መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » መጨነቃችን ለምንድነው ?

የትምህርቱ ርዕስ | መጨነቃችን ለምንድነው ?

ኑሮውን እንግሊዝ ያደረገው የተሻለ ነገር ፈልጎ ነው ። ሕንድ ራሱንና ቤተሰቡን ለማገዝ በቂ አልሆነችለትም ። በለንደን ከተማ ነዋሪ የሆነው ፕራቲክ ጆሺ ላለፉት አምስት ዓመታት ያልተሳካለት ነገር ሚስቱንና ልጆቹን ወዳለበት አገር አምጥቶ አብሮ መኖር ነው ። ሩጫው ውስጥ የቤተሰብ ናፍቆት ነበረ ። ፍቅር ፣ እልህ ፣ ጥረት እነዚህ ሁሉ ታግለውታል ። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ አሳቡ ሞላለት ። ኑ ብሎ መጥራትን አልፈለገም ። አብረው በደስታ ከሕንድ ወደ ለንደን እንዲጓዙ አለመ ። ወደ ሕንድ ሲገባ በምትኖርበት አካባቢ የታወቀች የሕክምና ባለሙያ የሆነች ሚስቱ ተቀበለችው ። ከእርሱ ጋር ለመጓዝም የዓመታት ምኞት ሞልቷልና ከሁለት ቀናት በፊት በፈቃድዋ ሥራ ለቀቀች ። ሥራ ከለቀቀች ከሁለት ቀን በኋላ ጉዞዋን ወደ ለንደን ለማድረግ ዕቃዋን ሸከፈች ። ቤተ ዘመዱን ተሰናብተው ፣ ተለያይተው መኖራቸው ያሳስባቸው የነበሩትን የቅርብ ሰዎች እጅ ነሥተው ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ጉዞ ጀመሩ ። ሦስት ልጆቻቸውን የያዙት ከራሳቸው ጋር አምስት ነፍስ የሆኑት ቤተሰብ ፣ በምዕራብ ሕንድ ከሚገኘው ከአሕመዳባድ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ለንደን የሚደረገውን ጉዞ ተሳፈሩ ።

የተሳፈሩበት አውሮፕላን ቦይንግ 787-8 ድሪምላይነር አውሮፕላን ነው ። የበረራ ቍጥሩም ኤ አይ 171 ነው ። በዚህ አውሮፕላን ውስጥ ከበረራ ሠራተኞች ጋር አጠቃላይ 242 ሰዎች ተሳፍረዋል ። ይህ ቤተሰብ የተቀመጡበት ወንበር መደዳ ሲሆን ባልና ሚስት አብረው ፣ ሦስቱ ልጆቻቸው በአንድ ላይ ተርታ ላይ ነበሩ ። ይህ ጉዞ የዘመናት ጥረት ፣ ጸሎትና ምኞት ውጤት ነበረ ። የሚወዱአቸው ቤተሰቦቻቸው እንዴት ሆነው ይሆን ? ብለው እንደሚጠብቁአቸው እርግጠኛ ናቸው ። ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በዕለተ ሐሙስ አውሮፕላኑ እንቅስቃሴ እንደ ጀመረ በታላቅ ደስታ መላው ቤተሰብ ፎቶ መነሣት ጀመረ ። አውሮፕላኑ በረራ ከጀመረ በኋላ ኢንተርኔት ሳይቸገሩ ወዲያው ያንን ውብ የቤተሰብ ፎቶ ለዘመዶቻቸው አጋሩት ። እኛ ያለነው በደስታ ነው ፣ እናንተም ደስ ይበላችሁ አሉ ። በርግጥም ፎቶ ይናገራል ። ደስታቸው ከጨዋነታቸው ጋር አብሮ ይወጣል ። ያ የቤቱ አባወራ ለንደን ሲደርስ በር ከፍቶ ቤተሰቡን “የምንኖረው እዚህ ነው” ሲል ይታየዋል ። ያ ቤት ለእርሱም አዲስ ነው ፣ ምክንያቱም ቀድሞ በግሉ የነበረ አሁን አራት ሰው የጨመረ ነውና አዲስ ቤት ተከራይቷል ። የሰው አገር ኑሮ እንደ ጠበቁት እንዳልሆነ አሁን ቢናገርም የሚያምነው የለም ። በልቡ ውስጥ ብዙ አሳብ ይመላለሳል ። ከደኅና ሥራዋ አስወጥቼ አሁን የለንደን ኑሮ ባይጥማት ምን ትል ይሆን ? እያለ ስለሚስቱ ማሰቡ አይቀርም ።

