የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሕዝቡን የሚጠብቅ መስፍን

“እነርሱም፦ አንቺ ቤተ ልሔም ፥ የይሁዳ ምድር ፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም ፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው አሉት ።” ማቴ. 2፡5-6 ።
ይህንን ድንቅ ትንቢት የተናገረው ነቢዩ ሚክያስ ነው ። ይህ ትንቢት የተናገረው ከክርስቶስ ልደት 700 ዓመት ቀደም ብሎ ነው ። 700 ዓመታትን ወደፊት አሻግሮ በመንፈስ መነጽር የቤተ ልሔሙን ሕፃን ተመለከተ ። እጅ ነሣ ፣ ሰገደለት ። የክርስቶስ ልደት የአካል ብቻ ሳይሆን የተስፋ እድምተኞች ነበሩት ። ሚክያስ ሰባት መቶ ዓመት ወደፊት አሻግሮ ያየውን የክርስቶስን ልደት እኛም ሁለት ሺህ ዓመት ወደ ኋላ ተመልሰን ብናየው ለሚያነክሰው ሕይወታችን ብርታት የሚሰጥ ነው ። ትንቢት ከሰው የአእምሮ ብቃት ባሻገር በመንፈስ ቅዱስ የሚታይ የእግዚአብሔር እቅድ መግለጫ ነው ። እግዚአብሔር ከሰባት መቶ ዓመታት በኋላ ለሰው የሚያደርገውን ታላቅ ፍቅርና ትሕትና ለነቢዩ ገለጠ ። ነቢዩም ከሰባት መቶ ዓመታት በኋላ ስለሚደረገው የእግዚአብሔር የምሕረት ተግባር ተደሰተ ። እኛ ግን ነቢዩ የሚያምነውን አምላክ እያመንን ነገ አልታይ ብሎን እንጨነቃለን ። ይህን ትንቢት ከተናገረ በኋላ የባቢሎን ምርኮ አርባ ዓመት ሳይቆይ መጥቷል ። ለ500 ዓመታት ያህልም እስራኤል መሪ አጥታ ኑራለች ። በትንቢቱና በፍጻሜው መካከል ብዙ የመከራ ገደል ቢኖርም የእግዚአብሔር ሰው የፍጻሜውን እንጂ የመሐሉን አያይም ።
ይህ ትንቢት ለ700 ዓመታት የእስራኤል ልብ የጠገነ ፣ ጨለማውን የገፈፈ ፣ ተስፋንም ያበሰረ ነው ። ዛሬ ንጉሥ ባይኖረንም ትልቅ መስፍን ይነሣልናል ብለው ይጠብቁ ነበር ። የሚጠብቅ መኖር ይፈልጋል ። ነቢዩ ይህን ትንቢት የተናገረው ቤተ ልሔምን እያያት ነው ። ከተማይቱን እያዋራት ነው ። ጌታችን ከደብረ ዘይት ቁልቁል ወደ ኢየሩሳሌም ሲወርድ ኢየሩሳሌም እንዳናገራት ነቢዩም ቤተ ልሔምን አነጋገራት ። /ሉቃ. 19፡41-44/ ቤተ ልሔም እንኳን ድሮ ዛሬም ጎስቋላ ናት ። በእስራኤል ምድር ከሚታዩ ቦታዎች ቤተ ልሔም የተጎዳች ናት ። መልክአ ምድሯም ወጣ ገባ በመሆኑ ለእይታ የምትማርክ አይደለችም ። ይህችን ቤተ ልሔም ማነሷን የሚቀይር አንድ በረከት ይመጣል ። ማነሷም የሚወገደው መልክአ ምድሯ ተስተካክሎ ፣ ቤቶቿ እንደገና ተገንብተው አይደለም ። በዓይን የሚታየው ያው ነው ። የመንፈስ ልዕልናዋ ግን ከሁሉ የሚበልጥ ነው ። ይኸውም እግዚአብሔር