የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መጽሐፍ ቅዱስ / ክፍል ሦስት

                                                                                 የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ               እሑድ፣ ሰኔ  29 2006 ዓ/ም
             የተለየ መጽሐፍ
መጽሐፍ ቅዱስ የዚህ ታላቅ ፍጥረተ ዓለም አስገኚ የሆነውን እግዚአብሔር በክብርና በፍቅር ይገልጠዋል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው ክፍል ብሉይ ኪዳን እግዚአብሔርን በክብርና በግርማ፣ በብዙ ሞገስና የኃጢአትን ቅጣት በሚሰጥ ጻድቅነት ያብራራዋል (ዘፀ. 34፡6-7)፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ሁለተኛው ታላቅ ክፍል ዐዲስ ኪዳን ደግሞ እግዚአብሔርን በፍቅሩ፣ በርኅራኄውና በቅርብ አባትነቱ ይገልጠዋል (ማቴ. 6፡9፤ ዮሐ.1፡18፤ሮሜ. 8፡15)፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ከአንድ ታላቅ ሰማያዊ አባት ለምድራዊ ልጆቹ የተላከ የፍቅር መልእክት ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ታሪክ፣ ስለ ሳይንስ፣ ስለ ፍልስፍና፣ ስለ መልክአ ምድር፣ …  የሚናገር መጽሐፍ ቢሆንም የሳይንስ ወይም የታሪክ መጽሐፍ ግን አይደለም፡፡ ሰዎች ከቆሙበት ዓላማና ሙያ አንጻር የመጽሐፍ ቅዱስን ምስክርነት ቢጠቅሱና አጋር ቢያደርጉትም የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ ዓላማ ግን ድኅነተ ነፍስ የተፈጸመበትን የዓለም ሁሉ ቤዛ የሆነውን ክርስቶስን መስበክ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ማለት ትርጉሙ የተለየ መጽሐፍ ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ ከሚገኙት በሚሊየን ከሚቆጠሩ የታሪክ፣ የፍልስፍና፣ የሥነ ልቡና፣ የሕግ … መጻሕፍት የተለየ የሚያደርገው ምንድነው ስንል፡-
1.  እስትንፋሰ እግዚአብሔር መሆኑ
መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡  ቋንቋውና ዘይቤው የሰው ልጆች ቢሆንም አሳቡ ግን የእግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ፈቃዱን ያሳወቀው በመጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ የተለያዩ መጻሕፍቶች እንዲሁም የሥነ ፍጥረት ምስክርነት ስለ እግዚአብሔር አጠቃላይ ግንዛቤ ይሰጡናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በልዩ መገለጥ የእግዚአብሔርን አሳብና ፈቃድ ይነግረናል፡፡ ይህ አሳቡና ፈቃዱም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ማዳን ነው (2ጢሞ. 3፡15)፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር አፍ የወጣ የአፉ ቃል ወይም የእስትንፋሱ ቊራጭ ነው፡፡ ጌታችን፡- “… ከእግዚአብሔር አፍ የሚወጣ…” በማለት ገልጾታል (ማቴ.4፡4)፡፡ ጳውሎስም፡- ‹‹የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ›› ይለዋል (2ጢሞ. 3፡16-17)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር መንፈስ (እስትንፋስ) ያለበት መጽሐፍ ነው፡፡ ሕይወትን ዓላማ ያደረገ፣ በድንቊርና ጨለማ ለሚኖሩ የዕውቀት ብርሃንን የሚሰጥ፣ በሀዘን ዋሻ ለተቀመጡም የደስታን አምባ የሚያወርስ ነው፡፡ እስትንፋስ ወይም ቃል ከልብ ሳይለዩ ከልብ እንደሚወጡ መጽሐፍ ቅዱስም የእግዚአብሔር የአሳቡ ማብራሪያ ነው፡፡ እስከ አሁንም የመለኮት ኃይል ያልተለየው ሕያው ቃል ነው፡፡


