የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መልካሙ ገድል

“ጢሞቴዎስ ልጄ ሆይ፥ አስቀድሞ ስለ አንተ እንደ ተነገረው ትንቢት፥ በእርሱ መልካም ጦርነት ትዋጋ ዘንድ ይህችን ትእዛዝ አደራ እሰጥሃለሁ” 1ጢሞ. 1፡18 ።
የትንቢት አገልግሎት የከበረ ነው ። በዓለም ላይ በፖለቲካ ተንታኞች ፣ በአየር ንብረት ባለሙያዎች ትንበያ ይደረጋል ። በታላላቅ ውድድሮች ላይም ትክክለኛ ግምት የሰጡ ሰዎች ሽልማት ይቀበላሉ ። ዕድል ነጋሪዎችም በጥንቆላና በአስማት በመጠቀም ስለ ነገ ያወራሉ ። አስተዋይ ሰዎችም ነገ እንዲህ ሊሆን ይችላል ብለው ከቀኑ በፊት ቀኑን በማየት ይዘጋጃሉ ፤ በዚህም አደጋን ይቀንሳሉና ይደነቃሉ ። ያለ ጊዜው የተፈጠረ መሪ በመባልም ሙገሳ ያገኛሉ ። ትንቢት ግን ከዚህ የተለየ ነው ። በአጭሩ ትንቢት፡-
·        ትንተና
·        ግምት
·        ጥንቆላ
·        የመልካም ምኞት መግለጫ
·        ግጥምጥሞሽ
·        አስተውሎት አይደለም ።

