የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መጻጉዕ

                      የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ……..ዓርብ፣ የካቲት ፳፯ /፳፻፯ ዓ.ም.
በብዙ ሕመም ይልቁንም በአገራችን እርዳታ ልታገኝ ባልቻለችበት በሽታ ተጨንቃ የነበረች አንዲት ወጣት እህታችን ከአገር ውጭ በተደረገላት ሕክምና ከዳነች በኋላ ተገናኘን። ይህች እህታችን በሕይወቷ አንድ ጥያቄ እንደ ተፈጠረ ነገረችኝ፡- “እግዚአብሔር ለምን በዚህ ሕመም ውስጥ አሳለፈኝ? ብዬ መጠየቅ ጀመርኩ፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ሕመም ውስጥ እንዳልፍ ያደረገው በዚህ ሕመም ውስጥ ለሚያልፉ ወገኖቼ እንድራራና እርዳታ እንዳደርግ ነው” አለችኝ፡፡ አሁን የወደፊት ራእይዋ በዚህ በሽታ ለሚሰቃዩ ወገኖች የመንከባከቢያ ማዕከል መክፈት መሆኑን በነገረችኝ ጊዜ እጅግ ደስ አለኝ፡፡ የእግዚአብሔርን የልቡን አሳብ ያወቀችለት ያህል ደስታ ተሰማኝ፡፡ እግዚአብሔር በችግር ውስጥ የሚያሳልፈን በችግር ውስጥ ለሚያልፉት እንድናዝንም ነው፡፡ ለእስራኤል ልጆች ከተሰጠው ማስጠንቀቂያ አንዱ፡- “እናንተም በግብፅ ምድር እንግዶች ነበራችሁና ከእናንተ ጋር የሚቀመጥ እንግዳ እንደ አገር ልጅ ይሁንላችሁ÷ እርሱንም እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ” (ዘሌ. 19÷33-34)  የሚል ነው፡፡
በሽታ የሥነ ልቡና፣ የአካል ጉዳት ብቻ ሳይሆን ለማኅበራዊ ቀውስም አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ማኅበረሰቡ አቅሙና የኑሮ ሰላሙ በበሽታ ምክንያት ይዛባል፡፡ የአንድ ሰው በሽታ የግሉ ብቻ አይደለም፡፡ አብረውት የሚታመሙ ብዙ ወገኖች አሉ፡፡ በበሽታ ምክንያት ሊሠሩ የሚገባቸው ተቀማጮች፣ ሊረዱ የሚገባቸው ተረጂዎች ይሆናሉ፡፡ የታመሙ ሰዎች ወዳጅ፣ ሐኪም፣ መንፈሳዊ አማካሪ ይፈልጋሉ፡፡ ከሕይወት ገጽታ አንዱ በበሽታ ውስጥ ማለፍ ነው፡፡ የተራ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ሁላችንም በዚህ የሕይወት መስመር ውስጥ እናልፋለን፡፡ እግዚአብሔር በነገው በሽታችን እንዲራራልን ዛሬ ለተቸገሩት በሕመም ለሚሰቃዩት መልካምነትን ማሳየት ፍቅራችንን በተግባር መግለጥ አለብን። ቃሉ:–  “ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው÷ እግዚአብሔር በክፉ ቀን ያድነዋል፡፡ እግዚአብሔር ይጠብቀዋል÷ ሕያውም ያደርገዋል÷ በምድር ላይም ያስመሰግነዋል÷ በጠላቶቹም እጅ አያሳልፈውም። እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል” ይላል (መዝ. 40÷1-3)፡፡


