የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መንገድ አለው/ ክፍል ሦስት

እሑድ ሐምሌ ፲፪/ ፳፻፯ ዓ/ም

 

“ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ” (ኢሳ. 43÷ 1)፡፡
                   
እግዚአብሔር የፍርሃት መድኃኒት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከፍርሃት ያድናል፡፡ የብዙ ሰዎች ውስጣዊ ስቃይ ፍርሃት ነው፡፡ ባለጠጎችና ድሆች፣ ትልልቆችና ትንንሾች የሚባሉ ሁሉ በፍርሃት ይናጣሉ፡፡ የፍርሃት ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ሁሉም ሰው ፍርሃት አለበት፡፡ ፍርሃት ገና በድምፁ የሚያስፈራቸው ወገኖች ብዙ ናቸው፡፡ ምንም የሚያስፈራ ነገር ሳይመጣባቸው ራሱ ፍርሃት እንደ ደራሽ ውሃ የተጠጋቸው ብዙ ወገኖች አሉ፡፡ ውጫዊውን አስፈሪ ድል ለመንሣት አጥር ያጠሩ፣ የጦር መሣሪያ የታጠቁ፣ ዘብ ያቆሙ ወገኖች በውስጣቸው የገባውን ስጋት ግን ድል መንሣት አልቻሉም፡፡ የሰው ልጅ ራሱ የራሱ ሲሆን የራሱም ጠባቂ ራሱ ሲሆን ፍርሃት ይገዛዋል፡፡ የእግዚአብሔር ሲሆን በልዑልም መጠጊያ ሲኖር ግን በእምነት ድፍረት ይመላለሳል፡፡ ቃሉ፡- “ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ”  ይላል (ኢሳ. 43÷ 1)፡፡
 
ፍርሃት የተለያዩ ምንጮች ቢኖሩትም የፍርሃት ዋነኛ ምንጩ የመጀመሪያው ሰው ራሱን ሲያይ የሚገጥመው ሲሆን ሁለተኛው የፍርሃት ምንጭ ደግሞ አካባቢውን በማየት የሚገጥመው ነው፡፡
 
1.       ራስን ማየት
 
በአንድ ወቅት የጌታ ደቀ መዛሙርት በታንኳ ሲጓዙ ታንኳይቱን የሚያዳፍን ማዕበል ገጠማቸው፡፡ ብርቱ ጥረት ቢያደርጉም ማለት ሸክም ቢያቀሉ፣ አቅጣጫ ቢለውጡ የማይቆም ማዕበል ነበር፡፡ ሌላ አማራጭ ለመፈለግም የማሰብ እንኳ ዕድል አላገኙም፡፡ ልብ አድርጉ! ታንኳይቱ እንዲህ የምትናወጠው ጌታ በውስጧ ሳለ ነው፡፡ ማዕበል ጌታ ከእኛ የመለየቱ ምልክት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ምን እንደምናደርግ ለማየት በማዕበል ሰዓት ዝም ይለናል፡፡ ግን አብሮን ነው፡፡

ጌታችን ማዕበሉ እየበረታ ሲሄድ በታንኳይቱ ውስጥ ተኝቷል፡፡ በታንኳ ውስጥ እንኳን በማዕበል ሰዓት በፀጥታው ሰዓትም መተኛት ይከብዳል፡፡ ክርስቶስ ግን ሰማያዊውን ሰላም እያሳየን ነበር፡፡ የአማኝ ሰላም ውጪው እየተናወጠ በውስጥ የሚሰማን የልብ ዕረፍት ነው፡፡ ጴጥሮስ ነገ የሞት ፍርድ ሊፈረድበት ሌሊቱን በሰንሰለትና በእግረ ሙቅ ተጠፍሮ ሰላማዊ እንቅልፍ ተኝቶ ነበር (የሐዋ. 12÷6)፡፡ የእምነት ሰው በሁከት ውስጥ ይተኛል፣ የማያምን ግን በሰላም ቦታም መተኛት ያቅተዋል፡፡ የእምነት ተቃራኒ ምንድነው? ስንል ፍርሃት፣ ጭንቀት ብለን መጥቀስ እንችላለን፡፡ 