ትንተናን ትንቢት ካልን ዙሪያ ገባውን በማጥናት ፣ ደመናውንና ነፋሱን በመመልከት መናገር እንጀምራለን ። ወጣት ሴት በማየት ስለ ትዳር ፣ ወንዱን በማየት ስለ ገንዘብ ፣ ሽማግሌውን በማየት ስለ ልጆች ነገር ፣ አገልጋዩን በማየት ስለ ብዙ ፍሬ ፣ ዶክተሩን በማየት ስለሚከፍተው ሆስፒታል መናገር ይህ ትንተና ነው ። አቋሙን ፣ ጾታውን ፣ አረማመዱን ፣ ስሜቱን በማንበብ እንዲህ ትሆናለህ ማለትም ግምት ነው ። በርኩስ መንፈስ በመመራትም ስለ ጎረቤት ክፉነት ፣ ስለ ምቀኛ መናገር ጠብን የሚያባብስ በመሆኑ ከቅዱሱ እግዚአብሔር የመጣ ትንቢት አይደለም ። በማስተዋልም እያዩ መራመድና ፣ ዛሬን በትክክል ኖሮ ለነገ ማትረፍ ትንቢት ሳይሆን አስተውሎት ነው ። ሕፃን ልጅን ትልቅ ሰው ትሆናለህ ማለት እየተጓዘበት ነውና ትንቢት አይደለም ። ተማሪን ትመረቃለህ ማለት የገባበት ጉዳይ ነውና ግድ ነው ። ሥራው ላይ ያለውን ሐኪም ሆስፒታል ትከፍታለህ ማለት ሥራ ፈጠራ እንጂ ትንቢት አይደለም ። ኃይለኛ ድምፅ በመጠቀም ሰውን የሚያስጮኹ የፈውስ ጸጋ የተሰጣቸው አይደሉም ፣ የፈውስ ጸጋ ያላቸው በዝምታም ያስወጣሉ ። እነ ማይክል ጃክሰን ሲዘፍኑ ብዙ ሰዎች የሚወድቁት በሚጠቀሙት የድምፅ ሞገድ እንጂ በፈውስ ጸጋ አይደለም ። ትልቁ የደም ሥር የሚያልፍበትን ቦታ ለይተው በመጨምደድ የሚጥሉ ፣ አውራ ጣት ሲረገጥ ሚዛንን መጠበቅ እንደማይቻል አጥንተው አውራ ጣትን በመርገጥ የሚያሽከረክሩ መለኮታዊ ጸጋ ሳይሆን ዘዴ የያዙ ናቸው ። የሚያስፈልገው የወደቀውን የሚያነሣ ጸጋ እንጂ የሚጥል አይደለም ። ከሺህ ሰው መካከል ቀይ የለበስሽ ማለት እውቀትም መገለጥም አይደለም ። ምክንያቱም ከሺህ ሰው መካከል ቀይ የለበሰች በግድ ትኖራለችና ። ዛሬ አዝነሽ ከቤትሽ የመጣሽ ፣ ባልሽ ያስለቀሰሽ ማለትም ብዙ አይደንቅም ፤ ባሏ የማያስለቅሳት ሴት ማግኘት ከባድ ነውና ። 
ሐዋርያው ጴጥሮስ፡- ይህን በመጀመሪያ እወቁ ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም ፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና ፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩይላል ። 2ጴጥ. 1፡20-21 ።
ትንቢት የተባለው የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ከልብ አፍልቆ መናገር ተገቢ አይደለም ። እግዚአብሔርን የውሸቱና የስሜቱ ተባባሪ በማድረጉ ታላቅ ፍርድ ይጠብቀዋል ። ለሰዎች ያለንን መልካም ምኞት መግለጥ ተገቢ ቢሆንም ትንቢታዊ ማድረግ ግን ተመጻዳቂነት ነው ። በትንቢት ቁርስ መብላት ፣ በትንቢት ትምህርት ቤት መመዝገብ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች ለከንቱነት ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ናቸው ። የሚሰሙትን ቃል በሙሉ ትንቢታዊ ማድረግ ትልቅ አደጋ ውስጥ የሚከት ነው ። ለምሳሌ አንድ ፈላስፋ፡- “ዛሬ ማታ እንሚሞት ሁነህ ተዘጋጅ ፤ ዘላለም እንደሚኖር ሁነህ ሥራህን ሥራ” ብሏል ። ይህ አባባል ትክክለኛ ነው ። ሞትንና ሕይወትን ስለ ማሰብ የሚናገር ነው ። ሰው በሞትና በሕይወት መካከል የሚኖር ፍጡር ነውና ። ይህን ቃል የሰማች አንዲት ሴት እንደሚሄድ ተዘጋጂ ተብያለሁ አሜሪካ እሄዳለሁ ፣ ሥሪ ተብያለሁ እስክሄድ ድረስ ሥራዬን እሠራለሁ ብትል የራስዋ ግምት እንጂ ትንቢት አይደለም ። ስብከታቸውን በሙሉ ትንቢታዊ የሚያደርጉ ሰባክያን ፣ ትንቢታዊ ማዳመጫ ገጥመው የሚሰሙ ምእመናን ትልቅ ጉዳት ውስጥ ይገባሉ ።
