የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መዝሙረ ምእመን 1

መዝሙረ ዳዊት 1፡1 ላይ የተመሠረተ ምክር

ማባበል ካለበት ፣ “አንተ እኮ ትልቅ ነህ” ከሚለው ፣ አስብቶ ከሚያርደው ፣ በውዳሴ ከንቱ ከሚያሰክረው ፣ ልጅን በአባቱ ላይ ፣ አቤሴሎምን በዳዊት ላይ ከሚያሥነሣው ከአኪጦፌል ምክር ፣ “እኔ የቋጠርሁት አይፈታም” እያለ በኃጢአቱ በሚኮራው ፣ ክፉ ሰው ምክር ካልሄድህ ምስጉን ነህ ። ፈተና ወዳንተ ሳይመጣ ወደ ፈተና መሄድ ፣ መድኃኒት አለና ብሎ በሽታን መዳፈር ፣ በሚያዳልጥ ስፍራ ላይ ቆሞ “አድነኝ” እያልህ መጸለይ ፣ እየጠጣህ ላለመስከር መታገል ፣ ከተቃራኒ ጾታ ጋር በድብቅ ስፍራ ተቀምጠህ እንዳትወድቅ መሞከር ከንቱ ግብዝነት ነው ። ነገር ግን በኃጢአተኛ መንገድ ካልቆምህ ፣ ኃጢአተኞች ሲያልፉ “ና እንሂድ” አይሉህምና ዕድለኛ ነህ ፣ ምስጉን ነህ ። ክፉ ባልንጀርነትን ካላራቅህ ፣ ደግ ባልንጀርነትን ካልፈለግህ የድንገት ፍላጻ ያቆስልሃል ። የዝሙት ፊልም እያየህ ለጸሎት አትነሣሣም ፣ ተውኔት ቤት እየዋልህ ወደ ጉባዔ እግዚአብሔር አትሄድም ። ኃጢአትን ከነምክንያቱ ከተውህ ምስጉን ነህ ።

በዋዛ ፈዛዛ ዘመንህን ካልጨረስህ ፣ “ሳቅ አምጡ” እያልህ አዝማሪ ዘዋሪ ካልጋበዝህ ፣ በመዳን እንጂ በመደንዘዝ ደስታን ካልፈለግህ ብፁዕ ነህ ። ከዘላለም ሕይወትህ ፣ ከምድራዊ ኑሮህ ጋር ምንም ግንኙነት በሌለው ነገር ጊዜህን ካላባከንህ ብፁዕ ነህ ። ሺህ ሰው በአንዴ ሲሞት “የአገሬ ገበሬ ይዋደዳል” ከሚሉ ፣ ሰው አገር ፣ አገርም ሰው መሆኑን ረስተው “አገር ከሚሞት ሰው ይሙት” ከሚሉ ፣ የራሳቸው ላብ እያስጨነቃቸው በሰው ደም ከሚቀልዱ ፣ እነርሱ እየሸሹ “ደም ሳይፈስስ ስርየት የለም” ከሚሉ ፣ “ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” እያሉ በደም ጎርፍ ከሚታጠቡ ፣ ሺህዎችን ሸኝተው ምንም እንዳልተፈጠረ ከሚያፈጥጡ ፣ የልጃቸውን ከባድ እንቅልፍ እየፈሩ በሰው ልጅ ሞት ከሚነግዱ ከዋዘኞች ወንበር ካልተቀመጥህ ብፁዕ ነህ ።

ወደ ገደል እየመራ ስትወድቅ ከሚስቀው ከክፉዎች ምክር ፣ በቃሉ ነው ነው የምትድነው ። ለውድቀት ከሚያጋልጡ ቦታዎች ፣ ሁኔታዎች የምትርቀው ያለማቋረጥ ነገረ መለኮትን ስታስስ ነው ። ክፉ ባልንጀርነትን ፣ የመብል ማኅበርን የምታመልጠው በቅዱሳን ኅብረት ፣ በምእመናን አንድነት ነው ። ገዳይ ጨካኝ ነው ፣ ዋዘኛ ግን በሬሳ ላይ ሳቅና ቅኔ የሚያመርት ነው ። በምድር ላይ የጭካኔ ጥጉ ዋዘኝነት ነው ። ዋዘኝነት እውነታን አለመቀበል ፣ ፣ ደምን ዝናብ ነው ፣ ሞትን ልደት ነው ብሎ መሳለቅ ነው ። በዚህ ወንበር ያልተቀመጠ ፣ መቼም ዋዘኛ አይራመድምና የሚራመዱትንም ይተቻልና ፤ በዚህ የስላቅ መደብ ካልተቀመጥህ ብፁዕ ነህ ።

አቤቱ ቃልህን እወደው ዘንድ በመልካም አስበኝ !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ተጻፈ ሐምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