ጀምረህ ከሆነ ሌሎች ይጨርሱታል ፥ ጨርሰህ ከሆነ ሌሎች ጀምረውታል። ይህ ግን ራእይን እንጂ ሕይወትን የሚመለከት አይደለም ። ሕይወትን ጀማሪና ፈጻሚ ልትሆን አትችልም ። አንተ ያለኸው በመካከሉ ላይ ነው ። የቀጠልከው ያልጀመርከውን ነው ፥ እየቀጠልህ ያለኸውም የማትጨርሰውን ነው ። ከኋላህ አባቶች ከፊትህ ደቀ መዛሙርቶች አሉ ። አንተ በመካከሉ ነህና ሁለቱም ዳር ያንተ አይደለም ። ለአባቶችህ ምዕራፍ ነህና ይደሰቱብሃል ። ያንተ ምዕራፍ ግን ደቀ መዝሙርህ ነውና ደስታህ ይቆይሃል ። ሙሉ ነገርን እንዲሁም ባዶ ነገርን አልተቀበልክም ። የማትሰጥ ድሃ ፥ የማትቀበል ባለጠጋ አይደለህም ። ባትሞላውም እንደሚሞላ ሆነህ ድከም ። በዓለም ላይ ካሉ ቅዱስ ሕመሞች አንዱ ይህ ነውና ። የሕይወትም ጣራ የማይደረስበት ነው ፥ አለመፈጸሙ ለነገው ትውልድ እንዳንጨርስበት ነው ። ሥራ ፈት ትውልድ እንዳይኖር ጉድለት በረከት ሁኗል።
ሙሉ ነገርን ለመስጠት አትድከም ። የማይነቀፍ ሥራ ለመሥራትም አትወጥን ። ሁሉም ነገር ጥሩ ይሆናል ብለህ አትገምት ። ይህ አደጋ ሳይሆን የምትኖርባትን ዓለም መተዋወቅ ነው ። ከሌለ ሙሉ ያለውን ጉድለት መቀበል ደስታ ይሰጣል ። ባይሞላም መጨመርህን አታቁም ። አሁን የምትሻው ቢሟላም ጉድለት ግን በሌላ መልክ ይመጣል። ጸሎትህን ቀጣይ የሚያደርገው “ጌታ ሆይ ና” የሚያሰኘው እኮ ይህ ነው ። የሚሰሙህ አክባሪዎችህ ናቸውና ደግሞም የመሰማት ዘመንህ ሳያልፍ ተናገር ። ከእምነትህ የሚወርሱ እውነተኛውን ሀብትህን ይካፈላሉና የማያልቀውን ስፈርላቸው ። ከልምድህ ለሚቀስሙ ፍጹሙን መምህር አሳያቸው ። ሙሉ ዓለም ያለው ሳይሆን የሚመጣው ነውና በጎዶሎ ዓለም ብታዝን ጥፋቱ ያንተው ነው ። ወንድ ልጅን አጥባ እንደማለት ነው ። ጡት አለው ወተት ግን የለውም ። ዓለም የፍጹምነት መሻት አላት ግን ፍጹምነት የላትም ። እጅግ ምስኪንነት ፍጹምነትን መሻት ነው ። የሕይወት ሙሉ ሥዕሉ ገና አልተገለጠም ። በጣም ሰፊ ነውና ከአዳም ጀምሮ እያዩት ነው። አንተም የአቅምህን ያህል አይተህ ለቀጣዩ ስፍራ ትለቃለህ ። ስታልፍ ሙሉነት ውስጥ ትጨመራለህ ። ቀጣዩም ትውልድ የማይጨርሰውን ይቀጥላል ። ሐረግን ነጠላ ሰረዝ ፥ መንገድን ድልድይ ያረዝመዋል ። ሁሉም ነገርህ ለማርዘም እንጂ ለመጨረስ አይደለምና ባልጨረስካቸው ትጋቶችህ ደስ ይበልህ ። ይህ ከገባህ ሕይወት ገብቶሃል ። መነቀፍን ከፈራህ አሁንም የፍጹምነት ታማሚ ነህ ። የሚነቀፍ ሕይወት ውስጥ ካለህ አሁንም ንስሐ የተዘጋጀው ላንተ ነው ። ቀጥሎ ያለውን ተመልከት፡-
…ሕይወት…
አንተ የመካከል ነዋሪ ነህ ። ትክክለኛ ሕይወትም የንጉሥ ጎዳና ናትና መሐሉን ትይዛለች። ልጀምር ልፈጽም ብላ አትታገልም ። አልፋ ዖሜጋነትን ከባለቤቱ አትነጥቅም። እንደ ፈሪሳዊ ወገኛ ፥ እንደ ሰዱቃዊ ዘበነኛ ሁለቱም መልካም አይደለም ። ሕይወት የመካከሉ ነው ። ፍጹምነትን መፈለግ ወይ የባሕል ወይ የዘመን ጥገኛ ያደርጋል። ብቻ ወዳጄ እንደሚጀምር ሰው እልኸኛ ፥ እንደሚፈጽም ሰው ትዕግሥተኛ ሁን ። አዎ አባቶችህ ጀምረውታል ። እነርሱም ክፍሉን አልዘጉትም ። መግቢያና ማጠቃለያው ካንተ ውጭ ነው ። ግና በአባቶችህ ወገብ ውስጥ ነበርህ ። ባንተ ወገብ ውስጥም ተማሪዎችህ አሉ ። የምታስተምረው በፈቃድህ ሳይሆን በግድ ነው ። ዓለሙ ትልቁ የመማሪያ ክፍል ነውና ሰዎች ይማሩብሃል ። አዎ አስተማሪ ነህ ። ዛሬን በትክክል ስትኖር ያልኖርክበትን ትላንትና ፥ የማትኖርበትን ነገ ሽልማት ተደርጎ ይሰጥሃል ። አራት ነጥብ መጀመሪያ ላይ የለም ። በጅምሩ ሕይወት ፍጹም ነገር አትፈልግ ። ለሁሉም ነገር ነጠላ ሰረዝ ስጠው ። እርሱ ያንተን ተስፋ ፥ የሰዎችን መለወጥ የሚጠብቅ ነው ።
መደምደሚያው ያለው በሰማይ ነው ። ግን የሕይወትህ ምዕራፍ የሚዘጋው “ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰላም ተገናኝቷል” በሚለው የደስታ ቃል ነውና ፍጻሜህን አታስበው ። ይልቁንም ዘምርበት ።
ዕለተ ወርቅ
ነሐሴ 12/2008 ዓ.ም.
ሰዓቱ 9፡00 ከቀኑ
ክብር ለእግዚአብሔር ፥ ጸጋ ለሚወዱት
ተጻፈ ለእገሌ / እገሊት