2.  ጊዜ የማይሽረው ቃል መሆኑ
ዕውቀት በዕውቀት በሚሻርበት ዓለም ላይ እንኖራለን፡፡ ዘመናዊነትም የሰው ልጅ ያለውን በቅጡ ሳይጠግብ ሌላ የሚፈልግበት ወረተኛነት ሆኗል፡፡ በዚህ ሹም ሽረት በበዛበት፣ ወረት ባጠቃው ዓለም ላይ ዘላለማዊው የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ዘመናዊ ሳይሆን ዘላለማዊ ነው፡፡ ጊዜ ከፍታዎችን ዝቅታ፣ ዝቅታዎችን ከፍታ ሲያደርጋቸው ዐይተናል፡፡ ገናም ለማየት  እንኖራለን፡፡ የማለፍን ሕግ የሚቋቋም መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡ ከዘላለማዊው እግዚአብሔር የወጣ ቃል በመሆኑ ዘላለማዊ ነው፡፡ ታሪኩ ይመክራል፣ ተግሣጹ ይመልሳል፣ ምክሩ ያሳርፋል፣ ትምህርቱ ያበራል፣ ማጽናናቱ ያቆማል፡፡ ጌታችን፡- “ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም” (ማቴ. 24፡35) ብሏል፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስም ከኢሳይያስ በመጥቀስ፡- “ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤ ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤ የጌታ ቃል ግን ዘላለም ይኖራል” ብሏል (1ጴጥ. 1፡24-25፣ ኢሳ. 40፡6-9)፡፡
3.  የሚለውጥ ኃይል መሆኑ
ባለንበት ዘመን ስለ ለውጥ ብዙ ይነገራል፡፡ ሰው በባሕርይው ላይ የበላይ መሆን ስላልቻለ የሞራል ውድቀቶች እየበዙ፣ ሰው እንስሳዊና አራዊታዊ ባሕርያትን እየተላበሰ ነው፡፡ ለውጥ አስፈላጊ መሆኑ ቢታመንበትም በምን እንደሚለወጥ ግን የሰው ልጅ አላወቀም፡፡ የሰው ልጅ በራሱ የለውጥ ፍላጎት እንጂ ኃይል የለውም፡፡ እግዚአብሔር ግን በወንጌል ውስጥ የሚለውጥ ኃይልን አስቀምጧል፡፡ “በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግምም ለግሪክ ሰው ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና” (ሮሜ. 1፡16)፡፡
ወንጌል የማያሳፍር መሣሪያ ነው፡፡ እነጳውሎስ አላፈሩበትም፣ ዛሬም ቤተ ክርስቲያን አታፍርበትም፡፡ ስንቶች ከኃጢአት ቀንበር ሲላቀቁ፣ ከሱስ ጨለማ ሲወጡ፣ ከአጋንንት እስራት ሲፈቱ በዓይናችን እያየን ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሰዎች የሚታነጹበት (የሚሠሩበት) መዶሻ ነው፡፡
እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለው ዓላማ ነፍሳችንን ማዳን ብቻ ቢሆን የዳንን ቀን ይሰበስበን ነበር፡፡ የዓላማው አንዱ ክፍል ግን ተለውጠን ሌሎችንም እንድንለውጥ ነው፡፡ የሰው ሕንፃ መሥራት ከባድ ቢሆንም ለመጽሐፍ ቅዱስ ግን ተችሎታል፡፡ አንድ ሰው፡- “መሐንዲስ ጠዋት ላይ ወደሚያሠራው ሕንጻ ሲሄድ የተሠራውን ሳይሆን ያልተሠራውን ያያል፡፡ እግዚአብሔርም በቃሉ የተሠራውን ሳይሆን ያልተሠራውን ማንነታችንን ይነግረናል፡፡” ብሏል፡፡    
4.   የዘላለም ሕይወትን ስለሚሰብክ
