ወዳጄ ሆይ !
ጆሮ እያለው የማይሰማ ሳያውቅ ያወቀ የሚመስለው ነው ። ተምሮ የደነቆረና ያወቀ የሚመስለው አንድ የሚሆኑት በጥፋታቸው ነው ። ጠላት ገንዘብህን ይውሰድ እንጂ ሰብእናህን እንዲወስድ አትፍቀድለት ። መሻገርህን ሳታረጋግጥ ድልድዩን አትስበር ፣ መውጣትህን ሳታረጋግጥ መሰላሉን አትገፍትረው ። ያሻገርህንና ከፍ ያደረገህን ወገን አትርሳው ። ደራሽ ውኃ ሲመጣ ዋና መለማመድ ከንቱ ነው ። ሊሄድ የፈለገን ቆይ አትበለው ፣ አካሉ ቢቀመጥም ልቡ ሂዷልና ። ለመሻገር የፈለከው ድልድይ ለመመለስ ፣ ለመውጣት የፈለከው መሰላል ለመውረድም ያስፈልጋል ። የሄደም መመለሱ ፣ የወጣም መውረዱ አይቀርምና ሁልጊዜ በትዕግሥት ኑር ።
ወዳጄ ሆይ !
ከእግዚአብሔርና ከቃሉ ውጭ እርግጠኛ የምትሆንበት ነገር በዓለም ላይ የለም ። የተራራቁትን የሚያገናኝ ፣ የተዋረዱትን ከፍ የሚያደርግ ሰው ቡሩክ ነው ። ድልድይና መሰላል ባለውለታ ቢሆኑም በእግር መረገጣቸው ግን ይገርማል ። ስትጀምር እግርህን የገፋልህንና ስትጨርስ እጁን የዘረጋልህን አትርሳ ። ለእውነተኛ ወዳጅህ ጊዜ ካጣህ መኖርህ የባከነ ነው ። መፈራራት ባለበት ፍቅር እውነተኛ አይደለም ።
ወዳጄ ሆይ !
የራስህን ምሁር በባዕድ መሃይም አትቀይረው ። ያወራኸው ነገር ከልብህ እያለቀ ይመጣልና ፍቅርህንና እቅድህን አትለፍልፈው ። የወጣልህን ሎቶሪ ሳታረጋግጥ አሮጌ ልብስህን አታቃጥል ። በወረት ፍቅር የከረመ ወዳጅህን ገሸሽ አትበል ። መሬትን ለቆ የበረረ መልሱ ማረፉ አይቀርም ፣ በወረት ፍቅር ያበደም እያፈረ መምጣቱ ግድ ነው ።
ወዳጄ ሆይ !
መጽሐፍ በሽፋን ፣ ሰው በአንድ ቀን አይታወቅም ። ሁሉም ቤት ታሪክ አለ ፣ የመዘገቡት ግን ታሪክ ይሆንላቸዋል ። አብዛኛው የዓለም ታሪክ የመገዳደል ታሪክ ነውና ቃየን ብዙ ልጆች አፍርቷል ። የተቀደደ የለበሰን ብትገፈው የምታጌጠው በተቀደደ ልብስ ነው ፣ ድሀን ዘርፈው ባለጠጎች የሆኑም ሲያፍሩ የሚኖሩ ናቸው ። እግዚአብሔር መስረቅን በትእዛዙ ሲከለክልህ ፣ መብላትን ግን በፍርድ ያግድሃል ።
ወዳጄ ሆይ !
ጠላት እንዳይገዛብህ እሳት ልጅህን ያዘው ፣ ወዳጅ እንዲያመጣልህ ውኃ ልጅህን ላከው ። ካልቸገረህ በቀር ከሞኝ ጋር አትጣላ ። ምግብ ያለ ውኃ ፣ ትምህርት ያለ ቅንነት ፣ ጀግና ያለ ደጀን ጥቅም የላቸውም ።
ወዳጄ ሆይ !
ያለ አቅምህና ያለ ችሎታህ ትልቅ ስድብ ከሰደቡህ እያሞኙህ ነው ። ለአቅመ መሰደብ መድረስህን ሳታረጋግጥ ሰደቡኝ ብለህ አትዘን ። በተስፋ ብቻ ከጎለቱህ በጦር ያባረሩህ የተሻለ ቦታ ያደርሱሃል ። በየሄደበት ቃል የሚገባ ካልሰጠ የሚወደድ የማይመስለው ሰው ነው ። ያልተሰጠህን ስትፈልግ የተሰጠህን ታጣለህ ። ያልደረስክበትን እውቀት ስህተት ነው ለማለት አትቸኩል ፣ የደረስክበትን ስህተት እንዳይደናቀፉ ለማያውቁ አሳውቅ ።
ወዳጄ ሆይ !
ከሚንጫጫ ብዙ ፣ ዝም ያለውን አንድ ሰው ፍራ ። ከሚጮኸው ውሻ ፣ የማትጮኸው ግመል ብዙ በረሃ ታቋርጣለች ። በብዕር መነጋገር ካልቻልን በጥይት እንነጋገራለን ። ያነበበ ቢተኛ እንኳ ነቅቶ የተኛ ነው ። ሳታነብ ሰው ሁሉ ከሚወድህ አንብበህ ብቸኛ ብትሆን ይሻላል ። ማንበብ የነፍስ ምግብ ፣ መጻፍ ግን የነፍስ ትግል ነው ይባላል ። ዛሬ ግን የሚታገሉት ቀርቶ የሚመገቡት ደከማቸው ።
ሰላማዊ ዘመን እዘዝልን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 20 ቀን 2013 ዓ.ም.