“በአንተ ታምናለችና በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ።” ኢሳ. 26፥3
የሚታመኑ ሰዎች በማጣት ከትዳር የዘገዩ፣ ከራእይ የቀሩ፣ ከፍቅር የጎደሉ ፣ ከሥራ ዓለም የወጡ፣ ከአገልግሎት የተፈናቀሉ፣ ከጅምራቸው የተመለሱ ሰዎች እንዳሉ እንሰማለን። ስለ መከዳታቸው ሲነግሩን ስለ መክዳታቸው ግን ነግረውን አያውቁም። አንተ እኮ ልጅ ነህ ብለው የጠዋቱን የሚያወሩን ትሞታለህና በሥርዓት ኑር ብለው ግን አያወሩንም። የሚታመን ቢገኝ ብቸኝነት ይገሠጻል፣ ሀብት ይደረጃል ፣ የአንድ አሳቢ የአንድ በሬ ሳቢ እንዲሉ አንድ ሰው ብቻውን ብዙ ነገር ማከናወን ይከብደዋል። አንድ ሰው ሁለት እጅ ቢኖረውም አንድ ነው። በአንዱ ነገር ብርቱ ቢሆን በብዙ ነገር ደካማ ነው። ታማኝ ሰው ግን በጎደለው አጥር ፣ ሙሉ ሆኖ ይቆማል። ሙሽራው ለፎቶ ብሎ ሙሽራይቷን ብድግ አድርጎ ሊያቅፋት ሲል ሱሪው ተተረተረ ፣ በጣም ደነገጠ፣ ሙሽራይት ድርቅ ብላ ቀረች፤ እርሱም የሚገባበት ጠፋው፣ በአዳራሹ ያለው ተጋባዥ የሚለው አጣ ፣ ግማሹ ሳቀ ። አንድ ሚዜ ግን ፈጠን አለና ኮቱን አወለቀ። ሙሽራውን ለመሸፈን ፈጠነ። ታማኝ ሰው ሲራቆቱ የሚሸፍን ነው።
ሰውዬው ሲራቆት የቅርብ ቢሆኑም አብረውት ደንግጠው የሚቆሙ ሰዎች አሉ። አጠገባቸው ካለው ሰው ጋር ለሐሜት የሚፈጥኑም አሉ። ለዓለም ለማሳየት ስልኩን የሚያወጣም አለ። ከዚያ መሐል አንድ ታማኝ ይገኛል። እርሱ ተራቁቶ ወዳጁን ያለብሳል። ቤተ ክርስቲያን ባሳለፈችው ታሪክ ወንድሙን የሚያጋልጥ ወንድም አልገጠማትም። እንደውም የወንድማቸውን ኃጢአት የራሳቸው አድርገው እኔ ልወቀስ ልከሰስ የሚሉ ከባቴ አበሳነትን ጉድን ሸፋኝነትን የተለማመዱ አባቶችን አፍርታለች። ስለ ራሱ ኃጢአት ኃላፊነት የሚወስድ በጠፋበት ዓለም የወንድሙን ኃጢአት የራሱ አድርጎ ወንድሙን ለንስሐ የሚያበቃ የክርስትና ታሪክ አለን። ታማኝ ሰው የወንድሙን ዕራቁትነት የሚሸፍን ነው። ዛሬ በደጉ ቀን ለክፉ ቀን ይሆነኛል ብለው የወንድማቸውን አበሳ መዝግበው የሚያስቀምጡ ምስኪኖች ሰዎች አሉ። አበሳ ያለበት በሌላው አበሳ እንዴት ፈራጅ ይሆናል?
ታማኝ ሰው ትዳሩን እስከ ሞት ድረስ በመሥዋዕትነት ያቆያል። የተደረገለትን በጎ ነገር አይረሳም። ለሰዎች ውለታ ክብር ይሰጣል። ታማኝ ሰው ያገኘ ራእዩን ያሳልጣል፤ መንገዱን ያረዝማል። በዓለም ላይ ሕዝብ በሌለበት ንጉሥ የለም። ተመልካች ባይኖርም ሯጭ አይኖርም ነበር ። አጋዥ ከተገኘ ሥራ ይቀላል። አብሮ የሚበላ ሰው ካለ ምግብ ይሠራል፤ ይበላል። አብሮ የሚጓዝ ከተገኘ መንገድ አያደክምም።
የሚታመኑበት፣ ልብ የሚጥሉበት ፣ ለአደራ የሚበቃ፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እየጠፋ ነው። ሰው ቢታጣ እግዚአብሔር አለ። በእግዚአብሔር መታመን የሰላም መሠረት ነው። በቁማቸው ጨርሰው ስሞት ልጆቼ ምን ይሆናሉ ? ብለው የሚጨነቁ ሰዎች አሉ። በእግዚአብሔር የታመኑ ግን ልጆቼ በእኔ በኩል ቢመጡም የእኔ አይደሉም ብለው ያርፋሉ። መጀመር የሚፈሩ እግዚአብሔር ያስፈጽመኛል ብለው ታምነው ይነሣሉ ። ሰው በሌለበት ማገልገል ከባድ ነው፣ ሕዝቡ አይሰማም ብለው የሚፈሩ በእግዚአብሔር ታምነው የቃሉን ዘር ይዘራሉ።
በእግዚአብሔር የሚደገፉ አይናወጡም። ወንበር ላይ ስንቀመጥ፣ ምሰሶ ስንደገፍ አይጥለንም ብለን ታመነን ነው። እግዚአብሔርን የወንበርና የምሰሶ ያህል መታመን ብዙ ጊዜ ያቅተናል። አይጥለኝም አይተወኝም ብሎ በእግዚአብሔር መተማመን የልብን ሰላም ይጠብቃል። እርሱን መደገፍም ማዕበላዊ ቀኖችን ያሻግራል።
ውድ ወዳጆች ሰላም የመታመን ውጤት ነው! በእግዚአብሔር የታመኑ ልባቸው በማዕበል ከመናወጥ ይድናል። ሰው የሦስት ነገሮች ውቅር ነው። የትላንት፣ የዛሬ፣ የነገ ። በእግዚአብሔር መታመን ትላንትን ይክሳል፣ ዛሬን ያሠራል፣ ነገን ያስውባል።
ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 15 ቀን 2017 ዓ.ም.