የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መቃብሩ ባዶ ነው!

                                                    የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ….. ዓርብ ሚያዝያ ፪/ ፳፻፯ ..
ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ እንደጻፈው፡- ከሳምንቱ በፊተኛው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለማ ሳለ ማለዳ ወደ መቃብር መጣች ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች፡፡ እንደ አይሁድ ልማድና ወግ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ በሦስተኛው ቀን ሽቶ ልትቀባው የጨለማው ግርማና የአይሁድ የፈሪሳውያን ዛቻና ቁጣ ሳያስፈራት በመቃብሩ ስፍራ የተገኘችው ማርያም እንዳሰበችው በመቃብሩ ስፍራ የጌታን ሥጋ አላገኘችም፡፡ በስፍራው ያጋጠማት ባዶ መቃብር ነበር፡፡ እናም በድንጋጤና በፍርሃት ውስጥ ሆና ይህን አስደንጋጭ ዜና ወደ ጴጥሮስና ጌታ ይወደው ወደነበረው ደቀ መዝሙር ለመንገር ገሰገሰች፡፡
 
 ሐዋርያቱም የምትለው ነገር እውነት እንደሆነ ለማረጋገጥ ወደ መቃብሩ ስፍራ አብረዋት መጡ፡፡ በእርግጥም ኢየሱስ ክርስቶስ በመቃብሩ ውስጥ የለም፡፡ መቃብሩ ባዶ ነው፡፡ እናም ሐዋርያቱ እያዘኑና እየተከዙ ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ ምናልባት በልባቸው ቀናተኞቹ አይሁድ ወስደው በሌላ ስፍራ ደብቀውት ይሆናል በማለት በጠላቶቻቸው ዓይን ውስጥ እንይገቡ በመፍራት ከመቃብሩ ስፍራ ላለመታየት ሐዋርያቱ ከዛ ስፍራ በቶሎ የተሰወሩ ይመስላል፡፡

እነዚህ የጌታ ደቀ መዛሙርትና ተከታዮች ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ስለ መከራው፣ ሞቱና ትንሣኤው የተናገራቸው ቃል ከልባቸው ጽላት ገና አልተጻፈም ነበርና ሞቱ በእጅጉ ያሳዘናቸውና ተስፋ ያስቆረጣቸው ሐዋርያቱ አሁን ደግሞ የጌታቸውና የመምህራቸው ሥጋው ከመቃብሩ ባለመኖሩ እጅግ አዝነውና ተክዘው ግራ በተጋባ መንፈስ እያዘኑና እየተከዙ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነው ወደ ቤታቸው አመሩ፡፡ ማርያም ግን የሕይወቷን ጌታና አምላክ፣ ለመረረ ኑሮዋ ጣዕም የሰጣትን ስሟንና ታሪኳን የቀየረላትን ጌታ ሳታገኘው ከመቃብሩ ስፍራ ላለመሄድ ወሰነች፡፡ እናም ዓይኗን ወደ ባዶው መቃብር መልሳ የጌታዋን መልካምነት፣ ፍቅሩን፣ ቸርነቱንና ምሕረቱን እያሰበች የፍቅር ዕንባዋን ማዝራት ጀመረች፡፡ በዛ ሁሉ የጌታ መከራ፣ ጭንቀትና ስቃይ ልቧን የሐዘን ጦር የወጋው፣ ሞቱ በእጅጉ ዕረፍት የነሳት መግደላዊት ማርያም አሁን ደግሞ ከመቃብሩ ስፍራ ያጣችው የጌታ ሥጋ ሌላ ሕመም ሌላ ስቃይ የጨመረባት ይመስላል እናም ዕንባዋ ከዓይኗ ብቻ ሳይሆን ከልቧ ውስጥ የፈለቀ ነበር፡፡


በእርግጥም ማርያም ለሩኅሩኁ ጌታ የነበራት ፍቅርና መገዛት እንዲሁ ተራና በቃል ብቻ የሚገለጽ አልነበረም፡፡ ፍቅሯ ከውስጥ ከነፍሷ የመነጨ ውድና ክቡር እንጂ እናም የማንንም ዛቻና ቁጣ ሳትፈራ   በዕንባ ጎርፍ እየታጠበች በጌታዋ መቃብር ስፍራ በትካዜ ሆና ቆዘመች፡፡ ጽናቷና ፍቅሯም የጨለማውን ግርማ የገፈፈ፣ ፍርሃትንና የአይሁድን ዛቻና ቁጣ ጸጥ ያደረገ፣ ከተራ ወኔና ድፍረት በእጅጉ የተለየ ልዩ ፍቅር፣ ልዩ ጽናት ነበር፡፡ ይህችን ፍቅር ያጀገናትን፣ ፍቅር ያበረታትን፣ ፍቅር ኃልና ወኔ የሆናትን አይሁዳዊ ሴት ኢየሱስ ብቻዋን በሐዘን ተውጣ በቆዘመችበት ስፍራ ተገልጾ «ማርያም» ሲላት ያ የለመደችውና የምታውቀው የፍቅር ቃል ጥሪው በጆሮዋ አልፎ ነፍሷ ድረስ ዘልቆ ተሰማት እናም ማርያም «ረቡኒ» አለችው ፊቷ በደስታና በሐሴት በርቶ፡፡ ትንሳኤና ሕይወት የሆነውን ጌታ አብዝታ ለፈለገችው፣ በብዙም ለወደደችው ልቧን በአዲስ ተስፋ ሊሞላው ኢየሱስ በመቃብሩ ስፍራ ለማርያም ተገለጸላት፡፡ ትንሣኤውንም ለማብሰር የተመረጠችና የመጀመሪያም ሆነች፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ለሁሉ ድንቅ የሆነ ነው፡፡ ሞት ለዘመናት የሰው ልጆችን ሁሉ ያሰጨነቀና ያሰገበረ የዘመናት ጠላት ነበር፡፡ መጽሐፍ እንደሚል ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ፡፡ በኃጢአትም ሞት እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትና ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፡፡ ይህን የማይቋቋሙትንና የማይጋፉትን ባለጋራ የሰው ልጅ በዘመኑ ሁሉ በፍርሃት የብርድ ቆፈን ውስጥ ሆኖ ይጠባበቅ ነበር፡፡ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ሰዎች ሞት በጨካኝ መዳፉ ጭብጥና እርግጥ አድርጎ ገዝቶአል፡፡ የዚህ ሞት ኃያልነትና ጭከናም ለብዙዎች የዓለማችን ሊቆችና ፈላስፎች ትልቅ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ የቆየ ነው፡፡ የሞትን ምስጢራዊ ኃይልና ብርታት ለመመራመርና ለመፈተሽ የሞከሩ ሁሉ ከድካምና ተስፋ ከመቁረጥ ውጪ አንዳንች ነገር ማድረግ ሳይቻላቸው እነርሱም በስተመጨረሻ የሞትን ጽዋ እየመረራቸውና እየዘገነናቸውም ቢሆን ሊጨልጡት ተገደዋል፡፡
ዛሬም በዘመናችን ስለ ሞት ሲነገር ስለ ሞት ሲወራ ፍርሃት መላ አካላቸውን የሚያርደው ጭንቅ ጥብብ የሚላቸው በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ ሞት በአካል መጥቶ አይደለም ገና የሞት ዜና ሲነገር የሚገቡበት የሚጠፋቸውን ወዳጆቻችንን የታዘብንበት አጋጣሚ እንደማይጠፋም አስባለሁ፡፡ በእርግጥ ሞትም ምስጢር የሚያደርገው ነገር ቢኖር በኃይላቸው፣ በጀግንነታቸው፣ በውበታቸው፣ በእውቀታቸው የተከበሩና ዓለማችንን ያስደነቁና ማንም አይደፍራቸውም የተባሉትን ሰዎች እንኳን ያ ሁሉ ኃይለኝነታቸውና ጀግንነታቸው፣ እውቀታቸውና ውበታቸው ሁሉ የሞትን ኃይል ማስገበርና መርታት ሳይችል ቀርቶ ከመቃብር አፋፍ ሲወርዱ አይተን ወይ ጉድ በማለት አዝነናል፣ ተገርመናልም፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ምናለ እንዲህ ዓይነቶቹ ጠቃሚ ሰዎች ሁሌም በኖሩ ብለን የተመኘንላቸውን ሞት ሲነጥቃቸው እያየን ሞትን የተራገምንበት ፍትህ አልባ በማለት በሞት ላይ ልባችን ቅይም ያለባቸውና የተማረርንባቸው ጊዜያት እንደማይጠፉም አስባለሁ፡፡
የዚህን ሞት በሰው ልጆች ላይ የጣለውን ከባድ የዘመናት ቀንበር በመስበር በኃጢአት ምክንያት በሰው ልጆች ሁሉ ላይ የነገሰውን ሞትን የረታ፣ ያሸነፈና  በሞት ላይ የሰለጠነ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ የተነሳ የሞት ኃይሉ ደከመ ሲኦልም እጅ ሰጠ፡፡ ሐዋርያት በቅዳሴያቸውም፡- «ሞትን ይሽር ዘንድ፣ የሰይጣንንም ማሰሪያ ይቆርጥ ዘንድ፣ ሲኦልንም ይረግጥ ዘንድ ቅዱሳንንም ይመራ ዘንድ ትንሣኤውንም ይገልጽ ዘንድ ለሕማም ተሰጠ ብለው እንዳመሰገኑት፡፡» ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ በቅዳሴውም እንደተናገረ፡- «በፈቃዱ ሞተ፣ ሞትን ይገድለው ዘንድ ሞተ፡፡ የሞቱትን ያድናቸው ዘንድ ሞተ፡፡ የተቀበሩትን ያስነሳቸው ዘንድ ተቀበረ፡፡ ሕያዋንንም ይጠብቃቸው ዘንድ ያደፉትን ያነጻቸው ዘንድ ኃጥአንንም ያጸድቃቸው ዘንድ የተበተኑትንም ይሰበስባቸው ዘንድ የበደሉትምን ወደ ክብር ወደ ጌትነት ይመልሳቸው