የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሕዝቡ ሁሉ በሰላም ይደርሳል

የመጨረሻው ክፍል/አንብቡ

“ይህንም ብታደርግ ፥ እግዚአብሔር እንዲሁ ቢያዝዝህ ፥ መቆም ይቻልሃል ፥ ደግሞም ይህ ሕዝብ ሁሉ በሰላም ወደ ስፍራው ይደርሳል።” ዘጸ. 18፡23 ።

ሕዝብ ቆሞ የቆመ ነው ። መሪ ደግሞ ተቀምጦ የቆመ ነው ። የራስን ትዳር መምራት በሚከብድበት ዓለም የብዙዎችን ኃላፊነት የተሸከሙ አባቶች ሊጸለይላቸው ይገባል ። መሪነት ተፈጥሮአዊ ጥበብ ነው ። መሪነት ሳይንስ ሲሆን ቀመሩ ሕዝብን ሊጎዳ ይችላል ። መሪነት በትምህርት ሊደገፍ ይችላል ፣ መሪነት ግን ስጦታ ነው ። መሪነት ስለ ሕዝብ ቍጭት ፣ ውስጣዊ ቅዱስ ሕመም ላለው የሚሰጥ ኃላፊነት ነው ። እግዚአብሔር ለትልቁ ወንበር ለማብቃት በትንንሽ ድርሻ ሰዎችን ይሞክራል ። ዳዊት ታማኝ የበጎች እረኛ ስለ ነበር የሕዝብ መሪ አደረገው ። በምን እንድንመዝን አናውቅምና በተሰጠን ነገር ታማኝ እንሁን ። ሙሴም ከበግ ጥበቃ ላይ ለመሪነት ተጠርቷል ። ዳዊት የፊት ጕስቍልናውን ሳያስብ የበጎች እረኛ ነበረ ፣ ከደስታውም ብዛት የተነሣ በገና ይደረድር ነበር ። ሙሴ ደግሞ የፊት ጥሩ ኑሮውን ሳያስብ በግ ጠባቂነትን ተቀብሎት ፣ ከልዑልነት እረኝነትን በደስታ መርጦ ነበር ። እውነት ከሌለበት ልዑልነት ፣ እውነት ያለበት እረኝነት ይበልጣል ። ሙሴና ዳዊት አሁን ላሉበት ነገር መታመናቸው በእግዚአብሔር የመምረጥ ዕድል ሆነላቸው ። እግዚአብሔር ጸጋን የሚሰጠው እንደ አህያ በማሸከም ሥርዓት ሳይሆን ፍላጎትንና ተነሣሽነትን እንዲሁም ታማኝነትን አይቶ ነው ። የተሰጠው ጸጋ የሚያድገውም በሰውዬው ትጋት ነው ። አሊያ ልብ እንደሌላቸው እንደ ፈረስና በቅሎ አስሮ እየነዳን ነው ብለን እናስብ ነበር ። ርኵስ መንፈስ እንዳደረባቸውና በራሳቸው ማዘዝ እንደማይችሉ ሰዎች በሆንን ነበር ።

የሙሴ የቀድሞ ጌታ ፣ እንዲሁም መምህርና አማት የሆነው ዮቶር ይሉኝታን አርቆ መሪውን መከረ ። መሪ የሚያጠፋው የልኩን ያህል ነውና ዝም አይባልም ። ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል ማለት ቆሻሻውን ጠርጎ አልጋ ሥር ይደብቃል ማለት ሳይሆን ያጸዳል ማለት ነው ። “ሰውን ሲወዱ ከነ …” ቢሆንም በጽዳት ዘመን አጽድቶ መውደዱ ፣ ሌላ ሰውም እንዲወደው ማድረግ ነው ። ዮቶር ንግግሩን ቀጠለ፡- “አሁንም እመክርሃለሁና ቃሌን ስማ ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል ፤ አንተ በእግዚአብሔር ፊት ለሕዝቡ ሁን ፥ ነገራቸውንም ወደ እግዚአብሔር አድርስ ፤ ሥርዓቱንም ሕጉንም አስተምራቸው ፥ የሚሄዱበትን መንገድ የሚያደርጉትንም ሥራ ሁሉ አሳያቸው ። አንተም ከሕዝቡ ሁሉ አዋቂዎችን ፥ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን ፥ የታመኑ ፥ የግፍንም ረብ የሚጠሉትን ሰዎች ምረጥ ከእነርሱም የሺህ አለቆችን ፥ የመቶ አለቆችን ፥ የአምሳ አለቆችን ፥ የአሥርም አለቆችን ሹምላቸው ። በሕዝቡ ላይ ሁልጊዜ ይፍረዱ አውራውን ነገር ሁሉ ወደ አንተ ያምጡት ፥ ታናሹንም ነገር ሁሉ እነርሱ ይፍረዱ እነርሱም ከአንተ ጋር ሸክሙን ይሸከማሉ ፥ ለአንተም ይቀልልልሃል ። ይህንም ብታደርግ ፥ እግዚአብሔር እንዲሁ ቢያዝዝህ ፥ መቆም ይቻልሃል፥ ደግሞም ይህ ሕዝብ ሁሉ በሰላም ወደ ስፍራው ይደርሳል።” ዘጸ. 18፡19-23 ።

