የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ….. ሐሙስ የካቲት 20/ 2006 ዓ/ም
አንድ ታዋቂ የሐዲሳት መምህር ለማስተማር በተጋበዙበት ደብር ፕሮግራም መሪው ሲያስተዋውቅ፡- “እኒህ መምህር ዓይነ ሥውርነት ሳከለክላቸው ይህን ሁሉ ዕውቀት ያተረፉ በመሆናቸው በእውነቱ ይደነቃሉ፡፡…..” እያለ ለማወዳደስ ፈለገ፡፡ እርሳቸውም ለስብከት ሲነሡ፡- “ይህ ወንድሜ ስለ ዓይነ ሥውርነቴ ተናግሯል፣ ነገር ግን አምፖል ተቃጠለ ማለት መብራት ሄደ ማለት አይደለም” በማለት ተናገሩ፡፡ ዓይን አምፖል ነው፣ መብራቱ ግን አእምሮ ነው፡፡ አምፖል በራሱ ብርሃን የለውም፣ ዓይንም የሕይወትን ምሥጢር ሊያይ አይችልም፡፡ አምፖል ውበት ቢኖረውም ያለ ኃይል አይሠራም፡፡ ትልልቅ ዓይኖችም ያለ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር የሚያየውን ሊያዩ አይችሉም፡፡ ብዙ ሰዎች በዓይናቸው ደጋግመው አይተውን ሊያልፉን ሲሉ “ምነው” ስንላቸው “አላየሁህም፣ ልብ ነው የሚያየው” ይላሉ፡፡ ትልቁ ዓይን ውሳጣዊ ነው፡፡ የውስጡ ዓይን ካላየ የላዩ አያይም፡፡ ለዚህ ዓለም ጉዞ፣ ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር ላለን መልካም ግንኙነት የሚያስፈልገን የሥጋ ዓይን ሳይሆን የልብ ብርሃን ነው፡፡ አህያ ትልልቅ ዓይኖች አሏት፣ ርቀት ግን ማየት አትችልም፡፡ ቆንጆ ዓይን ይዞ ራእይ ማጣትም እንደዚሁ ነው፡፡ አዎ አምፖል ተቃጠለ ማለት መብራት ሄደ ማለት አይደለም ያሉት እውነት ነው፡፡ ይህን ምሥጢር ሊናገር የሚችልም የልብ ብርሃን ነው፡፡
ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፡- “እግዚአብሔር በአጉሊ መነጽር አይታይም፣ በተወለወለ ልብ ግን ይታያል” ብለዋል፡፡ ከፊት ለፊታቸው ህርቅን ጠልተው ምግብ ለማቅረብ የጸዳ ሳሕን ያቀረቡ፣ በትምህርታቸው የሚኮሩ ባለመነጽሮች አሳዝነዋቸው ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት በውጫዊ ሳይሆን በውስጣዊ ነገር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የቀደሙት አባቶችም፡- “አቤቱ የልቡና ዓይኖችን ስጠን፣ ዘወትር አንተን ያዩ ዘንድ” ብለዋል፡፡ እግዚአብሔር የሚታየው በልብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እርሱንም ዘወትር ማየት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ዓይነ ሥውርነት ትንሽ ጉዳት ነው፤ ብዙ ዓይነ ሥውራን ታላላቅ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በመንፈሳዊ ቅኔና ዝማሬ አንቆጥቁጠዋታል፡፡ በመላው ዓለም እነዚህ የዝማሬ ማዕበሎች ዛሬም ድረስ የደነዘዘውን የሰው መንፈስ ያነቃሉ፡፡ የልብ ዕውራን ግን ምሬት እንጂ ምስጋና የላቸውም፡፡ ዓይነ ሥውርነት የሰውዬው ምርጫ አይደለም፣ ስለዚህ ኃጢአት ሆኖ አያስጠይቀውም፡፡ የልብ ጨለማ ግን ለክርስቶስ መንግሥት ለመገዛት ባለመፍቀድ የሚመጣ በመሆኑ ኃጢአት ነው፡፡
ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ዓይነ ሥውራንን በተአምራት ሲፈውስ የልብ ዕውራንን ግን በትምህርቱ ፈውሷል፡፡ የልብ ዕውርነት በተአምራት ሳይሆን በትምህርት የሚለቅ ነው፡፡ ለሚያስተውል ሰው ቋሚ ተአምር ትምህርት ነው፡፡ ጌታችንን በዘመኑ ሁሉ የተቃወሙት ኋላም ለሞት ያበቁት የሥጋ ዓይን ያጡ ሳይሆኑ የልብ ጨለማ የሰፈነባቸው ነበሩ፡፡ እርሱ ለሥጋ ዕውራን አዝኖላቸዋል፡፡ ለመማር ባልፈቀዱ የልብ ዕውራን ግን አዝኖባቸዋል፡፡ ዛሬም ብዙ ውሳጣዊ ጨለማ እየሰፈነ ይመስላል፡፡ መንፈሳዊ ግርዶሽ ብዙዎችን እየተቆጣጠረ ነው፡፡
ዘመናችን ሁሉም ነገር ትክክል ነው ወደሚል አዙሪት ውስጥ እየገባ ነው፡፡ የዚህ ውጤት ግን ልክ የሆነ ምንም ነገር የለም ወደሚል መደዴነት የሚያደርስ ነው፡፡ የዓለም አብያተ ክርስቲያናትም የዓለሙን ጩኸት እንደ ገደል ማሚቱ ከማስተጋባት ውጭ የመዳንን ድምፅ ማሰማት አልቻሉም፡፡ በእውነቱና በሐሰቱ መካከል ድንበር እስኪጠፋ መቀላቀል ይታያል፡፡ ይህም ብዙ መንፈሳዊ ግርዶሽ አስከትሏል፡፡ መንፈሳዊ ግርዶሻችን/ጨለማችን/ ምንድነው? ለጊዜው አራቱን እንመልከት፡-
1. ለአፈኞች የሰጠነው ክብረት፡-
ዓለም መሥራት የቻሉ ሳይሆን ማውራት የቻሉ መድረክ እየሆነች ነው፡፡ አንድ ታላቅ አባት የዶሮ ወረርሽኝ ከላቲን አሜሪካ በተነሣ ሰሞን ላይ ተገናኘን፡፡ ወዲያው መድኃኒቱ ተገኝቶ የስጋቱ ወሬ ፀጥ አለ፣ በዚያ ሰሞን ደግሞ የእንግሊዝ እግር ኳስ ወሬ በጣም ደርቶ ነበር፡፡ ታዲያ እኚህ አባት፡- “ዓለም ከጭንቅላት እግርን እያከበረ ነው ” አሉኝ፡፡ እንዴት ብላቸው፡- “የበሽታ መድኃኒት ያገኙ ሰዎች ስማቸው እንኳ አይጠራም፣ የኳስ ተጫዋች ደሞዝ ግን ቀኑን ሙሉ ሲወራ ይውላል፤ ኳስም ከእግዚአብሔር በላይ ተከታይ አግኝቷል ” በማለት በሀዘን አጫወቱኝ፡፡ ይህ በእውነት የዓለም መገለጫዋ ነው፡፡ በአሜሪካ አገር አንድ በቀልድ የሚያዝናና ቀልደኛ በወር ከዐሥር ሺህ ዶላር በላይ ሊያገኝ ይችላል፣ አንድ ሰባኪ ግን አንድ ሺህ ዶላር ቢሰጠው ከብዙ ማጉረምረም ጋር ነው፡፡ ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚቆረቆሩ ሰዎች ይህን ያህል ገንዘብ ተመዘበረ እያሉ ያነባሉ፣ ስንት ነፍስ እንደ ጠፋ ግን ማሰብ እንኳ አይፈልጉም፡፡ ለከበረው ነገር የሰጠነው ዋጋ በጣም ትንሽ እስከ ሆነ ድረስ ጭንቃታችን ይቀጥላል፡፡
