናውን ይጥላል ? “ወድጄሻለሁ” ከማለት አልፎ “አንቺን እንዳገባ እግዚአብሔር ነግሮኛል” ሲባሉ ሰተት ብለው የሚሄዱ ሰዎች ሕሊናቸውን የጣሉ አይደሉም ወይ ? የእግራቸውን እጣቢ ባናታቸው ላይ ሲደፉባቸው “አሜን ፣ አሜን” የሚሉ ፣ እንደ ፈረስ ሲሳፈሩባቸው “እልል” የሚሉ እንዴት ሕሊናቸውን ይጥላሉ ? በአደባባይ ገመናቸው ሲወጣ እግዚአብሔር አዋራጅ አምላክ ነው ወይ ? ብለው ለመጠየቅ ሕሊናቸውን የት ጥለውት ነው ? ስለሚያውቁት ኑሮአቸው ሲነገራቸው በደስታ የሚዘሉ የማያውቁትን መፍትሔ ግን አጥተው የሚመለሱ ሕሊናቸውን የጣሉ አይደሉም ወይ ? “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንዲሉ የጠንቋይ አምሮታቸውን በእግዚአብሔር ስም ለመወጣት “ተናገሩልኝ” የሚሉ ሰዎች ሕሊናቸውን የጣሉ አይደሉም ወይ ? አንዳንዶች ራሳቸውን ከሰው የሚፈልጉት እግዚአብሔር ለራሱ ለባለቤቱ ለመንገር አፍሮ ነው ወይ ?

ሐዋርያው ሕሊናቸውን ስለ ጣሉት ሰዎች ይናገራል ። ሁሉም ሰው በቂ እውቀት አይኖረውም ፤ ሁሉም ሰው ግን ማመዛዘኛ ሕሊና ተሰጥቶታል ። ሁሉም ሰው የነገረ መለኮት ግንዛቤ አይኖረውም ፤ ሁሉም ሰው ግን አታላዮችን ለማወቅ ሕሊናውንም መጠቀም አለበት ። “እግዚአብሔር የመገለጥ ወይስ የማጋለጥ አምላክ ነው ?” ብሎ ሰው እንዴት አይጠይቅም ? የሕይወታችንን መረጃ በቃሉ ውስጥ እንጂ በሰዎች ነቢይነት ውስጥ አስቀምጧል ወይ ? ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል ። እናጠምቃለን ፣ እንፈውሳለን ፣ እናውቃለን በሚሉ ዘንድ ብዙ ሰዎች የመንፈስ እስረኛ ሁነው ተቀምጠዋል ። ዕቃ ቢጭኑባቸው ፈረስ ነኝ የሚሉ ፣ አትውጡ ቢሏቸው ሎሌ ነኝ የሚሉ አያሌ ናቸው ። ብዙዎች ንብረታችሁን አስገቡና እዚህ ተቀመጡ ተብለው ቤታቸውን ለቀው ወጥተዋል ። በዚህ ዓመት ጌታ ይመጣል ተብለው ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት አስወጥተው መንነዋል ። ሕሊናቸውን የጣሉ በዚያ ዘመን ብቻ ሳይሆን በዚህ ዘመንም በዝተዋል ። ያልተማሩ ጮሌዎች የተማሩ ሞኞችን ሳይቀር በእምነት ስም ሲያታልሉ ይታያሉ ። ለማይረቡ አስተማሪዎች ተላልፈን የተሰጠን እስኪመስል ከሚያከብሩን የሚያዋርዱንን ፣ የሚንከባከቡን የሚገፈታትሩንን ወደናል ። ሐሰተኞቹ ጋ የምንሰስተው ገንዘብም ጊዜም የለም ፣ እውነተኞቹ ጋ ስንደርስ እጃችን ለመስጠት ፣ እግራችን ለመራመድ ይቆለፋል ።
“አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው ፥ መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ ፥ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና ፤” ይህን ቃል ስናነብ በእውነት እንባችን ወደ ውስጥ ይፈስሳል ። ከሚባርኩን አባቶች ወጥተን እግራቸውን ወደሚጭኑብን ስንነጕድ ፣ ከሚያሳልሙን አምልጠን የመኪናቸው ጎማ የረገጠውን ወደሚያስልሱን ስንሮጥ ፣ ልጆቼ ከሚሉትን ወጥተን ብራዘር ወደሚሉን ስንገሰግስ ያስተክዛል ። እኛን የማይመለከተውን የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃላት ሲደረድሩብን ለማን ነው የተነገረው ? አለማለታችን ይደንቃል ። ከዐውዱ ውጭ የተጠመዘዙ ጥቅሶችን እየተቀለብን ባልበሰለ ትምህርት የበሰሉትን መምህራን ስንንቅ በጣም ተጎድተናል ። “የአህያ ቆዳ ካልጋ ሲሉት ካመድ” እንዲሉ ከክብር ውርደትን