በመዝ. 1፡2 ላይ የተመሠረተ ምክር
“ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል ፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል ።” መዝ. 1፡2።
“አንተ ትልቅ ነህ” እያሉ ከሰገነት ላይ ከሚያወጡህ ፣ በልባቸው እየሳቁብህ ግዙፍ ወንበር ከሚለቁልህ ፣ “እንዳንተ ያለ አልተፈጠረም” እያሉ ማማ ላይ ከሚሰቅሉህ ፣ “ያንተ ቀለምና ቋንቋ መሳይ የለውም” እያሉ ነፋስ ከሚሞሉህ ከክፉዎች ምክር ራቅ ። እነዚህ ለስልሶ እንደሚዋጋ እንደ አዛባ እሾህ ፣ እግር ሥር እንደሚሽሎኮሎክ መርዛም እባብ ናቸው ። ወንድምን በወንድም ላይ ያስነሡት ፣ አንድ አገርን የቆራረሱት ውዳሴ ከንቱ በማፍሰስ ፣ የሞኙን ልብ በማንገሥ ነውና ስትወድቅ ከሚስቁ ከክፉዎች ምክር ተጠንቀቅ ። የክፉዎች ምክር ራስህን ለመውደድ ሌላውን መጥላት መስፈርት አድርጎ ያቀርባል ። አዎ አንተ ቆንጆ ነህ ፣ ነገር ግን ሌላው አስቀያሚ ነው ብለህ ለማጥፋት መነሣት አይገባህም ። ክፋትና ደግነት የሰውነት ጠባይ እንጂ የቀለምና የቋንቋ ወይም የጎሣ ጉዳይ አይደለም ። ስለዚህ እገሌ ጎሣ ክፉ ነው እገሌ ደግ ነው ብለህ አትሞኝ ። ከሁሉም ደግና ክፉ መኖሩን አስተውል ። ደግሞም “የሰው አገሩ ምግባሩ” መሆኑን ተረዳ ።
በሕፃናት ከሚነግዱ ፣ ሰውን እንደ ዕቃ ከሚሸጡ ፣ ሳይቸግራቸው ከሚያስቸግሩ ፣ በራራላቸው ላይ ከሚጨክኑ ፣ ጭካኔን ፈጥረው ከሚያሰራጩ ፣ አእምሮአቸው ታውኮ ከሚያውኩ ፣ ለሰው በሽታና ሞትን ከሚያወርሱ ፣ ጥጋባቸውን ለግል ረሀባቸውን ለጋራ ከሚያደርጉ ከኃጢአተኞች መንገድ አትቁም ። ጆሮህን ግፍ እንዳያስለምዱት ፣ ደጋግመው በመናገር ተማሪያቸው እንዳያደርጉህ ተጠንቀቅ ። በዚያ መንገድ የሄዱ እንደ ቃየን ተቅበዝባዥ የሕሊና ስደተኛ ሁነዋል ። ፈርዖን ከነሠራዊቱ በቀይ ባሕር ሰጥሟል ፣ ናቡከደነጾር ጤዛ ለብሶ ሰባት ዓመት ሣር ግጧል ። ከኃጢአተኞች መንገድ ዞር የምትለው ፣ የክፉዎችን ምክር እንቢ የምትለው ቃለ እግዚአብሔርን ሌሊትና ቀን ስታስብ ነው ።
ልባቸው ከማያዝን ፣ የደስታህ እንጂ የኀዘንህ አጋር ካልሆኑ ፣ ብልጠትን የኑሮ ዘዴ ካደረጉ ፣ ሰው የማያልቅ መስሎአቸው ፣ በማያውቃቸው አገር እንደ ጅብ ቁርበት አንጥፉልኝ ከሚሉ ፣ በምድረ በዳ እየሸሹህ በከተማ ከሚወዳጁህ ራቅ ። እነዚህ ዋዘኞች የዕድሜህ ብል ፣ የዘመንህ ነቀዝ ናቸው ። ከእነርሱ ፌዘኛነት ፣ ሃይማኖትን ሻጭነት የምትድነው ቃሉን በማሰላሰል ነው ።
ምክረ ሥላሴ ከሚገኝበት ቃሉ ፣ የክፉዎች ምክር እንዳያርቅህ ተጠንቀቅ ፤ ኃጢአተኞች እንደ ውኃ እያሳሳቁ እንዳይወስዱህ ፣ ከመንገዳቸው ከፊልም ፣ ከነውር ድርሰታቸው ራቅ ። ቃሉን እንዳታነብ ከሚያደርግህ ቀልዳ ቀልድ ሽሽ ። ያን ጊዜ ቀንህ ይበራል ፣ ሌሊትህ የዕረፍት ይሆናል ። የምትታወከው ሁከት መጥቶብህ ብቻ ሳይሆን ወደ ሁከት ሂደህም ነው ። ሰላምህን ጠብቃት ፣ እርስዋም ትጠብቅሃለች ። በክፉ ዘመን ቀንና ሌሊት ቃሉን በመስማት ራስህን አትርፍ ።
የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ቀንና ሌሊቴን በቃልህ ሸፍነው !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ተጻፈ ነሐሴ 3 ቀን 2015 ዓ.ም