ዘንድ፡፡» እንዳለ፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ሞት ሞት ለዘላለም ድል ተነሳ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡- «ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህስ ወዴት አለ? የሞት መውጊያው ኃጢአት ነው፡፡ የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፡፡ ነገር ግን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሳትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋን ይሁን፡፡» በማለት የሞትን ኃይል ለዘላለም ሰብሮ ነጻ ላወጣን አምላክ ምስጋናን፣ ክብርንና ውዳሴን ያቀርባል፡፡
        በዓለማችን ያሉ የትኛውም ሃይማኖት መስራቾች፣ መሪዎች፣ መምህራንና ነቢያቶች እስከ ዛሬ ድረስ ሞትን ድል አድርገው እንደተነሱ አልተጻፈልንም፣ አልተነገረንም፣ እኛም አልሰማንም፣ አላየንም፡፡ ግና የሞት ጉልበት ያሸነፋቸውንና የገዛቸውን እነዚህን ሰዎች ተከታዮቻቸው መቃብራቸውን አስጊጠው፣ አስውበውና ሸልመው በየዕለቱ በመዘከር ይወድሷችዋል፣ ይዘክሩአችዋልም፡፡ የእነዚህን የሃይማኖት መሪዎች፣ መምህራን፣ እና ነቢያት የሕይወት ታሪካቸው ከውልደታቸው ጀምሮ መልካምነታቸው፣ ታላቅነታቸው፣ ኃያልነታቸው፣ ገድላቸው፣ ክብራቸውና አስተምሀሮአቸው ተዘርዝሮ ሲያበቃ በስተመጨረሻ ደግሞ አይቀሬ የሆነው ሞታቸው ይነገራል፡፡ ለሞታቸው ምስክር ይሆን ዘንድም አድናቂዎቻቸውና ተከታዮቻቸው መቃብራቸውሮቻቸውን በታላቅ ክብር በማስጠበቅ ስማቸውና ታሪካቸው ከመቃብር በላይ ይቆይ ዘንድ ይተጉላቸዋል፡፡ ነጋ ጠባም መቃብራቸውን በመሳለም የመንፈሳቸውን ብርታትና ጽናት ለመካፈልም ይሞክራሉ፡፡
ወደ ክርስትና ሃይማኖት ስንመጣ ግን እውነታው ከዚህ በእጅጉ ተለየ ነው፡፡ ነቢይ፣ ካህን፣ መምህር፣ ንጉሥ፣ ጌታና አምላክ፣ የሃይማኖታችን ራስና ፈጻሚ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ  ከእነዚህ ሁሉ የሚበልጥ እጅግ ድንቅና ልዩ የሆነ ነው፡፡ ሕያው የሆነውን ጌታ ዛሬ በመቃብር ስፍራ የሚፈልገው የለም፤ መቃብሩን ለመሳለምም የሚገሰግሱ ልቦች የሉም፤ ባዶውን መቃብር የሚያስውብና የሚያስጌጥ ማንም የለም፤ ያን ባዶ መቃብር የሚያስብም ልብና መንፈስ ፈጽሞ የለም፡፡ ለምን ቢባል እርሱ ሞትን በሞቱ የሻረና በሞት ላይ የነገሰ ሕያው አምላክ በመሆኑ በሚያምኑትና በሚታዘዙት ልብ ውስጥ ሕያው ሆኖ ለዘላለም አለ፤ በእውነትና በመንፈስም እስከዘላለም ይመለካል፡፡  እናም የጌታችንን ወንጌል የጻፉልን ሐዋርያት ስለ ጌታችን ከልደቱ ጀምሮ በሞቱ ብቻ የሚቋጭ ታሪክ አልጸፉልንም፡፡ ይልቁንም በታላቅ የትንሣኤ ኃይል ሞትን ድል አድርጎ በክብር ወደ ሰማይ ሰማያት ያረገ የክብር ጌታ ደግሞም በክብር በሙታንና በሕያዋን ላይ ለመፍረድ የሚመለስ እንደሆነ እንጂ፡፡
የሕያዋን አምላክ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ መቃብር አልያዘውም፡፡ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነስቶአል፣ መቃብሩም ባዶ ነው፡፡ እርሱ በእውትም የሕያዋን አምላክ የጌቶች ጌታ፣ የነገስታት ንጉሥ እና የአማልክት ሁሉ አምላክ ነው፡፡ በጌታችን ትንሣኤ ቀን የትንሣኤያችንን በኩር ኢየሱስ ክርስቶስን በማሰብ ትንሣኤያችን ለሕይወትና ለድል እንዲሆንልን በቸርነቱና በታላቅ ጸጋው የአባቶቻችን አምላክ ይርዳን፡፡
                                                                     በፍቅር ለይኩን
                         መልካም የትንሣኤ በዓል፡፡    
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