ለምን እንደመረጥን ቆም ብለን ማሰብ ያሻናል ። ጮሌዎች እስከ መቼ የውሸት እያለቀሱ የእውነት ያስለቅሱናል ? በእውቀት በሥልጣኔ ማንም የማያታልላቸው ሰዎች በእምነት ነገር ጠፍተዋል ። ሐዋርያውንም የገረመው ይህ ነው ። በኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ክርክርና መለያየትን ያመጡት እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች ናቸው ። የብዙ የዋሃንን ልብ አስተዋል ። ባገለገሉአቸው ላይ ጠላት አድርገው አስነሥተዋቸዋል ። “አገባ ያለ ላያገባሽ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ” ይባላል ። እናገለግላችኋለን ያሉትን ጮሌዎች አምነው ብዙዎች የእውነት የሚያገለግሉአቸውን አምነው ሜዳ ላይ ቀርተዋል ። የነፋስ ሠረገላ ሜዳ ላይ ተሸክሞ ሸለቆ ላይ ይጥላል ። ማረፊያ ባለበት ሜዳ ላይ ልሸከማችሁ የሚሉ ተሸካሚ በሚያስፈልግበት ሸለቆ ላይ ጥለው ይሄዳሉ ። ሕሊና ግን “ለምን ?” ብሎ እንዲጠይቅ ተፈጥሯል ።
ሐዋርያው ለልጁ ለጢሞቴዎስ እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ ይለዋል ። እነዚህ ነገሮች ሚዛናዊነታቸውን ሲጠብቁ መልካሙን የእምነት ገድል መጋደል ይቻላል ። እምነት ያለ በጎ ሕሊና ሰማይን እንጂ ምድርን ፣ እግዚአብሔርን እንጂ ጎረቤትን ማየት አይችልም ። በጎ ሕሊና ያለ እምነትም ለሁሉም ስህተቶች ግላዊ ይቅርታ እያደረገ ይቀጥላል ። ሁለቱ ነገሮች በጣም አስፈላጊ ናቸው ። እምነት ለእግዚአብሔር በጎ ሕሊና ለሰው በጣም ያስፈልጋል ። ለእግዚአብሔር እምነት ፣ ለሰው በጎ ሕሊና ከሌለን መልካሙን ገድል መጋደል አንችልም ።
አሰስ ገሰሱን የሚያምኑ ፣ ሕሊናቸውን ቁጭ አድርገው ጮሌዎችን የሚያጅቡ እንዳሉ ሁሉ ጨርሶ የእምነት መንፈስ የተለያቸው ሰዎችን ማየትም እየበዛ መጥቷል ። ሁለቱም ጽንፎች አደገኛ ሲሆኑ የንጉሡ መንገድ ግን ከመካከሉ ነው ። በአጉል ትንቢትና በሐሰተኛ ተስፋ ያዘነ ትውልድ መጨረሻው ከሀዲ መሆን ነው ። እግዚአብሔር ያላለውን ብሏል እያሉ ተስፋም ቅጣትም መናገር በእግዚአብሔር ላይ ጠላት ማብዛት ነው ። ክርስትናን በምዕራቡ ምድር ያደረቁ እንዲህ ያሉ የሐሰት ተስፋዎች ናቸው ።
በጎ ሕሊና በየዕለቱ ልንለማመደው የሚገባን የሰላማችን መሠረት ነው ። ሁሉንም ነገር መጠራጠር ፣ ለነገሮች ሁሉ ክፉ ትርጉም መስጠት ፣ በሆኑ ነገሮች ስለተጎዳን በሚመስሉ ነገሮች መደንበር በጎ ሕሊናን መጣል ነው ። በጎ ሕሊናው ጨርሶ ሞኝ አድርጎን ሰው ተከታይ እንዳያደርገን ፣ በጎ ሕሊና ማጣቱም በጥርጣሬ ነፋስ እንዳያማታን መጠንቀቅ ያስፈልገናል ።
እምነት ሊኖረን ይገባል ። እገዚአብሔር እንዲህ ይላል እያሉ በሐሰት የሚናገሩ ሰዎች እግዚአብሔር ጨርሶ የማይል እንዳያስመስሉብን ፣ የማይናገርም አድርገን እንድንስለው እንዳያደርጉን መጠንቀቅ ይገባል ። እምነት ያስፈልገናል ። ዛሬም እግዚአብሔር በስሙ ፈውስን በረከትን ይሰጣል ። በእምነት የሚቀልዱ ሰዎች እምነት አልባ እንዳያደርጉን ፣ በጎ ሕሊናችንን እንደ ሞኝነት የሚቆጥሩም ክፉ እንዳያደርጉን ጥንቃቄ ያስፈልጋል ።
እምነትና በጎ ሕሊናን ይስጠን ብለን መለመን መልካም ነው ። መለማመድም ወሳኝ ነው ።
ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን ።
1ጢሞቴዎስ /21/
ታህሣሥ 4 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