ትንቢት አንድን ሰው ስናየው የሚሰማን ስሜት አይደለም ። የሰው ፈቃድ ካለበት ትንቢት መሆኑ ይቀራል ። ለሚወዱት ትልልቅ ዳቦ እየቆረሱ መናገር ፣ የሚጠሉት ላይ አመድ እየነሰነሱ መፎከር ይህ ትንቢት ላይሆን ይችላል ። ትንቢት እንድንናገርላቸው ጠርተውን ዶሮ ወጥ እያቀረቡ ፣ ጥብሱ እየሸተተን ምን ዓይነት ክፉ ነገር ልንናገር እንችላለን ? የግል ተንባይ ይዘው የሚንቀሳቀሱ መሳፍንት በቀደመው ዘመን ነበሩ ። ዛሬ ብዙ ባለጠጎች አሉ ። ትንቢት ግን ከሰው ፈቃድ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ነው ። ሰው ፈቅዶ የሚነግረን ፣ እኛም ልስማው ብለን የገመትነውን ሳይሆን እግዚአብሔር በራሱ ውዴታ የሚነግረን ድምፅ ነው ። ሐሰተኛ ትንቢቶች በዘመነ መሳፍንት የጦርነት መነሻ ሁነው ሲያስተላልቁ ኑረዋል ፤ ዛሬም ሰነፍ ትውልድ ያመርታሉ ፤ ነገ ደግሞ እግዚአብሔር የለም የሚሉ ከሀዲዎችን ያበዛሉ ።  
በእስራኤል ሦስት ዘመናት አልፈዋል ። እነዚህ ዘመናት ዘመነ መሳፍንት የሦስት መቶ ዓመት ታሪክ ፣ ዘመነ ነገሥት የአራት መቶ ዓመት ታሪክ ፣ ዘመነ ካህናት የአምስት መቶ ዓመት ታሪክ ናቸው ። በዘመነ መሳፍንትና በዘመነ ካህናት ነቢያት አልነበሩም ። እነዚህ ዘመናት በእስራኤል ቋሚ ነገሥታት ያልነበሩባቸው ዘመናት ናቸው ። ነቢያት አገራዊ አጀንዳ ፣ ሕዝባዊ መፍትሔ ይዘው የሚመጡ እንጂ በየጓዳው ለባለጠጋና ላበላቸው የሚተነብዩ የቤት ሠራተኞች አይደሉም ። የነቢያት ትልቁ አገልግሎታቸው ክርስቶስ ይመጣል ብለው ተስፋ መስጠት ነበረ ። ዛሬ ክርስቶስ ስለ መጣ ለፍቅሩ በመኖር መታዘዝ ይገባናል ። በነቢያት አገልግሎትም ማስተማር ፣ ስለ ነገ መናገር ፣ መገሠጽ ፣ መጻሕፍትን መጻፍ ዋነኛ ሥራቸው ነው ። ነቢያት ስለ ነገ የተናገሩት በአገልግሎታቸው ሩብ ያህል እንኳ አይሆንም ። ዛሬን ረስቶ ነገን የሚቧጥጥ አገልግሎት ሙሉ አይደለምና ።
ወጣቱ ጢሞቴዎስ ግን በደጋግ የእግዚአብሔር ሰዎች ትንቢት ተነግሮለት ነበር ። ትንቢቱም እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል ፣ በአገልግሎቱ የተለያየ ፈተና እንደሚገጥመውና ጸንቶ እንዲጋደል ነበረ ። የትንቢት ዓላማው ማስነፍ ሳይሆን ማዘጋጀት ነው ። እግዚአብሔር ትንቢትን አስቀድሞ የሚልከው፡-
1-  በእግዚአብሔር ወደ ታየ ቀን እንደምንሄድ አውቀን ልበ ሙሉ እንድንሆን ነው።

2-  በፍጻሜው ቀን ተቃዋሚ እንዳንሆን ነው ።

3-  ከስጦታው በፊት የመቀበል አቅም እንዲኖረን ነው ።

4-  በሚመጡት በጎና ክፉ ነገሮች እንዳንደናገጥ ነው ።
ጢሞቴዎስ መልካሙን ጦርነት እንዲዋጋ ሐዋርያው ያሳስበዋል ። መልካም ያልሆኑ ጦርነቶች አሉና ። ለክብርና ለዝና መጋደል ፣ ሌላውን ጠልፎ ለመቅደም መሞከር ፣ እኔ ብቻ ይድላኝ ብሎ የሌሎችን ኑሮ መዝጋት ፣ ስሜ ተነካ ብሎ ጦር መወራወር እነዚህ መልካም ጦርነቶች አይደሉም ። ስለ ወንጌልና ስለ እውነት የሚቀበሉት መከራ ግን መልካም ጦርነት ነው ።
ከመልካሙ ገበያ ያውለን ።
1ጢሞቴዎስ / 20/
ታኅሣሥ 3 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