የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መንፈስ ቅዱስ ሆይ !

አብረኸኝ ከሠራህ ፣ ሥራዬን ከሠራህልኝ ፣ እባክህ ልሥራ ። ለነበሩት ፣ ላሉትና ለሚመጡት ሕይወታቸው የሆንከው ፣ የብርሃን ጮራ እየፈነጠቅህ ትውልድን የምታነቃው መንፈስ ቅዱስ ሆይ መድረሻዬን እንዳውቅ አንተ ከእኔ ጋር ሁን ። መንገዱን ያላገኙ ፣ ከምንጩ አጠገብ ቆመው የተጠሙ ፣ ያላቸውን ከጎደላቸው መለየት ያልቻሉ ፣ በሰዋዊ ቃላት ለመሰበር ቅርብ የሆኑ ፣ ክርስትናና ዓለም የተቀላቀለባቸው መልክ የለሽ የሆኑ ብዙ ጎስቋሎች ይጠብቁሃልና አንተ የልቦች ዕረፍት መንፈስ ቅዱስ ሆይ እባክህ ና ።

በቤት በውጭ መራቆት የሰለቻቸው ፣ በአደባባይ የሚቀጡ ፣ በጊንጥ የሚገረፉ ፣ በጸጸት የሚንገላቱ ፣ አንተን ለመውደድ ፍላጎት እንጂ አቅም ያጡ ፣ ትዕግሥት በማጣት ራሳቸውንና ቤታቸውን ያፈረሱ ምስኪኖች አሉና አንተ የአብና የወልድ ሕይወታቸው እባክህ ድረስላቸው ! ጥያቄው ያስጨነቃቸው ፣ የተቺዎች መልስ ሌላ እንቆቅልሽ የፈጠረባቸው ፣ ዝንጉ አእምሮ የሚታገላቸው ፣ ከቤተሰብ ክበብ አፈንግጠው ብቸኝነት የሚያዋራቸው ፣ ለመድረስ እየፎከሩ ጉዞ ያልጀመሩ ፣ በአሳብ ሲነኩ የሚውሉ ፣ ሕልማቸው ፍቺ ያላገኘላቸው የምኞት ፍልመኞችን ታሻቸዋለህና ጸሎትን የምትቀድስ መንፈስ ቅዱስ ሆይ እባክህ አግኛቸው !

በነፋስ አቅጣጫ የሚጓዙ ፣ በአየር ንብረት አገሩን ፣ በአየር ጠባዩ ቀኑን እየለኩ የሚኖሩ ፣ ሲሞቱ ሊያበቁ የሚጣደፉ ፣ ሰው የማይመጣባቸው ዝጎች ፣ ወደ ሰው የማይሄዱ ሽባዎች ፣ ከነማንነታቸው የሚቀበላቸው ይሻሉና የድሆች አምባ ፣ መሳይ የሌለህ መንፈስ ቅዱስ ሆይ እባክህ መርምርህ ፈውሳቸው ። በጅምር የቀሩ ፣ ዓለም ሊወርሳቸው እግድ ያወጣባቸው ብዙ ትውልዶች አሉና መንፈስ ቅዱስ ሆይ በማይደፈረው አክናፍህ ሰውራቸው ። ጰራቅሊጦስ ሆይ፣ ልክ የሌለው ምስጋና ላንተ ይሁን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ተጻፈ ጳጕሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