የማዳን ጉዞውን በዚህች በቤተ ልሔም ጀመረ ። ሰው ክርስቶስን ሲያገኝ የሚታይ ኑሮው ባይለወጥም መንፈሳዊ ክብርና ሞገስ ግን ያገኛል ። ቤተ ልሔም የስሟ ትርጓሜ ቤተ ኅብስት ወይም የእንጀራ ቤት ማለት ነው ። ለዘመናት የስሟን ትርጓሜ አላገኘችም ። እነ ኑኃሚን ወደ ሞዓብ የተሰደዱት በቤተ ልሔም ራብ ተነሥቶ ነው ። /ሩት 1፡1/ አሁን ግን ዓለሙን ያጠገበው ኅብስተ ሕይወት ክርስቶስ በቤተ ልሔም ተወለደ ።
ቤተ ልሔም የተወዳጆች ከተማ ናት ። ራሔል የተቀበረችው በዚህች በኤፍራታ ቤተ ልሔም ነው ። ዘፍ. 35፡19 ። ዳዊት የተወለደው በቤተ ልሔም ነው ። የዳዊት ልጅ ክርስቶስም የተወለደው በቤተ ልሔም ነው ። ከትንሸዋ ከተማ ትልቅና ተወዳጅ ታሪክ ፈለቀ ። ትንንሾች ትልቅ አምላክ አላቸው ። ሁሉም ሰው ማነስን አይፈልግም ። ትልቁ ልዕልና ወይም ከፍታ ግን ክርስቶስ በነፍሳችን እንዲወለድ መፍቀድ ነው ።
ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ካንቺ ይወጣል አላት ። ነገሥታት በጠፉበት ከ500 ዓመታት በላይ መሪ ባልነበረበት አገር ይህ መስፍን የሚጠበቅ ነው ። እግዚአብሔር ለጨለማ ዓመታት የሚልከው ቃሉን ነው ። ይህ መስፍን የሚጠብቅ ስለሆነ እረኛም ነው ። መሳፍንት ሁሉ ሰራዊት ይጠብቃቸዋል ። ይህ መስፍን ግን ሕዝቡን የሚጠብቅ ነው ።
ዛሬም ኑሮዬ ቁልቁለት ሆነ ፣ ከአብሮ አደጎቼ የምከጅል ሰው ሆንሁ እያልን የምንተክዝ ፣ በማነሳችን የምናዝን ካለን ክርስቶስ በክብር በውስጣችን እንዲወለድ እንለምን ፣ ያን ጊዜ የመንፈስ ልዕልናን እናገኛለን ። አገሬ ከሁሉ አገር አነሰች ፣ የውርደቷም ማቅ ተቀዶ አላልቅ አለ የምትሉ ክርስቶስ በሰላም በውስጥዋ እንዲወለድ ጸልዩ ። ቤተ ልሔም ያነሰች የይሁዳ አንድ ክፍል ብትሆንም ጌታ ሲወለድባት ግን እስራኤልን የሚጠብቅ ፣ ከጠላት ፍርሃት የሚያድን መስፍን ወጣባት ። እግዚአብሔር ሕይወታችንን ሲባርከው ከእኛ ለብዙዎች ፣ ከአገራችን ለዓለም የሚተርፍ ነገር ይወጣል ።
ወዳጄ ሆይ አንሰህ አትቀርም ። እግዚአብሔር ከፍ ያደርግሃል ። በንስሐ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ቅረብ ። እህቴ ሆይ አንሰሽ አትቀሪም ካንቺ ለብዙዎች የሚሆን ብርሃን ይወጣል ። በንስሐ በጸሎት ጠብቂ ። አገሬ ሆይ አንሰሽ አትቀሪም ካንቺ ለዓለም የሚሆን መፍትሔ ይወጣል ። በንስሐ በጸሎት ወደ አምላክሽ ተመለሺ ።
የምትጠብቀን ገዥ ፣ የእስራኤል መስፍን ፣ የሕዝብህ እረኛ እባክህ ተነሣ  !!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