ብዙ አፈኞች ራሳቸውን እንዲህ ነኝ ብለው መዐርጋቸውን ሲናገሩ የሰማው ሁሉ “ናቸው” እያለ ይናገራል፡፡ ራሳቸውን ሾመው፣ ለራሳቸው ባወጡት መዐርግ የሚጠሩ አያሌ ናቸው፡፡ ደጃዝማች እገሌ እያልሁ ሳወራ አጎቴ፡- “ቆይ እነግርሃለሁ ዝም” አለኝ፡፡ “ምንድነው?” አልኩት፡- “እርሳቸው ሲሾሙ ነበርኩ” አለኝ፡፡ ታሪኩን ሲነግረኝ፡- “አንድ ምሽት እገሌ የሚባል ሆቴል ከበር መልስ ጋበዙንና ከዛሬ ጀምሮ ደጃዝማች ነኝ አሉ፣ ደጃዝማች ሆኑ” አለኝ፡፡ በመቀጠልም፡- “አንተ የእኔ ሰው ስትሳሳት መስማት ስለማልፈልግ ነው” አለኝ፡፡ እንዲህ ያለ ሹመት እንደሚሰጥና እንደበዛም ከዚያ በኋላ አወቅሁ፡፡ “ነኝ” ካሉ “ነህ” የሚባልበት ዘመን ላይ ነን፡፡ በዚያው ልክ ክርስቲያን ነኝ፣ አባት ነኝ እያሉ ብዙ ጥፋት የሚሠሩ አያሌ ናቸው፡፡ አንድ የቤተ ክርስቲያን ትልቅ መዐርግ የተሸከሙ አባት በሐሰት ክስ ስለማውገዛቸው ሲናገሩ፡- “በማይገባን ቦታ ስለተቀመጥን የማይገባ ሥራ እየሠራን ነው” ብለዋል፡፡ አዎ ዛሬ ያለው ግርዶሽ ለእውነተኞች ሳይሆን ለአፈኞች የሰጠነው ክብር ነው፡፡ በውጭ አገር በሰዓት ስንት ያገኛል እንጂ ምን ይሠራል? እንደማይባል ዛሬም ምን ያወራል እንጂ ምን ይተገብራል? ማለት እየቀረ ይመስላል፡፡ እግዚአብሔር ግን የአፍ ወዳጆችን ይጠላል፡፡
2. አፍቃሪዎች እንደ ሞኝ መቆጠራቸው፡-
ብዙ ሰዎች ጠላቶቻቸውን ለመውደድ ይጥራሉ፣ ግን አይሳካላቸውም፡፡ ጠላትን የመውደድ መነሻው ግን ወዳጅን መውደድ ነው፡፡ የሚጠሉን ስላሉ ከምናዝን የሚወዱንን እያሰብን እግዚአብሔርን ብናመሰግን የተሻለ ነው፡፡ የሚወዱን የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው፡፡ ካልተገነዘብን ሊወሰዱብን ይችላሉ፡፡ የሚጠሉንን ከማሳደድ የሚወዱንን ማክበር የተሻለ ነው፡፡ በክፉዎች ክፋት እያዘንን የመልካሞችን መልካምነት ግን የምንጠራጠር ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ በዛሬም ዘመን ብዙ እውነተኛ አፍቃሪዎች አሉ፡፡ በደምሳሳው እንደምንናገረው የፍቅር ሰው ያለቀበት ዘመን አይደለም፡፡ ዓለም ሁሉ በድሎ አንድ ኖህ በተገኘ ጊዜ እግዚአብሔር የእኔ ሰው ሲለው አላፈረበትም፡፡ ዛሬም አንድ ሰው ካለ እንደ እርሾ ይሆናል፡፡ መንፈሳዊ ግርዶሽን ካመጣው ነገር አንዱ አፍቃሪዎች እንደ ሞኝ መቆጠራቸው ነው፡፡ የዚህች ዓለም ዕድሜ እንዲቀጥል የፍቅር ሰዎች ያላቸው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡
3. ገንዘብ ጌታ እንዲሆን መፍቀዳችን፡-
ከዜና ጀምሮ እስከ መንደሩ የሚነገረው የሚሊየን ብር ዘገባ ነው፡፡ ስለ ትውልዱ ህንፀት፣ ስለ አገር ፍቅር፣ ስለ አንድነት… ካልታወጀ ገዢው ገንዘብ ይሆናል፡፡ ቅንነት የሚመራው እንጂ ገንዘብ የሚመራው አገርም ቤተሰብም ፍጻሜው ያማረ አይደለም፡፡ ገንዘብ አስፈላጊ ነው፣ አስፈላጊውን ነገር በተገቢው መንገድ ማግኘትም ኃጢአት አይደለም፡፡ ገንዘብ ሕይወት ተደርጎ ከታሰበ ግን ሰው ከራሱ በላይ ያየዋል፡፡ ብዙዎች ገንዘብ ለማግኘት ጤናቸውን ያጣሉ፣ በኃጢአት ይጨማለቃሉ፣ ሌላውን ወገን ይገድላሉ፡፡ ገንዘብ ትክክለኛ ቦታውን ካልያዘ የሁከት መነሻ ይሆናል፡፡ በንጉሡ ጊዜ ሺህ ሩቅ ስለነበር የሰው ስም እንኳ “የሺ” ሚል ነበር፡፡ በደርጉ ሚሊዮን ሩቅ ስለ ነበር “ሚሊዮን” የሚል ስም