የሕይወት ጅማሬና ግቧ እዚሁ ምድር ላይ ቢሆን አሳዛኝ በሆነ ነበር፡፡ ሕይወት ግን በሰማይም ትቀጥላለች፡፡ ይህ ዓለም ማቋረጫ መንገድ እንጂ መኖሪያ እንዳልሆነ በየዕለቱ በሞት የሚጠሩት ወገኖቻችን ይሰብኩናል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ የሚሰነብት እንጂ የሚቀር የለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ዋስትና ይሰጠናል፡፡
ከእስልምና ወደ ክርስትና የተመለሰ አንድ የእስልምና ሃይማኖት አዋቂ ሲመሰክር፡- “መጽሐፍ ቅዱስን ወድቆ ያገኘሁት መርከብ ውስጥ ነው፡፡ አንሥቼ ሳነበው ዮሐንስ 17 ላይ፡- ‹በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው› የሚለውን ለመጀመሪያ ጊዜ ሳነብ ልቤ ስንጥቅ አለ፡፡ ቀጥሎ ወደኋላ ስገልጥ፡- ‹በወልድ ያመነ የዘላለም ሕይወት አለው› የሚል ቃል ሳይ በምድር ላይ ስለ ሰማይ ዋስትና የሚሰጥ ሃይማኖት አለ ወይ; ያለሁበት ሃይማኖት የነፍሴን መዳን መመለስ ስላልቻለ በጣም እጨነቅ ነበር፡፡ ሕይወት እንዳለኝ ሳነብ ክርስቲያን ሆንኩ” ሲል ሰምቻለሁ፡፡
በእውነትም በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጸው ክርስትና ውጭ የዘላለም ሕይወት ዋስትናን በጽኑነት የሚሰብክ ሃይማኖት የለም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅል አሳብ ተብሎ የሚጠራው ቃልም “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና” የሚለው ነው (ዮሐ. 3፡16)፡፡
 
5.   የትንቢት እውነት ያለው ስለሆነ
ከእግዚአብሔር በቀር ነገን የሚያውቅና ስለ ነገ በእርግጠኝነት የሚናገር ማንም የለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የዛሬ ትምህርት ብቻ ሳይሆን ነገንም የሚያሳይ መስተዋት ነው፡፡ እውነተኛ ትንቢቶቹም በዘመን ተፈትነዋል፡፡ የእውነተኛው አምላክ ቃል እንደሆነም አስመስክሯል፡፡
ብሉይ ኪዳን ብዙ የትንቢት አንቀጾችን ይዟል፡፡ አብዛኛዎቹ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ ምጽአት ፍጻሜ አግኝተዋል፡፡ ጌታችን፡-
         በድንግልና እንደሚጸነስ (ኢሳ. 7፡14፤ ማቴ. 1፡23)
         በቤተ ልሔም እንደሚወለድ (ሚክ. 5፡2፤ ማቴ. 2፡5-6)
         ወደ ግብጽ እንደሚሰደድ (ሆሴ. 11፡1፤ ማቴ. 2፡15)
         በናዝሬት እንደሚያድግ (ማቴ. 1፡23)
         በባሪያ እጅ እንደሚጠመቅ (ኢሳ. 40፡3፤ ማቴ. 3፡3)
         በሠላሣ ብር እንደሚሸጥ (ማቴ. 27፡9)
         እንደሚሞት (ኢሳ 53፤ 1ጴጥ. 2፡24)
         በአብ ቀኝ እንደሚቀመጥ (መዝ. 109፡1፤ ዕብ. 1፡13) … የተነገረው ትንቢት በመጀመሪያው መምጣቱ ተፈጽሟል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዘመን መጨረሻም ብዙ የትንቢት ቃሎችን ይዟል (ማቴ. 24)፡፡ እነዚህም ትንቢቶች በዘመናችን ቃል በቃል ሲፈጸሙ እያየን ነው፡፡ ይህም መጽሐፍ ቅዱስ  አምላካዊ ቃል መሆኑን ያስረዳናል፡፡ አስተውሉ! መጽሐፍ ቅዱስ የተለየ መጽሐፍ የተባለው እስትንፋሰ እግዚአብሔር መሆኑ፣ ጊዜ የማይሽረው ቃል መሆኑ፣ የሚለውጥ ኃይል መሆኑ፣ ደግሞም የዘላለም ሕይወትን የሚሰብክልን የተንቢት እውነት ያለው በመሆኑ ነው፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