የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መጤዎች አይደለንም

“በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል ፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ፤ በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል ፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ ።” ኤፌ. 2፡20-22።

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ያገኙትን መንፈሳዊ መብት ይዘረዝራል ። እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም የእግዚአብሔር ቤተሰቦችና የቅዱሳን ዘመዶች ናችሁ ይላል ። እንግዳ ፊቱ እየሳቀ ልቡ የሚፈራ ነው ። እንግዳ በልቡ ቆሞ ተቀምጦ የሚበላ ነው ። እንግዳ ቢውል የማያድር ፣ ቢያድር የማይሰነብት ፣ ቢሰነብት የማይኖር ነው ። በዚህ ዓለም ላይ እንግዶች ነን ። እንግዳ ናችሁ የሚለን ያው መጽሐፍ እንግዳ አይደላችሁም ይለናል ። እንግድነታችን ለዚህች ዓለም ነው ። የማናውቃቸው ቤተሰቦች በልደት ተቀበሉን ፣ በዕለተ ሞታችንም የማናውቃቸው ሰዎች ይሸኙናል ። ቤት ስንሠራ እኛው ራሳችን እንደምንፈርስ እያሰብን ፣ ስንሮጥ አንድ ቀን እግራችን ተገንዞ መቃብር እንደምንወርድ እያመንን ሊሆን ይገባዋል ። ለመኪና ሁሉ ፍሬን ባይኖረው ኖሮ የአደጋ መሣሪያ ፣ የማለቂያ ዕቃ ይሆን ነበር ። የሰው ልጅ ፍሬኑ ፣ የትዕቢት ማብረጃው ሞቱን ማሰቡ ነው ። ከቤታችን ስለ መውጣታችን እንጂ ስለ መመለሳችን እርግጠኛ አይደለንም ። እርግጠኝነት በሌላት ሕይወት የሌላውን ኑሮ ማፍረስ አይገባንም ። በሰማይ ቤታችን ፣ በእግዚአብሔር ወዳጃችን ፣ በመንግሥተ ሰማያት ርስታችን ፣ በቤተ ክርስቲያን ማኅበራችን ግን እንግዶች አይደለንም ። ሐዋርያው መጻተኞች አይደላችሁም በማለት አጽንኦት ይሰጣል ። መጤዎች አይደላችሁም እያለ ነው ። እኛ ትክለኞች ነን ፣ እነ እገሌ ደጅ ጠኚዎች ናቸው ። እኛ ባለ ርስት ነን ፣ እነ እገሌ የመኪና ጎማ የተፋቸው ሰዎች ናቸው ። እኛ ነዋሪዎች ነን ፣ እነ እገሌ ስደተኞች ናቸው የሚል ድምፅ ብዙዎችን አድክሟል ። በሰማይ ቤታችን ፣ በእግዚአብሔር አባታችን ፊት ግን እንግዶችና መጤዎች አይደለንም ። “ተወልዶ ብልጫ ፣ አንክሶ ሩጫ የለም” እንዲሉ ።

በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ መታነጽ ምንድነው  ብለን መጠየቃችን አይቀርም ። ቤተ ክርስቲያን በፍጡራን ላይ ተመሥርታለች ማለት ነው ወይ  የሚል ጥያቄ ያስነሣል ። የቤተ ክርስቲያን መሠረትም የክርስቶስ ደም ነው እንላለን ። አዎ ነቢያት ፣ ነቢያት የተባሉት ስለ ክርስቶስ ቢናገሩ ነው ። ሽሮ በርበሬን የሚተነብዩ ነቢያት አይደሉም ። እውነተኛ ነቢይ ስለ ክርስቶስ ይታየዋል ። ሐዋርያት ፣ ሐዋርያት የተባሉት የክርስቶስ መልእክተኞች ወይም እንደ ራሴዎች በመሆናቸው ነው ። አባቶች ይህን በአጭሩ ሲገልጡ፡- “ነቢያት በመደመዱ ፣ ሐዋርያት ገደገዱ” ይላሉ ። መመድመድ ዱሩን መመንጠር ነው ። እውቀት ገላጭ ነቢይ የሌለበት ዓለም ዱር ነው ። ጨለማና መንገድ የለሽ ነው ። መገድገድም ለቤቱ መሥሪያ እንጨት መደርደር ነው ። ለምትሠራዋ ቤተ ክርስቲያን የገደገዱት እንጨት ምሥጢረ ሃይማኖት ነው ። በነቢያት ትንቢት ቤተ ክርስቲያን መመሥረቷ በብዙ ተስፋና ናፍቆት ክርስቶስን መጠበቅዋ ነው ። ነቢያትና ያገለገሉት ያ ሕዝብ የቤተ ክርስቲያን የተስፋ አባላት ነበሩ ። በሐዋርያት መመሥረቷ ሐዋርያት በሰበኩት በክርስቶስ ላይ ማረፍዋን የሚገልጥ ነው ። ሙሽሪት ቤተ ክርስቲያን ነቢያት ለክርስቶስ ዐጩአት ፣ ሐዋርያት ሚዜ ሆኗት ።

ሕንጸትን ያነሣል ። ቤተ ክርስቲያን ከበዓለ ሃምሳ ጀምሮ በሕንጸት ላይ ናት ። የሕንጸቱ ሕያዋን ጡቦች ምእመናን ናቸው ። የሕንጸቱ የመጨረሻ ዓላማ የእግዚአብሔር መኖሪያ መሆን ነው ። እግዚአብሔር አድሮባት ለዘላለም በክብር የምትኖር ቤተ ክርስቲያንን ማየት የመለኮት ዘላለማዊ እቅድ ነው ። አንድ ጡብ ብቻውን ቤት አይሆንም ። አንድ ምእመን ቤተ ክርስቲያን ቢባልም ብቻውን ቤተ ክርስቲያን አይሆንም ። ጌታችን የማዕዘን ራስ ድንጋይ ተብሏል ። የማዕዘን ራስ ድንጋይ ከብዙ አቅጣጫ የሚመጣውን ግንባታ የሚሸከምና የሚያገናኝ ነው ። ከሕዝብና ከአሕዛብ የመጡትን ያገናኘው ፣ ሁሉም ተሸክሞ ውበት የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ። ከእናቱ ማኅፀን የተመረጠው ነቢይ ኤርምያስና ፣ ዘመኑን በሙሉ በኃጢአት የፈጸመ ፈያታዊ ዘየማን/የቀኙ ወንበዴ የተገናኙት በማዕዘኑ ራስ ድንጋይ ነው ። እግዚአብሔር በመሥዋዕታን ደስ ከሚለው በላይ በኅብረታችን ደስ ይለዋል ። ኅብረትም መሥዋዕት ነው ። በመሥዋዕት ላይ መሞት አለ ፣ ኅብረት ለማድረግም እኔነትን መግደል ያስፈልጋል ። በመሥዋዕት ላይ እሳት አለ ፣ ኅብረትም ከሚለበልቡ ሰዎች ጋር ለመኖር መጨከንም ነው ። በሰማይ በኅብረት ልንኖር ዛሬ መለያየት አይገባንም ። እየተጋጠምን ነውና ሙሉ በሙሉ ባንስማማ ችግር የለውም ። እየተሠራን ነውና ጉድለት ቢታይብን ተሠርተን አለማለቃችንን አመልካች ነው ።

የኤፌሶን መልእክት ምዕራፍ ሁለት ትርጓሜ ተፈጸመ ።

የረዳን እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