ይወጣ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ሚሊዮን ሁሉም ሰው በመንገድ ላይ ቆሞ፣ ድንጋይ ላይ ተቀምጦ የሚያወራው ነው፡፡ ወሬው በጣም ከመድራቱ የተነሣ ሚሊዮን ብር ያለን ይመስለናል፡፡ ጨዋታው ከመድመቁ የተነሣም በዚህ ወር ሥራ የጀመረ ሠራተኛም ሚሊዮን ብር ማግኘት እንዳለበት ያስባል፡፡ ኑሮን ያዛባ ነገር እየተከሰተ ያለው፣ ሌብነትን ባሕል እያደረገ የመጣው የገንዘብ አምልኮት ነው፡፡ በገንዘብ የታወረ ሰው ምንም ወንጀል ከመፈጸም ወደ ኋላ አይልም፡፡ “ገንዘብ ለሚያዘው ታማኝ ሎሌ፣ ለሚገዛለት ክፉ ጌታ ነው፡፡”
4. የተሰቀለውን ጌታ አለማየት፡-
የተሰቀለ ነገር ከፍ ብሎ የሚታይ፣ የሰው ቁመት የማይደርስበት፣ ከቦታው ሲነሣ የት ሄደ? የሚባል፣ ሁሉ የሚያየው፣ የማይደበቅ፣ ሹመት ሽልማት የሆነ፣ የዓይን ማረፊያ፣ የፍቅር መልእክት ማስተላለፊያ፣ የልብ አዳሽ፣ የአእምሮ ፋና፣ የፍቅር ሆሄ፣ አለን የሚሉትና የሚጠብቁት ነው፡፡ የተሰቀለው ክርስቶስ ይህን ሁሉ ትርጉም ይይዛል፡፡ እርሱ የተሰቀለው ሕይወት ነው፡፡ የተሰቀለው ቁስ አይደለም፡፡ ከፍ ብሎ ሊታይ፣ ያለ ውድድር ሊመለክ፣ ስሙ ሲረሳ ለምን ተረሳ? የሚባልለት፣ የዓይን ማረፊያ፣ በመሸፋፈን ሳይሆን በመገለጥ የሚከብር፣ ሹመት ሽልማታችን፣ የተወደድንበት ማስረጃ፣ የምንወድበት ኃይል፣ የልብ ጠጋኝ፣ አለኝታ፣ የምንጠብቀው ተስፋ፣ የሚጠብቀን ረድኤት … ነው ፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ጌታ አለማየት መንፈሳዊ ግርዶሽ መሆኑን ይናገራል፡- “የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፣ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?” ብሏል (ገላ. 3÷1)፡፡ የተሰቀለውን ጌታ አለማየት አለማስተዋልና አዚም ነው ይለዋል፡፡ አለማስተዋል የልብ ጨለማ ነው፡፡ አለማስተዋል ትልቅ ቅጣት የሚያመጣ ነው፡፡ ቃሉ፡- “የማያስተውልም ሕዝብ ይገለበጣል” ይላልና (ሆሴ. 4÷14)፡፡ አዚም የሚባለው፣ ሰውየው ዓይኑ ተገልጦ ያያል ግን አያይም፡፡ አዚም ልብ አለማለት ብለን የምንተረጉመው አይደለም፡፡ አጋንንታዊ አሠራርም ያለው ነው፡፡ በሚያየውና በሚታየው መካከል የገባ መንፈሳዊ ግርዶሽ አዚም ይባላል፡፡ ክርስቶስን እንዳናይ የሚያደርገን መንፈሳዊ ውጊያም እንጂ አለማወቅ ብቻም አይደለም (2ቆሮ. 4÷4)፡፡ ትልቁ ጨለማም የብርሃናትን ጌታ ማየት አለመቻል ነው፡፡
ታዲያ ከዚህ መንፈሳዊ ግርዶሽ እንዴት እናመልጣለን? ወደ ቃሉ ብርሃን መጥተን ራሳችንን ለማየት መፍቀድ ያስፈልገናል፡፡ ችግሩ እንዲርቅ የችግሩን መኖር ማመን ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ንስሐ መግባትና ረድኤተ መንፈስ ቅዱስን መለመን ይገባል፡፡ ያን ጊዜ ዕይታችን የጠራ፣ ውሳኔአችን የማያጸጽት፣ ኑሮአችንም የሚያስደስት ይሆናል፡፡
እግዚአብሔር መንፈሳዊውን ግርዶሽ ያንሣልን!!!