ሐሙስ ፣ ሰኔ ፳፮1 ፳፻፮ ዓ.ም.
አንድ ሰው ፡- “ይህች ወኅኒ ዓለም አንድ መስኮት አላት፤ ይህም መስኮት ዘላለማዊነትን የምናይበት መጽሐፍ ቅዱስ ነው” ብሏል፡፡ ይህ ዓለም የግዞት ቤታችን ወይም ትልቅ እስር ቤት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ነፍስ በሥጋ አላዋቂነት ታስራለች፣ መንፈስ በዓይን ውሱንነት ተለጉማለች፡፡ በዚህች ወኅኒ ዓለም ባሻገር የምናይበት መስኮት፣ ከሞት በኋላ ያለውን ዓለም የምንጐበኝበት ማሳያ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ሕይወት በዚህ ዓለም ላይ የምናሳልፈው ኑሮ ብቻ ቢሆን በእውነት ኀዘኑ መጽናናት፣ ጉዳቱም ካሣ የሌለው በሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን ከሞት በኋላ ሕይወት አለ፡፡ ይህን የሚነግረንም መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ላለፉት ሦስት ሺህ ዓመታት የሰው ልጆች የቅርብ ጓደኛ፣ የሕይወት መስተዋት፣ የመንገድ ካርታ፣ አቅጣጫ ጠቋሚ (ኮምፓስ) በመሆን ያገለገለ ብቸኛ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን እንደሚገልጠው ዘመን የማይሽረው ዘላለማዊ ቃል ነው፡፡ (ማቴ.24&35፤ ኢሳ. 51&6፤48&8፤ 1ኛ ጴጥ. 1&23-25)፡፡
ሦስት ሺህ ዓመታትን ያህል የተነበበ መጽሐፍ የለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ለሦስት ሺህ ዓመታት በእምነት ተነቧል፡፡ በዚያ ዘመን የነበረውን ሰውና የዛሬውን ስልጡን ሰው፣ የትኛውንም የኑሮ ደረጃ የሚመጥን መጽሐፍ ቢኖር መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ዛሬም እንደ ንጋት የትርጉሙ ፍካት ይወጣል እንጂ ብርሃኑ አይደበዝዝም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሐቅ መጽሐፍ ስለሆነ የሰዎችን ብርታት ብቻ ሳይሆን ድካማቸውንም በግልጽ በማስፈሩ ከሌሎች አዋልድ መጻሕፍት ልዩ ያደርገዋል፡፡ የሰው ልጆች ተስፋ የሆነውን የደካሞችን ታሪክ በመያዙ እና የድካሙን መፍትሔ በመግለጡ ነው፡፡ ስለ ሰው ፍጽምና የሚናገሩ መጻሕፍትን ማንበብ አንባቢው ይህን ፍጽምና ስለማይደርስበት ተስፋ እንዲቆርጥ ያደርጉታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ሰውን ሰው ብቻ የሚል፣ ቢወድቅም የንስሐን ዕድል የሚያሳይ፣ ኃጢአተኞችን አድራሻ ያደረገ መጽሐፍ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በ1500 ዓመታት ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያው ጥራዝ እና የመጨረሻው ጥራዝ የ1500 ዓመታት ክፍተት አላቸው፡፡ ፀሐፊዎቹም በተለያየ ዘመንና ቦታ የኖሩ ዐርባ የሚያህሉ ናቸው፡፡ በ15ዐዐ ዓመታት የዘመን ርቀትና በተለያየ የኑሮ ጠባይ በኖሩ ዐርባ በሚያህሉ ሰዎች ቢጻፍም መጽሐፉ እርስ በእርሱ አይጋጭም፡፡ ለምን? ስንል የመጽሐፉ ደራሲ ሰዎች ሳይሆኑ መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ነው፡፡