ሕመም ብቻውን አይደለም፣ አብሮት የሚመጣ የችግር ጓዝ አለው፡፡ በሕመም ወዳጅ ይርቃል፣ ገቢ ይቀንሳል፣ ብቸኝነት ይመጣል፣ ተስፋ መቊረጥ ይከሰታል፡፡ እግዚአብሔር ካዘጋጀልን ትልቅ በረከት፣ በጌታ ፊትም ቆመን ከምንመልሰው  የእምነት ጥያቄ አንዱ ሕመምተኞችን መጠየቅ ነው (ማቴ. 25÷43)፡፡ ሕመምተኛና ሕፃን በትንሹ የሚያዝንና የሚደሰት ነው፡፡ ሕመምተኞችን ማጽናናት፣ በተስፋ ቃላትም ተስፋ የሚያስቆርጣቸውን ተዋጊ መፋለም ይኖርብናል፡፡ ሐኪም የሚሰጠው መድኃኒት የሚፈውሰው ጥቂቱን ነገር ነው፡፡ ኪኒን አካላዊ እንጂ መንፈሳዊ ፈውስ የለውም፡፡ ትልቊ ሕመም ያለው ደግሞ በኅሊናችን ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ ፍቅርና ወዳጅነት ትልቁ ሕክምና መሆኑን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ 
የዐቢይ ጾም አራተኛው እሑድ መጻጉዕ ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድዉያንን መፈወሱን ዕውራንን ማብራቱን የምናስብበት ቀን ነው፡፡ መጻጉዕ ማለት በሽተኛ ማለት ነው። በዚህ ቀን እግዚአብሔር በበሽተኞች ላይ ስላለው የፈውስ ዓላማ ከተቀደሱ ታሪኮች እየተጠቀሰ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ለበሽተኞችም ፈውስ ይበሰራል፣ ስለ ፈዋሽነቱም እግዚአብሔር ምስጋናውን ይቀበላል፡፡ እኛም ሕመምተኞችን እንድንጎበኝ በቀኑ እንታዘዛለን፡፡ በዕለቱ የሚዘመረው ዝማሬ ቅዱስ ያሬድ እንደ ደረሰው እንዲህ የሚል ነው፡-
“ዐበይተ ኃይላተ/2/
 ተአምረ ገብረ ኢየሱስ በዕለተ ሰንበት
 እምኲሉ ዘየዐቢ እነግር ዘገብረ
 ጽቡር የአውር ሕያው ዓይነ
ውእቱሰ ወረቀ ምድረ ወገብረ ጽቡረ
 ወቀብዖ ዓዕይንቲሁ ለዘዕውሩ ተወልደ ወአህየዎ”
ትርጉም፡-
“በሰንበት ቀን ኢየሱስ ታላላቅ ተአምራትን ያደርግ ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ የሚበልጥ ያደረገውንም እናገራለሁ። ጭቃ ደህናውን ዓይን ያጠፋል፣ እርሱ ግን በምድር ላይ ተፍቶ ጭቃ አድርጎ ዕውር ሆኖ የተወለደውን አዳነ። ይህ ግሩም ምሥጢር ነው፡፡”
ቅዱስ ያሬድ በሰኞ ዕለት በሚባለው የመጻጉዕ መዝሙር ደግሞ እንዲህ ብሏል፡-
በመስቀልከ ክርስቶስ
አውጻእከነ እምጽልመት ውስተ ብርሃን
በወንጌል መራሕከነ ወበነቢያት ናዘዝከነ
በመስቀልከ ጽልመት አብራኅከ
ወቀጥቀጥከ ኃይሎ ለጸላዒ
ትርጉም፡-
ክርስቶስ ሆይ በመስቀልህ ከጨለማ ወደ እውነተኛ ብርሃን አወጣኸን
 በወንጌል መራኸን በነቢያትም አጽናናኸን
 በመስቀልህ ጨለማን አበራህ
 የጠላትንም ኃይል ቀጠቀጥህ”
ሰው ለሌለው ሰው ሆነ
በዕለቱ የሚነበበው የወንጌል ክፍል የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 5÷2-9 እንዲህ ይላል፡-
“በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት፡፡ በእነዚህ ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበርና እንዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር  በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደነበር አውቆ፡- ልትድን ትወዳለህን? አለው ድውዩም ጌታ ሆይ÷ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፤ ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት፡፡ ኢየሱስ፡- ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው፡፡ ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ”
ከዚህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ሰባት ነጥቦችን ማውጣት እንችላለን፡-
1.     የበጎች በር
2.    አምስት መመላለሻ
3.    የውኃው መንቀሳቀስ
4.    መጀመሪያ መግባት
5.    ሠላሳ ሳምንት ዓመት
6.    የሰው ረሀብ
7.    አልጋን መሸከም
የበጎች በር
ለመሥዋዕት ወደ መቅደሱ የሚሄዱ በጎች ይገቡ የነበረው በዚህ በር ነው፡፡ በኢየሩሳሌም ቅጥር የተለያዩ በሮች ነበሩ፡፡ የሰው በር ከበጎች በር የተለየ ነበር። ሁሉም በራሱ በር ብቻ ይስተናገድ ነበር፡፡ ይህ ክብረትን ብቻ ሳይሆን አደጋንም ለመከላከል ይረዳል፡፡ ትልቅ ችግር የሚፈጠረው የሰውንና የእንስሳትን በር አንድ ስናደርገው ነው፡፡ ዛሬ ያለው ትልቊ ቀውስ ሰውን በሰው ክብር እንስሳን በእንስሳ ጥቅም፣ ገንዘብን በገንዘብ ልክ ያለማየት ነው፡፡ ከሰው ልጅ የውሻ ልጅ የሚል ተረት አለን፡፡ የተረቱ ምሥጢር ሕፃን ወስዶ ከማሳደግ ውሻ ማሳደግ ይሻላል የሚል ነው፡፡ ልጁ ካደገ በኋላ ይከዳል ውሻ ግን አይከዳም ማለት ነው፡፡ ችግረኛን እንኳ የምንረዳው ነገ የሚያደርግልንን ነገር ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ሰው ግን ከእንስሳ ከፍ ይላል፡፡ እኛ የምንፈልገው የማይታዘበንን አሳብ የማይሰጠንን እንስሳ ነው፡፡ የሚቃወሙን የሚከዱን ሰዎችም ለአእምሮ ጥንካሬአችን ያስፈልጉናል፡፡ ስለ አንድ ብር ሰው የሚገድሉ ሌቦች ለእነርሱ ከአንድ ሰው አንድ ብር ስለሚበልጥ ነው፡፡
በዚህ የበጎች በር ጌታችን መግባቱ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ ትልቁ መሥዋዕት መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ ትልቁ በግ የዋሁ የእግዚአብሔር ልጅ በበጎች በር ገባ፡፡ በዚህ በር ለመሥዋዕት ብዙ ሺህ በጎች ተነዱ፡፡ ኢየሱስ ግን በፈቃዱ እንደ በጎች ሊታረድ በዚህ በር ገባ፡፡ የእኛ ጌታ አማራጭ አጥቶ አልሞተም፡፡ ሊሞት መጥቶ ሞተልን!
አምስት መመላለሻ
ወደ መጠመቂያይቱ የሚገቡ በሽተኞች መንገድ እንዳያጡ መውጫና መውረጃው ብዙ ነበር፡፡ ከብዙ መግቢያዎች ግን አንዱ እንኳ ለመጻጉዕ ወይም ለሠላሳ ስምንት ዓመት በሽተኛው ዝግ ሆኖበት ነበር፡፡ ብዙ አማራጮች ነበሩ፣ ነገር ግን አንዱንም ማግኘት አልቻለም፡፡ ዛሬም ብዙ አማራጭ እያላቸው በአንዱ መግባት ያልቻሉ በማይታይ ገመድ ታስረው የሚኖሩ ወገኖች አሉን፡፡ መማር እየቻሉ የማይማሩ፣ መሥራት እየቻሉ የማይሰሩ፣ ማገልገል እየቻሉ የማያገለግሉ ብዙዎች ናቸው። መቻል ብቻውን ሥራ አይሠራም፡፡ መፍቀድ ወይም የፈቃድ ኃይል ያስፈልጋል፡፡ ከአምስት መንገዶች በአንዱ መግባት አለመቻል፣ ሳይሞክሩ በፍርሃት መቀመጥ ዛሬ ሊሰበር ይገባዋል፡፡
የውኃው መንቀሳቀስ
