መሳይ የሌለህ ብቸኛ ፣ ተመሳሳይ የሌለህ ልዑል ፣ ተቀራራቢ የሌለህ ምጡቅ ፣ የማትመረመር ምሥጢር ፣ የማትያዝ እሳት ፣ የማትወሰን መንፈስ ፣ የማትታፈን ምሉእ ፣ የማትቀየም የዋህ ፣ የማያደርጉልህ አድራጊ ፣ የማይናገሩህ የበላይ ፣ የማይከስሱህ ትክክል አንተ እግዚአብሔር ነህና አመሰግንሃለሁ ። የምድር መኸር ለአጨዳ በተቃረበበት ፣ የፍጥረት ሩጫ ሊገታ በደረሰበት ፣ የሚታየው ታጥፎ የማይታየው ሊዘረጋ መድረኩ በሚዘጋጅበት ፣ ሰው የሰውነቱን ክፋት ሁሉ ጨርሶ ለመጫረስ የመጨረሻ ቀጠሮ በያዘበት ፣ አገሩ ሰላም ነው ወይ ? የሚባልበት ጊዜ አልፎ ዓለሙ ሰላም ነው ወይ ? በምንልበት ዘመን ያለን ልጆችህ ሰላም እንልሃለን ። እየሰማን ደንቍረን ፣ እያየን ፈዝዘን ፣ ወንድም ወንድሙን ለሞት ሲያስበው መገረም አቁመን ፣ የትዳር መሠረቶች ሲናጉ የዕለት መጫወቻ ርእስ አድርገን ፣ ልጆች ያለ አሳዳጊ ጎዳና ሲወጡ እንዳላየን አልፈን ፣ የመጣውን ዕዳ ሳንከፍለው ሌላ ዕዳ እያቆየን ፣ እንደ አራዊት በመጫረስ ያሸነፈ የሚገዛበትን ዓለም ተመኝተን ፤ ልባችንን ለገንዘብ ስስ ፣ ላንተ ጠንካራ አድርገን ፣ ስለ ጸሎት እያነበብን መጸለይን አቁመን ፣ መፍትሔ እግዚአብሔር ነው እያልን በየዕለቱ ካንተ ርቀን ያለነውን ልጆችህን ስታስበን ምን አልከን ይሆን ? ለሰው ጠላቱ ቤተሰቡ የሆነበትን ፣ እርስ በርስ አሳልፈን የተሰጣጣንበትን ፣ ምስኪኖችን አፈናቅለን ፣ ችግረኞችን አይበቃችሁም ብለን ሞትን ከፍለን ፣ ከእኛ አስተሳሰብና ፍልስፍና ውጭ ያለውን ወገን መራገጫ ሜዳ አድርገን አድቅቀነዋል ፤ ይህ ሁሉ ሲሆን የማያዝነውን ልባችንን ይቅር በለው ። የሞትን ትርጉም የማያውቁ ሕፃናት ሲሞቱ ፣ ማለዳቸው ሠርክ ሲሆንባቸው ልባችን አላዘነምና ይቅር በለን ። በሽታ የዓለም ገዥ ሁኖ ድንበር የማያግደው ፣ ጠቢብ የማይመልሰው ሁኗልና በመገረፍህ ቍስል እባክህ ፈውሰን ። መዓትህን በምሕረት መልስልን ። አሜን ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 12 ቀን 2014 ዓ.ም.