 
ደቀ መዛሙርቱ ራሳቸውን ባዩ ጊዜ ከዚህ በላይ ማድረግ ስለማይችሉ በፍርሃት ራዱ፡፡ የሞት ሞታቸውን “ጌታ ሆይ አድነን ጠፋን” እያሉ ቀሰቀሱት፡፡ ጌታ ግን ማዕበሉን ከመገሰጹ በፊት የደቀ መዛሙርቱን ፍርሃት ገሰጸ፡፡ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ ስለምን ትፈራላችሁ?” አላቸው (ማቴ. 8÷26)፡፡ በዚህ ሰዓት እንደ ሰውነታቸው መፍራት ይገባቸዋል፡፡ ነገር ግን ጌታ ሳለ ጥፋት አያገኘንም ብለው ማመን ነበረባቸው፡፡ ከውጫዊ ማዕበል ይልቅ የውስጥ ፍርሃት መገሰጽ አለበት፡፡ ፍርሃት ካልተገሰጸ ማዕበል ቢቆምም መጨነቅ አይቀርም፡፡ ከማዕበል ይልቅ ፍርሃት አደጋ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታ አለማመናቸውን ገሰጸ፡፡
 
እግዚአብሔርን የለካነው በሰው አቅም ነው፡፡ ማመናችን ያስፈለገን ግን ሰው በማይችለው ነገር ላይ ጉልበት ለማግኘት ነው፡፡ እኛ የማንችለው ነገር ከገጠመን እንፈራለን፣ ሐኪም ከአቅም በላይ ነው ካለን ከእግዚአብሔር አቅም በላይ የሆነ ጉዳይ የገጠመን ይመስለናል፡፡ በእውነት አምላካችንን አሳንሰነዋል፡፡ እግዚአብሔር ከመረዳታችን በላይ ታላቅ ነው፡፡ የፍርሃት አንዱ መነሻ ራሳችንን ማየታችን ነው፡፡ አቅማችንን፣ ችሎታችንን ማየት፣ እግዚአብሔርን ግን አለማየት የፍርሃት መነሻ ነው፡፡ እምነት ግን ከተፈጥሮና ከሰው ችሎታ በላይ ይጓደዳል፡፡   
2.       አካባቢውን ማየት
 
ጴጥሮስን ሁላችንም የምናውቀው በችኩልነቱ ነው፡፡ ችኩልነቱ በአንድ ምዕራፍ ያስመሰገነውና ያስነቀፈው ሐዋርያ ነው (ማቴ. 16÷17,23)፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳ ተሳፍረው ወደ ማዶ ለመሻገር ጉዞ ጀመሩ፡፡ ሰዓቱ የጨላለመ ነበር፣ በዚያውም ላይ ማዕበል ያስጨንቃቸው ጀመረ፡፡ ጌታ አብሮአቸው አልነበረም፡፡ ከሌሊቱ በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕር እየተራመደ ሲመጣ ምትሐት መስሏቸው በጣም ተጨነቁ፣ በፍርሃትም ጮኹ፡፡ ኢየሱስ ግን እኔ ነኝ ብሎ አረጋጋቸው፡፡ ጌታ ባሕር እየተራመደ መምጣቱ የደነቀው ጴጥሮስ ጌታ ሆይ አንተ ከሆንህ እንድመጣ እዘዝ አለው፡፡ ጴጥሮስም ከታንኳዋ ወርዶ ባሕር ፀንታለት፣ ከተፈጥሮ ሕግ በላይ የመሬት ስበት ሳያግደው በባሕር ላይ እየተራመደ መጓዝ ጀመረ፡፡ ጴጥሮስ የጠራውን ኢየሱስን ባየ ጊዜ ሁሉ የማይቻለው ተችሎለት ተጓዘ፡፡ ጴጥሮስ ግን ሦስት ነገሮች ወደ ኅሊናው መጡ፡-  መስጠም ብጀምር የምድንበት መርከብ ርቃለች አለ፣ ዓይኑም ጨለማውን ማየት ጀመረ፣ በዚህ ጊዜ ጥርጣሬ ወደ ውስጡ ገባ፡፡ ልቡም በፍርሃት እየተናጠ ሲመጣ መስጠም ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታ ሆይ¦ አድነኝ ብሎ ሲጮህ ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ አዳነው ( ማቴ. 14÷22-33)፡፡ ጴጥሮስ ጥርጣሬው ቢያስነቅፈውም ሰጥሞ ሳያልቅ አድነኝ ብሎ መጮኹ ያስመሰግነዋል፡፡
 
