የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መሰልቸት

 
መሰልቸት ገጥሞህ ያውቃል ? ዛሬስ ተሰምቶሃል ? ካልሆነም አንድ ቀን ሊሰማህ ይችላልና እስቲ አዳምጥ ፡፡
 
መሰልቸት ጊዜ ፣ ጉልበት ፣ ዕድል እያለ ለመራመድ አለመፍቀድ ነው ፡፡
 
መሰልቸት ከሞት በፊት መሞት ፣ገዳይ ሳይመጣ ሞቶ መጠበቅ ፣ ሞትን መንገድ አጋምሶ መቀበል ነው ፡፡ መሰልቸት ስለ ትላንት ማሰብ አይደለም ፣ በጣም ስለ ትላንት በማሰብ መሪውን ወይም በትሩን መጣል ነው ፡፡ መሰልቸት ስለ ነገ ማሰብም አይደለም ፣ ነገን ማየት አለመቻልና ለመኖር አለመፍቀድ ነው ፡፡ መሰልቸት መናደድ ቢሆን በአንድ ነገር ይወጣ ይሆናል ፣ መሰልቸት ግን የፍግ እሳት ሲሆን ውስጥ ውስጡን ባለቤቱን በልቶ የሚጨርሰው ነው ፡፡ መሰልቸት ጭስ የማይታይበት ቃጠሎ ነው ፡
 
አጠገባችን ያሉ ስንፍናችን ፣ ልፍለፋችን ፣ ማጉረምረማችን ያደከማቸው ሰዎች ይሰለቹናል ፡፡ እኛን ሳይሆን ራሳቸውን እያራቁ ይመጣሉ ፡፡ እናጠፋው ዘንድ ሁሉንም ነገር ይተዉልናል ፡፡ ያለማቋረጥ የሰዎች ኑሮ እንቅልፍ ሲነሣንና ፣ የራሳችንን አስቀምጠን የሰው ወጥ ስናማስል ለጥቂት ጊዜያት ያደነቁን ሰዎች ይሰለቹናል ፡፡ መሰልቸት ከጥጋብ በላይ በመሆኑ ሊያዩን ይሳናቸዋል ፡፡ መቼም ሰልችቻለሁ ወይስ አሰልችቻለሁ ? ማለት ተገቢ ይመስላል ፡፡ ምክንያቱም መሰልቸት ጠብ ስለሌለው መራራቅና መረሳሳት ያመጣል ፡፡ እግዚአብሔር ርእስ ያልሆነበት ማንኛውም ግንኙነት የሚደመደመው በመሰለቻቸት ነው ፡፡
 
መሰልቸት መቆጣት አይደለም ፣ መቆጣት ገና ተስፋ ማድረግ አለው ፡፡ መሰልቸት ግን ለነገሮች ትርጉም ማጣት ነው ፡፡ መሰልቸት መጥገብ አይደለም ፣ መጥገብ በትክክል የመመገብ ድንበር ነው ፡፡ መሰልቸት የተዘረጋውን ገበታ በቃኝ ማለት ነው ፡፡ መሰልቸት ተደራራቢ ከሆኑ የሕይወት ፈተናዎች የሚመጣ ነው ፡፡ ሰይጣን አንድን ዓይነት ፈተና በመደጋጋም ሲያመጣ መሰልቸት ይመጣል ፡፡ መሰልቸት ሞዛዛ ከሆኑ ከሰይጣን ፈተናዎች የሚመጣ ነው ፡፡ ተደጋጋሚ በሽታ ፣ ተደጋጋሚ ማጣቶች ፣ ተደጋጋሚ ቤተሰባዊ ችግር ፣ ተደጋጋሚ በሰዎች መከዳት ሲገጥም መሰልቸት ይመጣል ፡፡ መሰልቸት ከጠላት ጋር ለመታረቅና ጊዜያዊ ሰላም ለማግኘትም የሚዳርግ ነው ፡፡ መሰልቸት ግን ማልቀስ ቢሆን ይቀል ነበር ፡፡ መሰልቸት ለማልቀስም አቅም ማጣት ነው ፡፡ መሰልቸት በውስጡ ቁስለት ፣ አልቻልም ባይነት ፣ በቃኝ ብሎ መሸነፍ ፣ ይህን ዓለም መጥላት ፣ ተስፋ መቁረጥ አለው ፡፡
 
