የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መንገድ አለው

መስከረም 8

“እግዚአብሔር በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው ፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው ።”

(ናሆም 1፥3)

እግዚአብሔር ከእስራኤል ውጭ ላሉት ሕዝቦችም ዓላማ አለው ። የቀደመ አሳቡ እስራኤልን አሳምኖ በእስራኤል ሌላውን ዓለም ማሳመን ነው ። ነቢዩ ዮናስና ነቢዩ ናሆም የነነዌ ሸክም የነበራቸው ፣ ለአሕዛብ የተላኩ ነቢያት ናቸው ። የነነዌ ሰዎች ከ825-785 ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በነበረው በዮናስ አገልግሎት ከሊቅ እስከ ደቂቅ ንስሐ ገብተው ነበር ። ለንስሐ የሰጡት ፈጣን ምላሽ፣ ከንጉሡ እስከ ሎሌ በአንድ ልብ መመለሳቸው፣ ብሔራዊ ንስሐን ማድረጋቸው ፣ በእግዚአብሔር ምሕረት መዳናቸው የዘመናት ትንግርት ሆኖ ይኖራል። ጾመ ነነዌ እያልንም በዓመት ሦስት ቀን እንጾማለን ። ነቢዩ ናሆም የተነሣው ዮናስ ከተነሣ ከ150 ዓመት በኋላ ነው ። እግዚአብሔር አምላክ ለነነዌ ዮናስን ነቢይ አድርጎ ላከ ፣ አሁን ደግሞ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያና ትንቢትን በናሆም በኩል ላከላት ። ነነዌ በንስሐዋ አልጸናችም። ወደ ትፋትዋ ተመልሳለች ። ትልቁ በደልዋ የደም ከተማ መሆንዋ ነው ። የውድቀት ዘመን እየመጣባት መሆኑን፣ የሚያስጠነቅቅ መልእክት ተላከላት ። ስላልሰማችም ጠፍታለች ።

በነነዌ ብዙ መወዛገብ ነበረ ። ከከተማ ከተማ ለመንቀሳቀስ የደኅንነት ዋስትና አልተገኘም ። ሰው ሁሉ የገዛ ወገኑን ፈርቶ ነበር ። በማን እጅ እንደሚሞት እንኳ እርግጠኛ አልነበረም ። ፍርሃት ከተማይቱን ያዋራት ነበር ። ሁሉም ሰው ስለ መሸሻ ያስባል ፣ ወዴት እንደሚሸሸ ግን አያውቀውም ። ነነዌ የኃጢአት ግርሻት ያሰቃያት ፣ በነቢዩ በዮናስ ዘመን ከነበረው ስህተትዋ የኋላ ድካሟ ያናውጣት ጀመር ። የሰው ዋጋ የወደቀባት ፣ አራዊት በሁለት እግር ቆመው የሚሄዱባት አገር ሆና ነበር ። ይህ ቀን እንዴት ያልፍ ይሆን ? የሚሉ ተሳቃቂዎችም በውስጥዋ ነበሩ ። በንስሐ የእግዚአብሔርን ምሕረት ከፈለጉ እግዚአብሔር መንገድ እንዳለው ተስፋ ተሰጥቷቸዋል ።

“እግዚአብሔር በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው ፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው።” ወጀብና ዐውሎ ነፋስ መንገድ የሚዘጉ ፣ አላሳልፍ ብለው የሚያስጨንቁ ናቸው ። ወጅብ ሲነሣ መርከቡ መናወጥ ይጀምራል ። ተሳፋሪውም ብዙ ብርና ወርቅ ቢይዝም በባሕር ላይ ካለ ባለጠግነት ምድር ላይ ያለ ድህነት ይሻላል ይላል ። ቢያንስ ሕይወቱን ያተርፋልና ። ወጀቡና ነፋሱ የተወሰነውን የመርከብ አካል ሳይሆን ሁሉንም ያናውጣል ። ወዮለት ለካፒቴኑ ብሎ ተስፋሪው አይመጻደቅም ። ሁሉንም ይዞ የሚሄድ የሞት ሠረገላ ሊሆን ይችላል ። በአገር ላይ የሚመጣ ነውጥም ለይቶ የሚጐዳ ሳይሆን ሁሉን የሚያደማ ነው ። ለወጀቡ አቅጣጫ መቀየር እንደ መፍትሔ ይወሰዳል ። መንግሥታት የፖሊሲና የፖለቲካ ፣ የኢኮኖሚ ማሻሻል በማድረጋቸውም የማይቆም ወጀብ ሊነሣ ይችላል ። አንዳንድ ወጀብ በንስሐ ብቻ ፀጥ የሚል ነው ።

ጊዜ በማይሰጠው ፣ ሕይወትንም ንብረትንም ሊነጥቅ በመጣ ወጀብ ፣ በሚያናውጥ የሽብር ዜና ውስጥ እግዚአብሔር መንገድ አለው ። ወጀብና ነፋሱን ገሥጾ መንገድ ይሰጣል ። ሌላ ጊዜ ወጀብና ነፋሱ እያለም መንገድ ይሰጣል ።

ምን አልባት የተፋነውን በመላሳችን ወጀብና ነፋስ መጥቶብን ይሆናል። እግዚአብሔር የያዘልን መከራና ፈተና ከእርሱ ስንርቅ እላያችን ላይ ወርዶብን ይሆናል። እግዚአብሔር በቃልም በጽሑፍም መልእክት ይልካል ። ለነነዌ ነቢዩ ዮናስና ናሆም ተልከዋልና ። እኛስ አላሳልፍ ያለን ወደፊት መራመድ ፣ ባሻገር መመልከት የከለከለን ፣ ተስፋና ጉልበት ያሳጣን ምን ይሆን ? በምታነክስ አገር ላይ መኖራችን ይሆን ? ዕለት ዕለት የሰዎች መጨካከን ፣ ፈውስ ያጣንለት በሽታችን ፣ የልጆቻችን አጉል ምርጫ እንዴት እናልፈዋለን እያሰኘን ይሆን ? ፍርድ ከሚወጣባት ከጽዮን ቤተ ክርስቲያን ፍርድ ማጣታችን ደጃፉን ግድግዳ አድርጎብን ይሆን? መምህራን በሐሰት፣ ዳኞች በጉቦ በመታወራቸው መድረሻ ጠፍቶን ይሆን?

በንስሐ በጌታ ፊት እንውደቅ እርሱ መንገድ አለው ። አይዟችሁ የከበደን አይከብደውምና በእግዚአብሔር አሳላፊነት ደስ ይበለን !

ዕለተ ብርሃን 7

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