ከፊት ለፊታችን የጠራንን ጌታ ካላየን፣ የረገጥነው እንደ ባሕር ያለችውን ዓለም፣ የምናየውም ጨለማ፣ የምናደምጠውም የጥፋት ማዕበልን ነው፡፡ እኛን ሊረዱ የሚችሉ ቀዛፊዎች /አገልጋዮች/ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ከእኛ ርቀው ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ የጠራንን ጌታ እያየን የጥሪውን ድምፅ ‹‹አልለቃችሁም›› ብሎ ያሰማንን የተስፋ ቃል እያሰብን ወደፊት ልንገሰግስ ይገባል፡፡ አስተማማኝ የኑሮ መሠረት የለኝም፣ ሥራዬ ኮንትራት ነው፣ የመኖሪያ ፈቃዴ አልታደሰም፣ የትዳሬ ነገር ገና አልተወሰነም … የምንል ከሆነ ጴጥሮስ የረገጠውን ባሕር እናስብ፡፡ ጌታ ባሕርን መረማመጃ ያደርጋታል፡፡ ምንም ተስፋ ሰጪ ነገር አይታኝም ባልንጀሮቼ ሁሉ አሁን አጠገቤ የሉም፣ የሚያውቁኝ ሁሉ አልቀዋል፣ ከዚህ በኋላ ሰው ማልመድ ሰልችቶኛል፣ ልጆቼ የሚያድጉበት የተሻለ ስፍራ አይታየኝም፤ ትዳሬም ጥቅም ሊበትነው ይችላል የምንል ከሆነ ጴጥሮስ በጨለማ ውስጥ መጓዙን አስቡ፡፡ የሚወራው ሁሉ መልካም አይደለም፣ ሰውን ሁሉ እንድንፈራ አድርጎኛል፣ ብቸኝነት ሳይሻል አይቀርም፣ ያስጠጉት ገደለ እየተባለ ከማን ጋር ይኖራል፣ ወንጀሉ በርክቷል፣ ሰው አውሬ ሆኗል የሚል ፍርሃት ይዘን ከሆነ በማዕበል ውስጥ የተራመደውን ጴጥሮስን አስቡ፡፡ ኢየሱስን፣ የጠራንን ጌታ ካየን ባሕሩም፣ ጨለማውም፣ ነፋሱም፣ ከእኛ የራቀው መርከቡና ባልንጀሮቻችን ስጋት አይሆኑንም፡፡ የጠራን ጌታ ከዚህ ሁሉ በላይ ነው! እርሱ ባሕር ተራምዶ ሊረዳን ይመጣል፡፡ እርሱ ሲመጣ ጨለማው በብርሃን፣ ነውጥ በሰላም ይለወጣል፡፡
 
