የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መጽሐፍ ቅዱስ /ክፍል ሰባት/

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ                                             ቅዳሜ   ሐምሌ 26/2006 ዓ/ም

የአዲስ ኪዳን ጥናት በቅኝት መልክ
አዲስ ኪዳን ማለት አዲስ ውል አዲስ ስምምነት ማለት ነው፡፡ ለምን አዲስ ኪዳን ተባለ ስንል ፊተኛውን ኪዳን አስረጅቶ ስለገባና የዘላለም ኪዳን ስለሆነ ነው (ዕብ. 8፥13፤ 1፥1-2)፡፡ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር አዲስ ኪዳን እንደሚገባ አስቀድሞ በነቢያት ተናግሯል (ኤር. 31፥31-34፤ ዕብ. 8፥8-13)፡፡ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ሲነጻጸሩ አዲሱ ኪዳን ብልጫ አስገኝቷል፡፡ ብሉይ ኪዳን ባሰጣጡ ጊዜያዊ ሲሆን አዲስ ኪዳን ግን ዘላለማዊ ነው (ማቴ. 11፥13፤ ሉቃ. 16፥16)፡፡ ብሉይ ኪዳን የተሰጠው በሙሴ መካከለኛነት ሲሆን አዲስ ኪዳን ግን በእግዚአብሔር ልጅ መካከለኛነት ተሰጥቷል (ገላ. 3፥19፤ 1ጢሞ. 2፥5)፡፡ ብሉይ ኪዳን ሕዝቡን ሊያድን ስላልቻለ የኲነኔ አገልግሎት ነበረ፤ አዲስ ኪዳን ግን የሕይወት አገልግሎት ነው (2ቆሮ. 3፥7-11)፡፡ ብሉይ ኪዳን በድንጋይ ላይ የተጻፈ የሕግ ግዴታ ሲሆን አዲስ ኪዳን ግን በልባችን ጽላት ላይ የተጻፈ የፍቅር ሕግ ነው (2ቆሮ. 3፥3)፡፡
የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሰባት በሚያህሉ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የተጻፈ የሃያ ሰባት መጻሕፍት ጥቅልል ናቸው፡፡ እነዚህ ደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስ እስኪያድርባቸው ጌታን ይከተሉ የነበረው ለምድራዊ ትልቅነት ነበር፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ ሞትን አሸንፎ ከተነሣና መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ከምድራዊ የክብር አሳብ ተላቀው ሁሉን ጥለው ተከተሉት፡፡ ወንጌሉንም በማይመቹ ሁኔታዎች ለዓለም አደረሱ፡፡ መልእክቶቹን የጻፉት በርቀት የነበሩትን ክርስቲያኖች በእምነታቸው ለማጽናት ነው፡፡ የመልእክቱ ባለቤት መንፈስ ቅዱስ ግን እኛን ጭምር በዚያ መልእክት ውስጥ ይመለከት ነበር፡፡
አዲስ ኪዳን እንደ ብሉይ ኪዳን ሁሉ የራሱ የሆነ አከፋፈል አለው፡፡ ስለዚህ በአራት ተከፍሎ ይጠናል፡፡ ወንጌል፣ ታሪክ፣ መልእክትና ትንቢት፡፡
                                ወንጌል