በ1456 ዓ.ም በጀርመናዊው በጆሐን ጉተንበርግ የሕትመት መሣሪያ ከመፈልሰፉ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ በጻሕፍት አማካኝነት በእጅ እየተገለበጠ ይባዛ ነበር፡፡ ይህም ለ1500 ዓመታት ያህል በትጋት ተሠርቷል፡፡ ጻሕፍቱም በዕብራይስጡ “ያህዌ“ የሚለው የእግዚአብሔር ስም ጋ ሲደርሱ መሬት ላይ ወድቀው ይሰግዱ፣ እጃቸውን ታጥበው “ያህዌ” የሚለውን ስመ አምላክ ይጽፉ ነበር፡፡ በትክክል የጻፉአቸውን ለማወቅም መላው ብሉይ ኪዳንን በፊደል ቆጥረውት ስለ ነበር ከቁጥሩ አንድ ከጐደለ እንደገና ይጽፉ ነበር፡፡ እንዲህ ባለ ክብር እና ጥንቃቄ እንዲጽፉ ያደረገ ምንድነው ስንል መጽሐፍ ቅዱስ አምላካዊ ጥበቃ እንደ ተደረገለት ያሳየናል፡፡ /በአገራችን በጎንደር ዘመነ መንግሥት ቅዱሳት መጻሕፍት እንዲህ ባለ ታላቅ ጥንቃቄ ይጻፉ ነበር፡፡ ሊቃውንቱ ወፍ ጭጭ ከማይልበት ቦታ ተቀምጠው፣ የጽሑፍ እንቅፋት የሆነው የመብል አሳብ እንዳይገባባቸው ብርዝ እየተበጠበጠ፣ ማለፊያ ምግብ እየተሰናዳ ይጽፉ ነበር፡፡ የአጻጻፉም ምድብ አምስት ነበር፡፡ አንደኛው ምድብ፡- ብራና ዳምጦ ሰሌዳ ያዘጋጃል፤ አዘጋጅቶም ወደሚጽፉት ያስተላልፋል፡፡ ሁለተኛውም ምድብ፡- ብዕር ቀርጾ፣ ቀለም በጥብጦ ፊደል ይጽፋል፡፡ ጽፎም ወደ እርምት ክፍል ያስተላልፋል፡፡ አራሚዎችም በጥንቃቄ ዐርመው ለአራተኛው ምድብ ይሰጣሉ፡፡ ዐራተኛው ምድብም፡- ጥራዞቹን ሰብስቦ የሚሰፋ ሲሆን የስፌት ክፍልም ለድጉሰት ክፍል ይሰጣል፡፡ የድጉሰት ክፍልም መጻሕፍቱን ደጉሶ ወደ ቤተ መጻሕፍት ይመራል፡፡ ታዲያ ፀሐፊው ፊደል ከገደፈ፣ በንጉሡ ‹‹ሠ›› የሚጻፈውን በእሳቱ ‹‹ሰ›› ከጻፈ ጣቱ ይቆረጥ ነበር ይባላል፡፡/
በሙት ባሕር ከተገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅልሎች አንዱ
በ1947 ዓ.ም በሙት ባሕር አካባቢ ከብት ይጠብቅ የነበረ አንድ የዐረብ እረኛ በማሰሮ ውስጥ የተቀመጡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ቁርጥራጮችን አግኝቷል፡፡ ከመጽሐፈ አስቴር በቀር ሁሉንም የብሉይ ኪዳን ክፍሎች በቁራጭ ተገኝተዋል፡፡ እነዚህ ጥንታዊ ጽሑፎች በክርስቶስ ዘመንና ከክርስቶስ ዘመን በፊት የተጻፉ የብሉይ ኪዳን ቅጂዎች ናቸው፡፡ እስከ 1947 እ.ኤ.አ የነበሩት ጥንታውያን ቅጂዎች አንድ ሺህ ዓመታት ያስቆጠሩ የማሶሬቶች ቅጂ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ቅጂዎች ጋር በሙት ባሕር አካባቢ የተገኙትን በተለይ የኢሳይያስን የትንቢት መጽሐፍ ለማስተያየት ተሞክሮ በሙሉ አንድነት ተገኝቶበታል፡፡ በዚህም ሁለት ጥርጣሬዎች መልስ አግኝተዋል፡፡
1. መጽሐፍ ቅዱስ በልዩ ጥንቃቄ የተገለበጠና የትርጉም ፍልሰት እንዳይደርስበት አምላካዊ ጥበቃን ያገኘ መጽሐፍ መሆኑን፣
2. በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተነሡ አንዳንድ ተቺዎች መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናት ርዝመት በቋንቋዎችና በኮፒዎች ሽግግር የመጀመሪያ መልእክቱን ስቷል በማለት ለሚሰጡት ሂስ መልስ ሆኗል፡፡
