መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » መስቀል ቅዱስ ኤፍሬም /306-373 ዓ.ም./ እንደሰበከው

የትምህርቱ ርዕስ | መስቀል ቅዱስ ኤፍሬም /306-373 ዓ.ም./ እንደሰበከው

እንኳን ለ2011 ዓ.ም የመስቀል በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ !
መስቀል የጣዖት አምልኮን አጠፋ። ለዓለም ሁሉ በማብራት ሁሉንም ሕዝብ ወደ አንዲቷ ቤተ ክርስቲያን በመሰብሰብ በፍቅር አንድ አደረጋቸው።
†         መስቀል የሙታን ትንሣኤ ነው ።
†         መስቀል ለክርስቲያኖች ተስፋ ነው ።
†         መስቀል ለሽባው ምርኩዝ ነው ።
†         መስቀል ለድሀው አጽናኝ ነው ።
†         መስቀል የትዕቢተኛው መጥፊያ ነው ።
†         መስቀል ተስፋ ለቆረጡ ተስፋ ነው ።
†         መስቀል በባሕር ለሚጓዙ/ለመርከበኞች ምግብ ነው ።
†         መስቀል ለአውታታዎች መሸሸጊያ ነው ።
†         መስቀል ለድሀ አደጎች አባት ነው ።
†         መስቀል ለኀዘነተኞች መጽናናት ነው ።
†         መስቀል የሕፃናት ጠባቂ ነው ።
†         መስቀል የሰው ልጅ ክብር ነው ።
†         መስቀል የሽማግሌዎች አክሊል ነው ።
†         መስቀል በጨለማ ለሚኖሩት ብርሃን ነው ።
†         መስቀል ለባሮች ነጻነት ፣ ላልተማሩት ጥበብ ነው።
†         መስቀል የነቢያት ስብከት ፣ የሐዋርያት የመንገድ ጓደኛ ነው ።
†         መስቀል የልጃገረዶች ድንግልና ፣ የካህናት ደስታ ነው ።
†         መስቀል የቤተ ክርስቲያን ብሎም የዓለም መሠረት ነው ።
†         መስቀል የአብያተ ጣዖታት ውድመት ፣ የአይሁዳውያን ፈተና ነው።
†         መስቀል የለምጻሞች መንጻት ፣ የደካሞች ብርታት ነው ።
†         መስቀል ለተራቡ እንጀራ ፣ ለተጠሙ ምንጭ ነው ።
†         መስቀል የመነኮሳት መልካም ተስፋ ፣ ለተራቆቱትም ልብስ ነው ።
በዚህ ቅዱስ መሣሪያ ጌታችን ክርስቶስ ሁሉንም ይውጥ የነበረውን የሲዖልን አንጀት አራቆተ በዲያብሎስ አፍ ያሉትን ብዙ ወጥመዶችም ዘጋ። መስቀልን ተመልክቶ ሞት ፈራ ፤ ከአዳም ጋር አብሮ ይዞ የነበረውን ሁሉን ፍጥረት ለቀቀ ። እግዚአብሔርን የተሸከሙ ሐዋርያት መስቀልን ታጥቀው የጠላትን ሁሉንም ኃይል ድል አደረጉ ፤ ሰውን ሁሉም በመረባቸው አጠመዱ። የተሰቀለውንም እንዲያመልኩ ሁሉንም አንድ ላይ ሰበሰቡ ። (ወታደሮች) በጦር መሣሪያ እንደሚታጠቁት የክርስቶስ ሰማዕታት የአሳዳጆችን ዕቅድ ሁሉ ድል አደረጉ ። በግልጽም መስቀል የተሸከመውን አምላክ ሰበኩ። ለክርስቶስ ብለው መስቀሉን ተሸክመው በዓለም ያለውን ሁሉንም ነገር ካዱ ፤ በበረሃና በተራራ በዋሻ ኖሩ ፣ ዓለምንም እንቢ አሉ ።
ነገር ግን ይህ የማይበገር የኦርቶዶክስ ግንብ ፣ የሰማያዊው ንጉሥ የድል መሣሪያ የሆነውን መስቀሉን ለማመስገን የተገባ ቋንቋ እንዴት ያለ ነው !? ኃያሉ ጌታ በመስቀል  በቃላት የማይገለጥ በረከትን ለሰው ልጆች ሰጠ ።
ስለዚህ በግንባራችን ፣ በዓይናችን ፣ በአፋችንና በደረታችን ላይ ሕይወት የሚሰጠውን መስቀል እናስቀምጥ ። (እነዚህን አካሎቻችንን) የክርስቲያኖች የማይበገር መሣሪያ ፣ የአማኞች ተስፋና ብርሃን በሆነው በመስቀል እናስጊጣቸው ። በዚህ የኦርቶዶክስ እምነት ምርኩዝ ፣ አዳኝ በሆነውም በቤተ በክርስቲያን የምስጋና መሣሪያ ገነትን እንክፈት ። ለአንድ ሰዓትም ይሁን ለአንዲት ቅጽበት መስቀልን አንርሳ ፤ አሊያም ያለ መስቀል አንዳች አናድርግ ። ነገር ግን እንቅልፍ ስንተኛ ሆነ ስንነሣ ፣ ስንሠራ ሆነ ስንመገብ ወይም ስንተኛ ፣ መንገድ ስንጓዝም ሆነ በባሕር ስንሄድ አሊያም ወንዝ ስናቋርጥ የአካል ክፍሎቻችንን ሁሉ ሕይወት ሰጪ በሆነው መስቀል እናስጊጥ ። “ከሌሊት ግርማ ፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ ፥ በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ነገር ፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን” (መዝ 90(91)፥5-6) አንፍራ ። ኦ! እናንተ ክርስቲያኖች ሁልጊዜ የክርስቶስን መስቀል እንደ ረዳትና አጋዥ ከጎናችሁ ከያዛችሁ የሚቃወመን ኃይል አይቶት ይርዳል ፤ ይሸሽማልና ።  “ዲያብሎስ ወደ እናንተ አይመጣም፤ አንዳች መቅሰፍትም ወደ መኖሪያችሁ አይገባም ።”
ለዘላለሙ አሜን !
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