ወንጌል የሚባለው ከማቴዎስ እስከ ዮሐንስ ያሉት አራት ክፍሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ክፍሎች የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መጸነስ፣ መወለድ፣ መኖርና መሞት፣ ትንሣኤና ዕርገት በሙሉነት ስለሚተርኩ ወንጌል የሚለውን ስያሜ አግኝተዋል፡፡ ወንጌል ማለት ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ መልእክት ነው (ሮሜ. 1፥3-4)፡፡ ወንጌል ቃሉ ዩአንገሊዎን ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው፡፡ ትርጉሙም የምሥራች ቃል ወይም የድኅነት ዜና ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ተወልዶ በመስቀል ላይ ስለ ኃጢአታችን ሞቶ ዓለምን ማዳኑን ስለሚናገርና ፍርድን የሚጠባበቁ ኃጢአተኞች ተስፋ ስለመጣላቸው ወንጌል ወይም የምሥራች ቃል ተብሏል፡፡
አራቱ ወንጌላት ቀጥተኛ ግባቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ድኅነት የሚጠይቀውን ሙሉ መንገድ ተጉዞ የሰውን ዘር ከዘላለም ጥፋት ማዳኑ ነው፡፡ ፀሐፊዎቹም ሁለቱ ማለትም ማቴዎስና ዮሐንስ ከጌታ አሥራ ሁለት ደቀ መዛሙርት መካከል ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ማርቆስና ሉቃስ ከሐዋርያት ጋር በቅርበት የነበሩ ከእነርሱ የሰሙትን በጥንቃቄ የጻፉ ናቸው፡፡ የማቴዎስ፣ የማርቆስና የሉቃስ ወንጌላት ተመሳሳይ ትረካ ያላቸው ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው መሆኑን በመግለጥ እግዚአብሔር በሰውና በሰው ታሪክ መካከል ያደረገውን ይተርካሉ፡፡ ዮሐንስ ግን በተለየ ሁኔታ የኢየሱስ ክርስቶስን ዘላለማዊ ክብር በመግለጥ አምላክነቱን ሰዎች እንዲቀበሉት ይጥራል፡፡ ቢሆንም ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ተገልጦ ያደረገው ተአምርና የተናገረው ቃል ሰማይ ብራና፣ ዕፅዋት ሁሉ ብዕር፣ ውቅያኖስ ሁሉ ቀለም ቢሆኑ ተጽፎ አያልቅም (ዮሐ. 21፥25፤20፥30)፡፡ ለመዳናችን የሚበቃን ግን ተጽፎልናል፡፡


አራቱ ወንጌላት
የማቴዎስ ወንጌል፡- በአዲስ ኪዳን ውስጥ ብዙ ምዕራፍ ካላቸው ሁለት መጻሕፍት አንዱ የማቴዎስ ወንጌል ነው፡፡ ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው ለአይሁድ ስለሆነ የዘር ሐረግን፣ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን በብዛት ይጠቅሳል፡፡ አይሁድ መሢሑን እንዲቀበሉ መሢሑ የአብርሃምና የዳዊት ዘር መሆኑን የሚገልጥ የዘር ፍሰትን ያወሳል፡፡ ለማስረጃም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን በብዛት ይጠቅሳል፡፡ በዘር ሐረጉ ግን አይሁድ የማይጠቀሙበትን ስልት በመጠቀም አራት ሴቶችን ጠቅሷል (ማቴ. 1፥4 ቁ. 5.6.16)፡፡ አይሁድ በዘር ሐረግ ውስጥ ሴቶችን አስገብተው አይቆጥሩም ነበርና፡፡ ክርስቶስ ግን የመምጣቱ አንዱ ዓላማ ይህን ልዩነት ለማስወገድ ነበር፡፡