በዓለም ላይ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጠላቶችን ተቋቁሞ የኖረ መጽሐፍ አይገኝም፡፡ ጠላቶቹም ተራ ሰዎች ሳይሆኑ ነገሥታትና ጳጳሳት፣ ፈላስፎችና ከሃድያን ነበሩ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ለዓለም የተሰጠው በእስራኤል በኩል ነው፡፡ እስራኤል ደግሞ መጽሐፉን ለቤተ ክርስቲያን ስታስረክብ በመውደም፣ በፍልሰት የተጐዳች አገር ናት፡፡ እስራኤል ሦስት ጊዜ ፈርሳ ሦስት ጊዜ ተሠርታለች፡፡ እስራኤል ስትፈርስ መጻሕፍቱም አብሮ የመቃጠልና የመማረክ ዕድል ገጥሟቸዋል፡፡ ስለዚህ በባቢሎን ምርኮ (በ586 ቅድመ ክርስቶስ) መጽሐፍ ቅዱስ ጥቃት ደርሶበታል፡፡ በሰባ ዓመተ ምሕረት የኢየሩሳሌምና የታላቁ መቅደስ መቃጠልም የመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥተኛ ጉዳት ነበረ፡፡ በሐዋርያት ዘመንና ከሐዋርያት ዘመን በኋላ የተነሡ መናፍቃን መልእክት ባልፃፉ ሐዋርያት ስም “የእገሌ ወንጌል” በማለት ፍጹም የኑፋቄ መጻሕፍትን ለማስገባት ሞክረዋል፡፡ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተሰነዘረ ቀጥተኛ ጥቃት ነው፡፡ ብዙ ዘመን ተሻግረን በ1526 ዓመተ ምሕረት ዊልያም ቲንዴይል መጽሐፍ ቅዱስን በእንግሊዘኛ ቋንቋ በመተርጎሙ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፉ ክብር በቋንቋ ሽግግር የጠፋ በማስመሰል በ1536 ዓ.ም በእሳት ተቃጥሎ እንዲገደል አድርጋለች፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ተከታዮቹን ብቻ ሳይሆን ራሱንም ለመከራ ያዘጋጀ መጽሐፍ ቢሆንም ጳውሎስ ያለው ግን ጸንቶ ይኖራል፡፡ መልእክተኞቹን እንጂ መልእክቱን ማሰር አይቻልም (2ጢሞ.2&9)፡፡
በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተነሡ ብዙ ፈላስፎችም፡- “መጽሐፍ ቅዱስ ከእንግዲህ ወዲህ የሚያነበው የለም” ብለው ነበር፡፡ በሚገርም ሁኔታ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ከቤተ መቅደስ ንብረትነት ወጥቶ የእያንዳንዱ ሰው የግል ሀብት ደግሞም የቅርብ ጓደኛ የሆነው ከእነዚህ ጠቢባን ነን ባዮች ንግግር በኋላ ነው፡፡ በአሁን ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ ከ2800 ቋንቋዎች በላይ ተተርጉሟል፡፡ ይህንን ያህል የቋንቋዎች ሽፋንና የሕትመት ብዛት ያገኘ ከመጽሐፍ ቅዱስ በቀር ሌላ መጽሐፍ የለም፡፡ በዓለም ላይ በሚገኙ ደረጃቸውን በጠበቁ ሆቴሎች መጽሐፍ ቅዱስ በእንግዳ ማረፊያ ክፍል ይቀመጣል፡፡ የክርስቲያን ደሴት በተባለችው በኢትዮጵያ ግን በማደሪያ ክፍል መጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን የኃጢአት መሣሪያ ነው የሚቀመጠው፡፡ ይህ የሚያሳዝን ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች ሥጋዊና መንፈሳዊ ድርሰቶች ልዩ የሚያደርገው የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ መሆኑ ነው (2ኛ ጢሞ. 3&16፣ ዮሐ. 6&63)፡፡ ስለዚህ ፊደል ሳይሆን ሕይወት ሰጪ ቃል ነው(2ኛ ቆሮ. 3&6)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች መስክሯል፤ ሰዎችም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ አሳታሚዎች መልእክት በየትርጉም መጻሕፍት የመጀመሪያ ገጽ ላይ ብንመለከት የሕይወት ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ እነዚህ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እያፈሰሱ የሚያሳትሙት ዓለም አቀፍ ማኅበራትና የትርጉም ሥራ ድርጅቶች መጽሐፉን በመደጋገም ከዘለቁት በኋላ የሰጡት ምስክርነት የማይታበል ነው፡፡ ለምሳሌ፡- አንዱን ብንመለከት፡-
“መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን አሳብ፣ የሰውን ሁኔታ፣ የደኅንነትን መንገድ፣ የኃጢአተኞችን ፍርድና የምእመናንን ደስታ ይዟል፡፡ ትምህርቱ የተቀደሰ ነው፤ ሕግጋቱም የጸኑ ናቸው፤ ታሪኩም እውነት ነው፣ ፍርዱም አይናወጥም፡፡ ጠቢብ ትሆን ዘንድ አንብበው፣ ትድን ዘንድ ጠብቀው፡፡ የሚበራ መብራት፣ የሚደግፍህ ምግብ፣ የምትደሰትበትም መጽናኛ አለው፡፡
የመንገደኛ ካርታ፣ የመናኝ ምርኩዝ፣ የአውሮፕላን ነጂ መመሪያ፣ የወታደር ሰይፍ፣ የክርስቲያን ሕግ ነው፡፡ በዚህም ገነት ይገኛል፣ መንግሥተ ሰማያት ይከፈታል፣ የገሀነም ደጆች ይዘጋሉ፡፡ ዐቢዩ መልእክት ክርስቶስ፣ ዕቅዱ የእኛ ደኅንነት፣ ግቡም የእግዚአብሔር ክብር ነው፡፡
የማስታወስ ኃይልን ይሞላ ዘንድ፣ ልብን ይገዛ፣ እግሮችንም ይመራ ዘንድ ይገባል፡፡ አዘውትረህ በዝግታና በጸሎት አንብበው፡፡ የሀብት ማዕድን፣ የክብር ገነት፣ የደስታ ወንዝ ነው፡፡ በሕይወት ሳለህ ተሰጥቶሃል፣ በፍርድ ቀን ይከፈታል፣ ለዘላለምም ይታወሳል፤ ከፍተኛውን ኃላፊነት ያስከትላል፣ ለታላቅ አገልግሎትም ዋጋ ይሰጣል፣ ቅዱስ ትእዛዛቱንም የሚያቃልሉትን ሁሉ ይከùንናል፡፡” ይላል፡፡
የአሜሪካ 16ኛ ፕሬዝዳንት የነበሩት አብርሃም ሊንከን፡- “መጽሐፍ ቅዱስን በማንበቤ ብዙ አትርፌአለሁ እስቲ አንተም በመንፈስና በእምነት ተሞልተህ አንብበው፤ በሕይወት ዘመን ሁሉ የተሻለ ሰው ሆነህ ትኖራለህ፣ እንደ ተከበርህም ታልፋለህ” ብለዋል፡፡ አንድ ሰውም፡- “መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አእምሮንና መንፈስን ወደሚያድስ ለምለም ስፍራ እንደ መጓዝ ነው” ብለዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ትውልድን የሚሠራ መጽሐፍ መሆኑን ፕሬዝዳንት ቶማስ ጃፈርሰን፡- “መጽሐፍ ቅዱስ ዜጐችን በሙሉ ቀና ያደርጋል፡፡ ባሎች የተሻሉ፣ ጨዋና ከሁሉም በላይ ደግሞ ደግ አባት እንዲሆኑ ይረዳቸዋል” በማለት ገልጸዋል፡፡
ይቀጥላል