አውሮፕላኑ የበረራውን ፈቃድ አግኝቶ መሬት ለቆ በአየር ላይ ለመሰቀል ተንደረደረ ። 30 ሰከንዶች የበለጠ መብረር አልቻለም ። በአንድ የሕክምና መስጫ ጣቢያና የተማሪዎች ማደሪያ ሕንፃ ላይ ተከሰከሰ ። አንድ መንገደኛ በተአምር ሲተርፍ 241 መንገደኞች በሙሉ አለቁ ። ለንደንን እያሰቡ አንድ ሕንፃ ላይ ቀሩ ። ቤተሰቦቻቸው ለከርሞ ያገናኘን ብለው ነበረ ፣ አሁን በሬሳ ተገናኙ ። ከደቂቃ በፊት ውብ ፎቶዎች ነበሩ ፣ አሁን ግን የሚቀበር ደኅና አስከሬን የለም ። እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ አውሮፕላኑ በተከሰከሰበት አካባቢ የነበሩ ብዙ ሰዎች እንደ ሞቱ ይገመታል ። ዓለም የቅጽበት ዕድሜ ናት ። ደስታው በጣም አጭር ነው ። አጭር ደስታ ፣ ረጅም ኀዘን የዓለም መገለጫ ነው ። ያ አባወራ አምስት ዓመት ሙሉ የደከመለትና የናፈቀው ነገር አምስት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ሁሉም ነገር በምድር ላይካስ አመድ ሆነ ። ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀሩ አምስቱ የቤተሰብ አባላት ፣ የአምስት ዓመት ምኞታቸው ሳይፈጸም ፣ በአምስት ደቂቃ አለቁ ።

በጣም እንጨነቃለን ። ስለ ራሳችን ስለ ቤተሰባችን አቅላችንን እስክንስት እንረበሻለን ። አሳባችን ግን ሞልቶም ላይሞላ ይችላል ። ብዙ የተጨነቅንለት ጉዳይ ደስታው ለአምስት ደቂቃ ሊሆን ይችላል ። ዓለም ለማለፍ በጣም ትቸኩላለች ። ራሳችንንም ቤተሰባችንንም ሳናተርፍ መቅረትም አለ ። ይህ አባወራ አንድ ቀንም ለራሱ አልኖረም ። ሚስቱና ልጆቹ በዓይኑ ላይ ነበሩ ። ኑ ቢላቸው ኖሮ የእርሱ የመሄጃና የመመለሻ ትኬት ዋጋ ይቀንስለት ነበር ። ጉጉቱ ግን ከፍ ያለ ነበረ ። በሕንድ የቀረውን ቤተሰቡን የተሰናበተው ለካ ለጊዜው ሳይሆን ለዘለቄታው ነበር ። ለንደን ለማደር አስበው ሰማይ አደሩ ።

የዚህ ዓለም ኑሮ ከእውነቱ ውሸቱ ይበዛል ። አለሁ ማለት ትልቁ ውሸት ነው ። አሳባችን ሩቅ ፣ አዳራችን ቅርብ ነው ። የምንጨነቀው ለምንድነው ? ስኬት ሞትን ሲያፋጥን እንጂ ሲያርቅ አይተንም አናውቅም ። በእግዚአብሔር ተስፋ ከማድረግ ውጭ በዚህ ዓለም ላይ ተማምነው የሚያወሩበትና የሚኖሩበት ምንም ነገር የለም ። እነዚህ የሞቱት ከእኛ ይልቅ ኃጢአተኞች ስለሆኑ አይደለም ። እግዚአብሔር እነርሱን አስችሎ እኛን ሊያስተምረን ስለፈለገ ነው ። እንደ ባለ አእምሮ ማለም ማቀድ መልካም ነው ። ከእግዚአብሔር ጋር ያልቆጠረ ግን ሲቆጥር ይኖራል ። የቆጠርነውን እየረሳን ስንቸገር አብሮ የሚያቋጥር ሰው እንፈልጋለን ። አሊያ ስንቆጥር ልንውል ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ያልቆጠረም ሲቆጥር ይኖራል ። በእውነት ለቤተሰባችን የሚያስፈልገው የሰለጠነ ምድር ፣ የተቀናጣ ኑሮ ፣ የተሻለ ትምህርት ቤት ነው ብለን ማሰባችን መልካም ነው ። ከሁሉ በፊት የሚያስፈልጋቸው እግዚአብሔር ነው ። እየሮጥንም እየተጨነቅንም አይሆንምና አንዱን መምረጥ አለብን ። የሰው አቅም ማሰብ ነው ፣ መፈጸም የአምላካችን ሥልጣን ነው ። የዓለም ደስታ ዕድሜው አጭር ነውና ለሰማዩ ደስታ እንዘጋጅ !

ኤልሻዳይ ሆይ የዓለምን ከንቱነት የቃልህን ጽኑነት ግለጥልን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