የማርቆስ ወንጌል– ከወንጌላት ትንሽ ምዕራፎች ያሉት የማርቆስ ወንጌል ነው፡፡ የትምህርቱም ስልት የክርስቶስን የእጁን ተአምራት በመግለጥ በዘመኑ የነበሩ ሮማውያንን ለማሳመን ነው፡፡ ጌታችን በተያዘ ሌሊት እርቃኑን በነጠላ ሸፍኖ ይከተለው ነበርና በያዙት ጊዜ ነጠላውን ትቶ ራቁቱን የሸሸው ወጣት ማርቆስ መሆኑን ብዙ ሊቃውንቶች ይናገራሉ (ማር. 14፥51-52)፡፡ እናቱ ቤቷን ለአገልግሎት በመልቀቋ የማርቆስ እናት ቤት የመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን የሚል ስያሜ አግኝታለች (ሐዋ. 12፥12-17)፡፡ ማርቆስ ከበርናባስ፣ ከጳውሎስና ከጴጥሮስ ጋር ብዙ ጊዜ አገልግሏል፡፡ የጴጥሮስም የመንፈስ ልጁ ነው (1ጴጥ. 5፥13)፡ ወንጌሉን የጻፈውም ከእነዚህ ሐዋርያት በጥልቀት በመጠየቅና በማዳመጥ ነው፡፡
የሉቃስ ወንጌል፡- ሉቃስ ከአሕዛብ ወገን የሆነና በክርስቶስ ያመነ የጳውሎስም ደቀ መዝሙር የሆነ ሰው ነው፡፡ በሙያውም ሐኪም እንደ ነበረ ተጠቅሷል (ቈላ. 4፥14)፡፡ ስለ ክርስቶስም ሙሉ ትረካ ያቀረበ ፀሐፊ ነው፡፡ ወንጌሉን የጻፈው ከአሕዛብ ወገን ለነበረና ላመነ ቴዎፍሎስ ለሚባል ወዳጁ ነው፡፡ ማቴዎስ ወንጌሉን ከዘር ሐረግ ይጀምራል፣ ማርቆስ ከጥምቀቱ ይጀምራል፣ ሉቃስ ግን የኢየሱስ ክርስቶስ መልእክተኛ ከሆነው ከዮሐንስ መጥምቅ የጽንሰት ዜና ይጀምራል፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሉቃስ ወንጌሉንና የሐዋርያት ሥራን ጽፎአል፡፡
የዮሐንስ ወንጌል፡- ዮሐንስ ወንጌላዊ ከሦስቱ ወንጌላት በተለየ ሁኔታ ወንጌሉን ጽፎአል፡፡ ሦስቱ ወንጌላውያን የኢየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆንና ሰብአዊ ቅርበቱን ተርከዋል፡፡ ዮሐንስ ደግሞ የክርስቶስን መለኮታዊ ክብር በማጉላት ጽፎአል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰውነትና ፍጹም አምላክነት መቻቻል አለባቸው፡፡ ሰውነቱ አምላክነቱን ጋርዶብን አምልኮ እንዳንነፍገው፣ አምላክነቱ ሰውነቱን ሸፍኖብን እንዳናርቀው መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የወንጌላውያኑም ጭንቀት ይህ ነው፡፡ ዮሐንስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ አንድ ወንጌል፣ ሦስት መልእክታት፣ አንድ የራእይ መጽሐፍ ጽፎአል፡፡
ታሪክ
በአዲስ ኪዳን የታሪክ ክፍል ተብሎ የሚጠራው አንድ ጥራዝ ብቻ ነው፡፡ እርሱም የሐዋርያት ሥራ ነው፡፡
የሐዋርያት ሥራ፡- የሐዋርያት ሥራን የጻፈው ሉቃስ ነው፡፡ የጻፈውም ወንጌልን ለጻፈለት ቴዎፍሎስ ለተባለው ወዳጁ ነው፡፡ በሉቃስ ወንጌል እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት ሲናገር የሐዋርያት ሥራ ደግሞ ከዕርገቱ በኋላ ስላሉት ዐሥር ቀኖችና ስለ መንፈስ ቅዱስ መውረድ ይናገራል፡፡ የመጽሐፉ ሙሉ ይዘት ወንጌል ከኢየሩሳሌም እስከ ሮም ከዚያም እስከ መላው ዓለም በእንዴት ያለ ጸጋና ዋጋ መድረሱን የሚተርክ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት አድሮ የሠራው ሥራ በመሆኑ የሐዋርያት ሥራ ቢባልም ታሪኩን ስንዘልቀው ግን “የመንፈስ ቅዱስ ሥራ” ቢባል መልካም ነበር ያሰኛል፡፡ በዚህ መጽሐፍ በስፋት የተገለጠው የጴጥሮስና የጳውሎስ አገልግሎት ነው፡፡ መጽሐፉ እንደ ሌሎቹ መልእክታት በሰላምታ ወይም በምርቃት አይዘጋም፡፡ ይህ የሚያስረዳን የሐዋርያት ሥራ በትውልድ ሁሉ መቀጠሉን ነው፡፡