ምክርን የሚሰማ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ይሆናል ። ምክር የማይሰማ መንፈሰ እግዚአብሔር ይርቀዋል ። ሙሴ ዋነኛ ሥራው ነቢይነትና ካህንነት ነው ። በካህንነት በእግዚአብሔር ፊት ይገኛል ፣ በነቢይነት ያስተምራል ። የሙሴ ድርሻ መጸለይና ምሪት መቀበል ፣ እንዲሁም ሕዝቡን ማስተማር ነው ። ነገር ሲዳኝ መዋል የእርሱ ሳይሆን የሌሎች ድርሻ ነው ። ሙሴ ቦታውንና ድርሻን ማወቅ አለበት ። ከእርሱ ይልቅ የተሻለ አድርገው የሚሠሩ አሉና ዝቅ ያለው ነገር ላይ መዋል የለበትም ፣ አምኖ መስጠት አለበት ። ይህ ሲሆን ሌሎችም በጸጋቸው እንዲገለጡ ያደርጋል ። ሥራ ፈትንም ይቀንሳል ። ኃላፊነትን ያሰርጻል ፣ ተተኪ መሪዎችንም ያፈራል ። ታዲያ ዮቶር እስከ ዛሬ የሚጠቀስ ትልቅ የመሪዎች መስፈርትን አወጣ ። መሪን ለመምረጥና ኃላፊነትን ለመስጠት እንደ ሳሙኤል ቁመናን ማየት ፣ የአገር ፣ የጎጥ ልጅ መፈለግ ተገቢ አይደለም ። መስፈርት ከሌለ አገርና ትውልድ ያብዳሉ ።

መስፈርቱ አራት ነው ። አንደኛ አዋቂነት ፣ ሁለተኛ፡- ፈሪሀ እግዚአብሔር ፣ ሦስተኛ ታማኝነት ፣ አራተኛ፡- ጉቦን መጸየፍ ናቸው ። እውቀት አስፈላጊ ነው ፣ አለማወቅ እውርነት በመሆኑ ይዞ ገደል ይገባል ። ፈሪሀ እግዚአብሔር አስፈላጊ ነው ፣ ከበላዬ እግዚአብሔር አለ የሚል ወይም መሪ ያለው መሪ ሥራው የተለካ ነው። ታማኝነት በልብም ፣ በቃልም ፣ በሥራም ነው ። መሪ ያመነውን ወገን ሊታመንለት ይገባል ። ጉቦን መጸየፍ አስፈላጊ ነው ። ጻድቁን ኃጥእ ፣ ኃጥኡን ጻድቅ የሚያሰኝ ጉቦ ነው ። ሁሉ የእርሱ ነውና መደለያን መጸየፍ ይገባዋል ። ከሁሉ በላይ የወጡበት መሰላል ሊወርዱበትም ያስፈልጋልና ወገንን ማክበር ይገባል ።

“ይህንም ብታደርግ ፥ እግዚአብሔር እንዲሁ ቢያዝዝህ ፥ መቆም ይቻልሃል ፥ ደግሞም ይህ ሕዝብ ሁሉ በሰላም ወደ ስፍራው ይደርሳል።” ዘጸ. 18፡23 ። ሙሴ ድርሻውን ሲያውቅ ‹ በመስፈርት ሲሾም ፣ ኃላፊነትን ሲያከፋፍል ፣ ዋና ጉዳዮችን ብቻ ሲመለከት ያን ጊዜ ተቀምጦ መዋል ይቀርና መቆም ይችላል ፣ ጉዞም ይጀመራል ፣ የላላው ተስፋ ይጠብቃል ። ሁሉን ከያዘው ግን ዕድሜው እያጠረ ይመጣል ፣ የሚቆይበትንም ጊዜ አጉል ነዋሪ ሁኖ ያሳልፈዋል ። እርሱ ሲቆም ሕዝቡ በሰላም ወደ ስፍራው ይደርሳል ። እስራኤል በጉዞ ታክተው እዚሁ እንቅር ፣ ወደ ኋላ እንመለስ ብለው እንደ ነበር ይታወሳል ። ትውልድ ይመጣል ፣ ትውልድ ይሄዳል ። ሁሉም ነገር ወደታሰበለት ግብ እየተጓዘ ነው ። መሪ ከፊት ሲሆን ሕዝቡ በሰላም ይደርሳል ። አሊያ የራበው ሕዝብ መሪውን ይበላል የተባለው ይፈጸማል ። ትልቁ ረሀብ ፍርድ ማጣት ነው ።

መንፈሳውያን መሪዎች ፣ አባቶችና ሊቃውንት ሕዝብን ወደ ስፍራው በሰላም ለማድረስ ከሙሴ መማር ግድ ይላል ።

ተፈጸመ

ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