የምንፈልጋቸው ነገሮች አለመሆናቸው ፣ ሰዎች ለራሳቸው ስሜት ብቻ መኖራቸው ፣ የማንውጠው የማንተፋው ጉዳይ ፣ በልቅሶም በሳቅም መግለጥ ያዳገተ መንቻካ ነገር ሲገጥም መሰልቸት ይመጣል ፡፡ ዓይንን ከክርስቶስ ላይ ዘወር አድርጎ ሰዎች ላይ ማድረግ ሲጀመር መሰልቸት ይመጣል ፡፡ ይህ ከባድ ውድቀት አለው ፡፡ ፈተናው ገደል አፋፍ ላይ ሊያደርሰን ይችላል ፡፡ መሰልቸት ግን ገደል ውስጥ ዘለን እንድንገባ ያደርገናል ፡፡ መሰልቸት ፈተና ሳይሆን ለፈተናው ያለን የመጨረሻ ምላሽ ነው ፡፡
 
በኀዘን ላይ ሰዎች ሲያለቅሱ ይውጣላቸው ተዉአቸው ይባላል ፡፡ መሳቅ ከጀመሩ ግን ወዲያው ይይዟቸዋል ፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ ከኀዘን እያለፈ ነውና ፡፡ መሰልቸት ስሜታዊ መገለጫዎችን ከመጠቀም በላይ ነው ፡፡ ማስረዳት አለመቻልና አለመፈለግ ፣ ዋጋ የለውም ብሎ ጨርሶ መኖር ፣ ግን ይህ ሁሉ ለምን ሆነ ? የሚል ጥያቄ ነው ፡፡ ሰይጣን እንድንሰለችና ከመስመር እንድንወጣ ተደጋጋሚ ፈተናዎችን ያመጣብናል ፡፡
 
የፉክክር ኑሮ ውስጥ መግባት አደገኛ የመሰልቸት መምጫ  ነው ፡፡ በቀላሉ የምናደርገውን ነገር ሰዎች እንዲያደርጉት መጠበቅ ከመሰልቸት ያደርሳል ፡፡ ሁሉንም እንደ አመጣጡ መመለስ አለመቻል ፣ የውጊያ ሽሽት ወደ መሰልቸት ያደርሳል ፡፡ “ውኃ ቢወቅጡት እንቦጭ” ሲሆን መሰልቸት ይወለዳል ፡፡ ሰዎችን ለማስደሰት መሞከር መሰልቸት ያመጣል ፡፡ ሰዎች የሚከፉት እናስደስታችሁ ባልን ቁጥር ነው ፡፡ ለእግዚአብሔር ደስታ ስንኖር እርሱን የሚያውቁ ይደሰቱብናል ፡፡ የማይበስሉ ነገር ግን ማገዶ የሚፈጁ ሰዎች መሰልቸት ያመጣሉ ፡፡ ያልተማሩ የተማረውን መንቀፋቸው ብቻ ሳይሆን የተማረው ባልተማሩት ተስፋ መቁረጡ የአገራችን ትልቅ ችግር ነው፡፡ አዎ መሰልቸትን የምንከላከለው በአንድ መንገድ ብቻ ነው ፡፡ እግዚአብሔርን በማየት ፡፡
 
ከሁሉም ነገር መጠበቅ ያለብን የልኩን ነው ፡፡ ከአበባ ጊዜያዊ ውበትን፣ ከእንስሳ ጊዜያዊ ወዳጅነትን ፣ ከሰዎች መለዋወጥን መጠበቅ አለብን ፡፡ የልኩን ያህል የኖረ ሰው ዛሬ እኛን ለማስደሰት ከልኩ በላይ አይሆንም ፡፡ የሚመጥነንን ባንሰማም የሚመጥናቸውን እንደ ተናገሩ ፣ የሚመጥነንን ባንቀበልም የሚመጥናቸውን ያህል እንደ ወረወሩ መገንዘብ አለብን ፡፡ እግዚአብሔር ግን የልኩን ያህል ይገለጣል ፡፡ ለሰማያዊ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ለምድራዊ ኑሮም እግዚአብሔርን ማየት ያስፈልገናል ፡፡
 
መሰልቸት የሚወዱትን ያስጠላል ፡፡ እየመጣ ያለውን ደስታም ይገፋል ፡፡ የጸሎት መልሱንም አይፈልግም ፡፡
 
በልጅ ሕመም ፣ በኑሮ ችግር ፣ በትዳር ውጣ ውረድ ፣ በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ሆናችሁ መሰልቸት የገጠማችሁ ፣ ከሊቶስጥራ እስከ ቀራንዮ መስቀልን ፣ ለእርሱ የማይገባውን መከራ የተሸከመውን ጌታ አስቡ ፡፡ አካባቢያችሁን ስታዩና ስታዳምጡ ትሰለቻላችሁ ፡፡ የጠራችሁን ጌታ ስታዩ እንደ ጴጥሮስ ውኃውን እንደ ዓለት ትረግጣላችሁ ፡፡
 
 
 
የደስታ ቋጠሮ/17
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
 

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