መልእክት
የአዲስ ኪዳን ሦስተኛው አከፋፈል መልእክት ነው፡፡ መልእክት የሚባሉት ከሮሜ እስከ ይሁዳ ድረስ ያሉት 21 የመጻሕፍት ጥቅልል ናቸው፡፡ ፀሐፊዎቹም ጳውሎስ፣ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ፣ ያዕቆብና ይሁዳ ናቸው፡፡ የተጻፉትም ለግለሰቦችና ለአብያተ ክርስቲያናት ነው፡፡
የጳውሎስ መልእክታት
ከሮሜ እስከ ዕብራውያን ድረስ ያሉት ዐሥራ አራት መልእክቶች ጳውሎስ የጻፋቸው መልእክቶች ናቸው፡፡ ጳውሎስ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት መካከል አይደለም፡፡ ጌታ ካረገ ከስምንት ዓመት በኋላ ነው የተጠራው፡፡ ክርስትናን በብርቱ ይቃወም በነበረ ሰዓት በደማስቆ መንገድ በመብረቅ ብርሃን ጥሎት፣ ሦስት ቀን ዓይኑን አውሮት በወንጌል አመነ (የሐዋ. 9፥18)፡፡ ከሁሉ ኋላ የተጠራ ቢሆንም ከሐዋርያት ይልቅ ሮጧል፣ ዋጋ ከፍሏል፣ አብያተ ክርስቲያናትን መሥርቷል፣ መልእክታትን ጽፏል፡፡ በመጨረሻም በ67 ዓ.ም በሮም አደባባይ በሰይፍ ሞቷል፡፡ መልእክቶቹ ግን ከከዋክብት ደምቀው በዓለም ሁሉ በየዕለቱ ያበራሉ፡፡ መልእክታቱ የተጻፉት ለግለሰቦችና ለአብያተ ክርስቲያናት ሲሆን ምእመናንን ለማጽናት፣ ለመገሰጽ፣ ለማጽናናት፣ ቤተ ክርስቲያንን ፍሬያማ ለማድረግ ባጠቃላይ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመንና በማወቅ ለማደግ ተጽፈዋል፡፡ ጳውሎስ መልእክታቱን የጻፈው ከእስር በፊትና በእስር ዘመን ነው፡፡ መልእክታቱም አብያተ ክርስቲያናቱ በሚገኙበት አገርና ግለሰቦች ተሰይመዋል፡፡ ለምሳሌ፡- የሮሜ መልእክት ሮም ለምትገኘው ቤተ ክርስቲያን የተጻፈ ሲሆን የጢሞቴዎስ መልእክት ደግሞ የጳውሎስ የመንፈስ ልጅ ለሆነው ለኤፌሶኑ ጳጳስ ለጢሞቴዎስ የተጻፈ ነው፡፡
የጴጥሮስ መልእክታት
ጴጥሮስ ከኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አንዱና የመጀመሪያው ሲሆን የኢየሱስ ክርስቶስን የእጁን ተአምራት፣ የቃሉን ትምህርት በቀጥታ የተቀበለ ነው፡፡ ጳውሎስ የአሕዛብ ሐዋርያ ሲሆን ጴጥሮስ የአይሁድ ሐዋርያ ነበር፡፡ በ67 ዓ.ም በሮም አደባባይ የቊልቊሊት ተሰቅሎ እስኪሞት በብዙ ስደትና መከራ ወንጌልን ሰብኮአል፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሁለት መልእክታትን ጽፎአል፡፡ የመጀመሪያው መልእክቱ በተለያዩ የእስያ አውራጃዎች ስለ ወንጌል ለተሰደዱ ክርስቲያን አይሁዶች የጻፈው ሲሆን በመታገሥ ያለውን ሰማያዊ ዋጋ በመግለጥ ሊያጸናቸው ጽፏል፡፡ ሁለተኛይቱ የጴጥሮስ መልእክት ደግሞ በክርስቲያኖች መካከል ሰርገው ስለገቡ የሐሰት መምህራን (መናፍቃን) ምእመናን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጽፎአል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የአረማውያን ነገሥታትን ያህል የሐሰት መምህራንም ጎጂዎቿ ናቸውና፡፡