ጴጥሮስ ጨለማውንና ነፋሱን ባሰበ ጊዜ በልቡ ምን አቀበጠኝ፣ አርፌ ብቀመጥስ ሳይል አይቀርም፡፡ ፍርሃቱ ጥርጣሬን፣ ጥርጣሬው መስጠምን አስከተለበት፡፡ ጴጥሮስ የፈራው አካባቢውን ባየ ጊዜ ነው፡፡ ጌታን ካላየን ዙሪያችን ጨለማና ማዕበል ነው፡፡ ጌታን ካየን ግን እነዚህ ተገዳዳሪዎች እያሉም መጓዝ እንችላለን፡፡ አዎ የፍርሃት ምንጩ ራስንና አካባቢን ማየት ነው፡፡ ራሳችን ለራሳችን ዋስትና መስጠት እንፈልጋለን፡፡ አካባቢውም ዋስትና ካልሰጠን መኖርን እንሰጋለን፡፡ ወገኖቼ! የተቤዠን እርሱ ዋስትናችን ነውና አሳባችንን ሰማያዊ እናድርግ፡፡
 
ቃሉ፡- “ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ” (ኢሳ. 43÷1) ይለናል፡፡ መቤዠት አንድን ሰው ወይም ዕቃ በተሸጠበት ዋጋ መልሶ በመግዛት የራስ ንብረት ማድረግ ነው፡፡ መቤዠት ከተራ ግዢ ይለያል፡፡ የመቤዠትን ዋጋ የሚከፍልም የቅርብ ዘመድ ነው (ዘሌዋ.25÷25)፡፡ ለምሳሌ፡- መሬት ለእያንዳንዱ እስራኤላዊ የተሰጠ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ ስለዚህ መሬትን መሸጥ መለወጥ አይቻልም ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ስጦታ አይሸጥምና፡፡ ታዲያ እስራኤላዊው ድህነት ፀንቶበት፣ ችግር አይሎበት መሬቱን ቢሸጥ የቅርብ ዘመዶቹ የሽያጩን ሙሉ ዋጋ በመክፈል ያስመልሱለት ነበር፡፡ ይህ መቤዠት ይባላል፡፡ እግዚአብሔር በጸጋ አክብሮ በመልኩ አስውቦ ፈጥሮን ነበር፡፡ ነገር ግን የፍቅር፣ የማስተዋል ድህነት ወድቆብን ሀብታችንን ሸጥን፡፡ አዳምና ሔዋን በነፍስ በሥጋ ስደተኞች ሆኑ፡፡ ኢየሱስ ዘመዳችን ሆኗልና የተወሰደብንን የማስመለስ የዘመድ ዕዳ ወደቀበት፡፡ ስለዚህ ነፍሱን አስይዞ ሕይወትንና ጸጋን መለሰልን፡፡ የተቤዠን በብርና በወርቅ ሳይሆን በገዛ ደሙ ነው፡፡ ስለዚህ፡- “ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ” አለን፡፡
 
አንድ ንብረት፡- ሠሪ፣ ሻጭና ገዢ አለው፡፡ ሠሪው ያውቀዋል፣ ገዢው ይፈልገዋል፡፡ አምላካችንም የሚሸጠን ሳይሆን የሠራንና የገዛን ነው፡፡ ያውቀናል፣ ይፈልገናል፡፡ አንድ ንብረትን አስቡ፡- ለምሳሌ፡- ቤት የገዛው ሰው ለቤቱ ጥበቃ ያቆማል፡፡ ገዝቶታልና በልዩ ይጠብቀዋል፡፡ የገዛ አይጥልምና፡፡ ጌታችን ገዝቶናል፡፡ የገዛን ሊጥለን አይደለምና ደስ ይበላችሁ!! የፍርሃት ምንጩ ለራስ ዘብ መሆን ነው፡፡ እኛ ግን ራሳችንን የምንጠብቅ ሳይሆን የገዛን የሚጠብቀን ዋስትና ያውም አምላካዊ ከለላ ያለን ሕዝቦች ነንና ፍርሃት ዛሬ በስሙ ይረገጥ፣ መንገድ አለው በርቱ! ካላችሁበት ነገር እንዴት እንደምትወጡ ሳይሆን ማን እንደሚያወጣችሁ እወቁ!
                           -ይቀጥላል-     
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