ውኃው ሲንቀሳቀስ ወይም ሲናወጥ ወዲያው መግባት የፈውስ ዕድልን ያስገኝ ነበር፡፡ ሕመም የተለያየ ነው፡፡ ዛሬ ለአገልጋዮች ትልቁ ሕመማቸው የወገናቸው መዳን ነው፡፡ ወገናቸው ቃሉን ለመስማት ሲንቀሳቀስ ፈጥነው መግባትና ከዚህ ጭንቀት መፈወስ አለባቸው፡፡ ካልተንቀሳቀሰ ፈውስ የለም፡፡ ሲንቀሳቀስ ግን ፈውስ አለ፡፡ የሕዝብ ለወንጌል መንቀሳቀስ የአገልጋዮችም ፈውስ ነው። ሕዝብን የሚያንቀሳቅስ እግዚአብሔር ነው። የተንቀሳቀሰውን ሕዝብ ማገልገል አለብን። አሊያ ሃይማኖት የሚመስሉ ብዙ የፋሽን ተቋማት ሕዝቡን በድፍርስ ውሃ ይበክሉታል። የራበው ምግብ አይመርጥምና ሕዝቡ በትምህርት ብክለት እንዳይጠፋ ማሰብ ይገባናል።  
መጀመሪያ መግባት
የቤተ ሳይዳ ፈውስ ለአንደኞች የሚሰጥ ሽልማት ነው፡፡ የጌታ ፈውስ ግን ለሠርክ እድምተኞችና ለማታ ተማሪዎችም የሚሆን ነው /ማቴ. 20፡1-16/፡፡ በእግዚአብሔር ቤት በልጅነታችን ተጠርተን ከሆነ መልካም ነው፡፡ ብዙ ዘመን በዓለም ካሳለፍንም እግዚአብሔር በረከቱን ለአንደኞች ሳይሆን ለአማንያን አዘጋጅቷልና ቶሎ እንግባ፡፡
ሠላሣ ስምንት ዓመት
ለበሽተኛ ትንሹ ደቂቃ የዓመት ያህል ያስጨንቀዋል፡፡ የሥቃይ ሰዓት ረጅም ነው፡፡ ይህ ሰው በዚህ ሁሉ ዘመን አንድ ቦታ ላይ ተቀምጦ አንድ ነገርን እያየ ይኖራል። ብዙዎች መጥተው ተፈውሰው ይሄዳሉ፣ እርሱ የሰውን ፈውስ ቆጣሪ እንጂ የራሱን ፈውስ ተመልካች አልነበረም፡፡ ሠላሣ ስምንት ዓመት ወረፋ ቢይዝም ሰዎች እርሱ ይቅደም አላሉም ነበር። የሰው ራስ ወዳድነት በዚህ ሰው ይታያል። ጌታ ግን ደረሰለት፡፡ ሰዎች ባያዝኑልን የሚያዝንልን አምላክ አለ፡፡ ወደ ፈዋሹ ውኃ መሄድ ባንችል የሚፈውሰን አምላክ እስከ አልጋችን መጥቶ ይዳብሰናል፡፡
የሰው ረሀብ
እስረኛ፣ በሽተኛ፣ ስደተኛ ሰው ይርበዋል፡፡ ሰላምታ የሚሰጠው፣ በፍቅር የሚቀበለው ሰው ይርበዋል፡፡ አለመፈለግ ሕመም አለው፡፡ ይህ ሰው – ሰው የለኝም እያለ ኖሯል፡፡ አሁን ግን ክርስቶስ ሰው ሆኖ ሰው ሊሆነው መጣለት፡፡ ሰው የለኝም ለምንል ክርስቶስ ሰው ሆኖ መጥቷልና እስቲ እባካችሁ አሁን አመስግኑት፡- የእኔ ሰው አንተ ነህ። ሰው ራቀኝ ሰው ረሳኝ ብዬ ላላዝን ቃል እገባልሃለሁ። ሁሉን የምትሆንልኝ አንተን ፈውሴ ጌታዬ ብዬ አመሰግንሃለሁ።  
ሰው በሰው ሆኖ ሲጠቃቀም
እኔ የምጠራው ያላንተ የለም
አልጋን መሸከም
ያ በሽተኛ አልጋው ሠላሣ ስምንት ዓመት ያለማጒረምረም ተሸክሞታል፡፡ አሁን ዳግም ተራ መጣ፡፡ አልጋውን ለመሸከም በቃ፡፡ ሠላሣ ስምንት ዓመት የተኛ በሽተኛ ትንሽ ማገገም ያስፈልገዋል፡፡ ጌታ ግን ሲፈውስ ማገገም የለበትም፡፡ ስለዚህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው። ለብዙ ዘመናት የተሸከሙንን የምንሸከምበት ቀን ይመጣል፡፡ ያሳደጉንን፣ ያስተማሩንን መሸከም ተራውን መቀበል እውነተኛ ፈውስ ነው፡፡
ወገኖቼ ዛሬ በጤና ውለን ከሆነ እግዚአብሔር ይመስገን። ጤና ብናጣ ኖሮ ለካርድ፣ ለምርመራ፣ ለመድኃኒት ምን ያህል እናወጣ ይሆን? ይህንን ወጪ ዛሬ ለታመሙት በማዋል እግዚአብሔርን እናክብር። በበሽታ ላይ ረሀብ የሚጫወትባቸው ችግር የደፈራቸው ስንት ወገኖች አሉና እናስባቸው፡፡ ልብ አድርጉ፡- እግዚአብሔር የእኛን ደስታ ያስቀመጠው በሌሎች ጉድለት ውስጥ ነው፡፡    
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