የዮሐንስ መልእክታት
ዮሐንስ የክርስቶስን መለኮታዊ ክብር ለማጉላት ወንጌሉን እንደ ጻፈ  ዓይተናል፡፡ ደግሞም ሦስት መልእክታትንም አዘጋጅቷል፡፡ መልእክታቱንም ሆነ ወንጌሉን እንዲሁም ራእዩን የጻፈው በዕድሜው መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡ የመጀመሪያይቱን መልእክቱን የጻፈው በዘመኑ ተስፋፍቶ የነበረውን የመናፍቃንን እንቅስቃሴ ለመጋፈጥና ምእመናን በፍቅር እየተባበሩ እምነታቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛይቱን መልእክት ደግሞ የጻፈው ለአንዲት አማኝ ሴት ሲሆን ከስህተት ትምህርት እንድትጠበቅ ነው፡፡ ሦስተኛይቱ የዮሐንስ መልእክት በቤቱ እንግዶችን ለሚቀበል ጋይዮስ ለተባለ በጎ አማኝ ለምስጋና የጻፈለት መልእክት ነው፡፡
የያዕቆብ መልእክት
ያዕቆብ ከጌታ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነው፡፡ ይህ ያዕቆብ ይህችን ቀደምት መልእክቱን የጻፈው በስደት ለተበተኑት ክርስቲያን አይሁድ ሲሆን የመልእክቱ ዋና ዓላማ በመከራቸው እንዲፀኑና እምነታቸውን በምግባር እንዲገልጡ ለማነቃቃት ነው፡፡
የይሁዳ መልእክት
ባለ አንድ ምዕራፍ ከሆኑት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አንዱ የይሁዳ መልእክት ሲሆን ይሁዳም መልእክቱን የጻፈው በስም ላልተጠቀሱ አማንያን ነው፡፡ የመልእክቱም ዓላማ ክርስቲያኖች ሁሉ እምነታቸውን እንዲጠብቁ ለማስጠንቀቅ ነው፡፡
ትንቢት
በአዲስ ኪዳን ውስጥ የትንቢት መጽሐፍ ተብሎ የሚጠራው የዮሐንስ ራእይ ነው፡፡
የዮሐንስ ራእይ፡- ዮሐንስ ፍጥሞ በምትባል ደሴት ተግዞ /ታስሮ/ ሳለ በራእይ ያለፈውን፣ ያለውንና የሚመጣውን ተገልጾለት ጽፏል፡፡ የዮሐንስ ራእይ ክርስቲያኖችን ለማይቀረው የክርስቶስ ምጽአት ያዘጋጃል፡፡ አገላለጹም ሥዕላዊ ነው፡፡ ይህ የሆነው ሥዕል ከብዙ ቃላት ይልቅ የመናገር አቅም ስላለውና ዳግመኛም መጽሐፉን ከአደጋ ለመከላከል ነው፡፡ ትንቢቶቹ በግልጽ ቢጻፉ ኖሮ አረማውያን ነገሥታት በቶሎ ይጠፉታልና ጠላት ለመቀነስ ነው፡፡
ይህንን ጥናት ስናጠና የመጽሐፍ ቅዱሳችንን ማውጫ እየተመለከትን ብናጠና ይበልጥ ይብራራልናል፡፡ አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በምዕራፍ ይከፈላል፡፡ ምዕራፉ ደግሞ በቊጥር ይከፈላል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሲጠቀስ በአጭሩ ይጠቀሳል፡፡ ለምሳሌ፡- ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ አሥራ አምስት ቊጥር ስድስት ቀጥሎ ባለው መልኩ ይጠቀሳል፡- (ዘፍ. 15፥ 6)፡፡
                                                                  ይቀጥላል
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