የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መጽሐፍ ቅዱስ / ክፍል ስድስት

                                         ሰኞ፣ ሐምሌ 21/2006 ዓ.ም.

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በቅኝት መልክ

መጽሐፍ ቅዱስ ማለት “ልዩ መጽሐፍ” ማለት ነው፡፡ በዓለም ላይ ከሚገኙት መጻሕፍት ልዩ የሚያደርገው በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈና ሕይወት ሰጪ መጽሐፍ በመሆኑ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የኪዳን መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚመራው በኪዳኑ መሠረት ነው፡ ከእያንዳንዱ ሰው ጋርም ኅብረት የሚያደርገው በኪዳን ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የኪዳኑ ቅዱስ ሰነድ ነው፡፡ እነዚህም ታላላቅ ኪዳናት ሁለት ሲሆኑ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ይባላሉ፡፡ ኪዳን የሚያሟላቸውን ነገሮች ቀጥሎ ባለው ሠንጠረዥ ተገልጿል፡፡
ኪዳኑ
ኪዳን ሰጪ
ኪዳን ተቀባይ
የኪዳን ግዴታ
የኪዳን በረከት
የኪዳን ምልክት
ብሉይ ኪዳን
እግዚአብሔር
እስራኤል
ሕግን መጠበቅ
ከነዓንን መውረስ
ሰንበት
አዲስ ኪዳን
እግዚአብሔር
በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ
እምነት
የዘላለም ሕይወት
ቅዱስ ቊርባን
       
የሰንጠረዡ ማብራሪያ ፡- በሁለቱም ኪዳናት የኪዳኑ ባለቤትና ኪዳን ሰጪ እግዚአብሔር ነው (ኤር. 31፥31-34፤ ዕብ. 8፥8-12)፡፡ የመጀመሪያው ኪዳን (ብሉይ ኪዳን)  የተሰጠው ለአንድ ሕዝብ (ለአይሁድ) ሲሆን አዲስ ኪዳን ግን የተሰጠው ለመላው ዓለም (ላመኑት ሁሉ) ነው (ዘፀ. 24፥1-8፤ዮሐ. 3፥16)፡፡ ብሉይ ኪዳን የሕግ ግዴታ ሲኖረው አዲስ ኪዳን ደግሞ በክርስቶስ ማመንን ይጠይቃል (2ቆሮ. 3፥4-18፤ ገላ. 2፥16)፡፡ የብሉይ ኪዳን በረከቱ ምድራዊ ሲሆን  የአዲስ ኪዳን ግን ሰማያዊ በረከት ነው (ኢያ. 1፥1-9፤ ኤፌ. 1፥3)፡፡ ኪዳን ማስታወሻ /ምልክት/ ያስፈልገዋል፡፡ የብሉይ ኪዳን ምልክቱ ሰንበት ሲሆን በአዲስ ኪዳን ግን ቅ/ቊርባን ነው (ዘፀ. 31፥17፤ ሉቃ. 22፥20)፡፡

የሁለቱ ኪዳናት ሰንሰለት
        ሁለቱ ኪዳናት ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን እንደማያቋርጥ የወንዝ ፈሳሽ፣ አንዱ አንዱን እንደሚስበው ሐረግ፣ አንደኛው በአንዱ እንደ ታሠረ ሰንሰለት የታሪክና የእምነት ትስስር አላቸው፡፡ አንዱ ያለ አንዱ እንደማይቆም የሕንጻ   ካብ ሁለቱ ኪዳናት ተደጋግፈዋል፡፡ ብሉይ ኪዳን ጅምር ሲሆን አዲስ ኪዳን ፍጻሜ ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን ያለ አዲስ ኪዳን መጨረሻ የሌለው መጀመሪያ ነው፡፡ አዲስ ኪዳንም ያለ ብሉይ ኪዳን መጀመሪያ የሌለው መጨረሻ ነው። ስለዚህ ስብከታችን ከብሉይ ኪዳን ተነሥቶ ወደ አዲስ ኪዳን ሲመጣ ዘላለማዊነትን ያገኛል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የኪዳናቱን ትስስር ጥላና አካል፣ ምሳሌና እውነት፣ ትንቢትና ፍጻሜ እያለ ይገልጠዋል (ቈላ. 2፥16፤ ዕብ. 10፥1፤ ሉቃ. 24፥44)፡፡
የብሉይ ኪዳን ጥናት በቅኝት መልክ
        ብሉይ ኪዳን ማለት ምን ማለት ነው? ስንል ብሉይ ማለት በግእዝ ቋንቋ አሮጌ /ያረጀ/ ማለት ነው፡፡ ኪዳን ማለት ደግሞ መሐላ፣ ውል ስምምነት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ብሉይ ኪዳን ማለት የቆየ መሐላ ማለት ነው (ዕብ. 8፥13)፡፡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በአራት ይከፈላሉ፡፡ እነርሱም፡-
   ኦሪት
   ታሪክ
   ጥበብና
   ትንቢት ይባላሉ፡፡
ኦሪት
        ኦሪት ማለት ሕግ ማለት ነው፡፡ የኦሪት መጻሕፍት የሚባሉትም ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ኦሪት ዘዳግም ያሉት አምስት መጻሕፍት ናቸው፡፡ ፀሐፊያቸውም ሙሴ ነው፡፡
ኦሪት ዘፍጥረት፡- “ዘ” የሚለው የግእዝ ፊደል “የ” የሚለውን የአማርኛ ቃል የሚተካ አገናኝ ቃል ነው፡፡ ኦሪት ዘፍጥረት ማለትም “የመፈጠር ሕግ” ማለት ነው፡፡ የኦሪት ዘፍጥረት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ምዕራፎች ስለ ዓለምና ስለ ሰው ተፈጥሮ ስለሚናገሩ ከሦስቱ የመግቢያ ምዕራፎች አሳብ በመነሣት ኦሪት ዘፍጥረት ወይም የመፈጠር ሕግ የሚለውን ስያሜ አግኝቷል፡፡
ኦሪት ዘፀአት፡- “የመውጣት ሕግ” ማለት ነው፡፡ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ባርነት ነጻ መውጣታቸውን ስለሚተርክ የመውጣት ሕግ ተብሏል።
ኦሪት ዘሌዋውያን፡- “የሌዋውያን ሕግ” ማለት ነው። ሌዋውያን የመቅደስ አገልጋዮች ናቸው። መጽሐፉ ስለ ሌዋውያን አገልግሎት ስለሚናገር የሌዋውያን ሕግ ተብሏል። መልእክቱ ቅድስናን የሚመለከት በመሆኑም “የቅድስና ሕግ” ይባላል። ትልቁ የአገልግሎት መገለጫም ቅድስና ስለሆነ ኦሪት ዘሌዋውያን መባሉ መልካም ነው።
ኦሪት ዘኁልቍ፡- “የመቆጠር ሕግ” ማለት ነው። የእስራኤል ልጆችን እንዲቆጥር እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘበት ክፍል ስለሆነ የመቆጠር ሕግ ተብሏል፡፡
ኦሪት ዘዳግም፡- “የመደገም ሕግ” ማለት ነው፡፡ ሙሴ በምድረ በዳ ለተወለዱት የእስራኤል ልጆች የሕጉን መጽሐፍ እንደገና ስላስተማራቸው የመደገም ሕግ ተባለ፡፡ በክፍሉ ላይ ሙሴ ከግብጽ ምድር ለወጡት የእግዚአብሔርን ውለታ ሲያዘክር፣ በምድረ በዳ ለተወለዱት ደግሞ ትእዛዙን ይከልስላቸዋል፡፡
ታሪክ
የታሪክ ክፍል የሚባለው ከመጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ እስከ መጽሐፈ አስቴር ያሉት 12 መጻሕፍት ናቸው፡፡
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ፡- የነዌ ልጅ የኢያሱ መጽሐፍ ማለት ነው፡፡ የነዌ ልጅ ኢያሱ ከሙሴ ቀጥሎ እስራኤልን የመራና የተስፋቸው ፍጻሜ የሆነችውን ከነዓንን ያከፋፈለ መሪ ነው፡፡ ፀሐፊው እርሱ ስለሆነም መጽሐፉ በስሙ ተሰይሟል፡፡
መጽሐፈ መሳፍንት፡- ከኢያሱ ሞት በኋላ 13 መሳፍንት እስራኤልን አስተዳድረዋል። እግዚአብሔር ሕዝቡን በመሳፍንት አድሮ ከጠላት እንዴት እንደታደጋቸው የሚገልጽ መጽሐፍ ነው። ሳሙኤል እንደጻፈውም ይገመታል።
መጽሐፈ ሩት፡- በሴት ስም ከተሰየሙት ሁለት መጻሕፍት አንዱ መጽሐፈ ሩት ነው፡፡ ሩት ከዚህም ሌላ አሕዛባዊት ሴት ስትሆን በእግዚአብሔር ጥበብ የዳዊት የሴት ቅድመ አያት ለመሆን በቅታለች፡፡ ፀሐፊው ሳሙኤል እንደሆነ ይነገራል፡፡
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊና ካልዕ፡- እነዚህ በታላቁ ነቢይ በሳሙኤል የተሰየሙት ሁለት መጻሕፍት ከመሳፍንት ዘመን ማብቂያ ጀምሮ ያለውን ዘመነ ነገሥትን ይተርካሉ፡፡ ሰፊ ሽፋንም የተሰጣቸው የመጀመሪያው ንጉሥ ሳኦልና ሁለተኛው ንጉሥ ዳዊት ናቸው፡፡ ቀዳማዊ ማለት አንደኛ ማለት ሲሆን ካልዕ ማለትም ሁለተኛ ማለት ነው፡፡ የእነዚህ መጻሕፍት ፀሐፊ ሳሙኤል ስለሆነ በእርሱ ስም ተሰይመዋል፡፡
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊና ካልዕ፡- ከሦስተኛው ንጉሥ ከሰሎሞን እስከ ባቢሎን ምርኮ የነገሡትን የ360 ዓመታት የነገሥታት ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፈ ነገሥት ተብሏል፡፡ ፀሐፊው ማን እንደሆነ አልታወቀም፡፡ 
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊና ካልዕ– ዜና መዋዕል ማለት የዘመናት ታሪክ ማለት ነው፡፡ ከመጽሐፈ ነገሥት ጋር ሙሉ በሙሉ የዘመን ትስስር አለው፡፡ ወይም አራቱም መጻሕፍት የተወሰኑ ዘመናትን በጣምራነት ይተርካሉ፡፡ ልዩነቱ ግን የነገሥት ሁለት መጻሕፍት የቤተ መንግሥቱን ታሪክና ውድቀት ሲተርኩ የዜና መዋዕል መጻሕፍት ግን የቤተ ክህነቱን ሂደትና ውድቀት ይተርካሉ፡፡ አራቱም መጻሕፍት እስከ ባቢሎን ምርኮ ድረስ ዘግበዋል፡፡ የዜና መዋዕል መጻሕፍትም ዕዝራ እንደ ጻፋቸው ይነገራል፡፡
መጽሐፈ ዕዝራ፡- ዕዝራ ፀሐፊና ካህን ነበር፡፡ በባቢሎን ምርኮ ያደገ ሰው ነው፡፡ ቤተ መቅደሱ እንዲሠራና ሕዝቡም መንፈሳዊ መነቃቃት እንዲያደርግ የታገለ ሰው ነበር፡፡ ፀሐፊውም ራሱ ስለሆነ መጽሐፈ ዕዝራ ተብሏል፡፡
መጽሐፈ ነህምያ፡- ነህምያ በባቢሎን ምርኮ አገር የንጉሡ ጠጅ አሳላፊ ነበር፡፡ ስለ ኢየሩሳሌም መፍረስ ስለ ቅጥርዋ መናድ አብዝቶ ያዝን ነበርና በንጉሡ ፈቃድ ቅጥርን አደሰ፣ አስተዳደርዋንም መለሰ፡፡ መጽሐፉን ራሱ ነህምያ ስለ ጻፈው በስሙ ተሰይሟል፡፡
መጽሐፈ አስቴር፡- አስቴር በምርኮ አገር ንጉሡን ያገባች ሴት ስትሆን ወገኖቿ አይሁድ የታወጀባቸውን የሞት አዋጅ እንዲቀይር በቆራጥነት የደከመች ሴት ናት፡፡ አይሁድም የሞት አዋጁ በሕይወት ተለውጦላቸዋል፡፡ በሴት ስም ከተሰየሙት ሁለት መጻሕፍት አንዱ መጽሐፈ አስቴር ነው፡፡ ፀሐፊው ማን እንደሆነ አልታወቀም፡፡ አይሁድ ከሞት የዳኑበትን ቀን “ፉሪም” ዕጣ ማለት ነው ሲያከብሩ መጽሐፈ አስቴርን ያነቡ ነበር፡፡
ጥበብ
የጥበብ መጻሕፍት የሚባሉት ከመጽሐፈ ኢዮብ እስከ መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ድረስ ያሉት አምስት መጻሕፍት ናቸው፡፡
መጽሐፈ ኢዮብ፡- በጥንት ዘመን ስለኖረና በሕይወት ብዙ ተፈትኖ ነጥሮ ስለወጣው ስለ ኢዮብ የሚናገር መጽሐፍ ሲሆን መጽሐፉም በራሱ በኢዮብ ተሰይሟል፡፡ ፀሐፊው ማን እንደሆነ አልተገለጸም፡፡
መዝሙረ ዳዊት፡- ነቢዩና ንጉሡ ዳዊት ስለ ሕይወቱ ስለ ኑሮው ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገው ንግግር ነው። ደራሲውም የመዘምራን አለቃ ዳዊትና ሌሎችም ዘማርያን ናቸው።
መጽሐፈ ምሳሌ፡- የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ምሳሌ ነው፡፡ ሰሎሞን ሦስት መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ መጽሐፈ ምሳሌ፣ መጽሐፈ መክብብ፣ መኃልየ መኃልየ ዘሰሎሞን ይባላሉ፡፡ መክብብ ማለት ሰባኪ ማለት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ውጭ ስላለው ነገር ከንቱነት ይናገራል፡፡ መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ማለት ደግሞ ከመዝሙሮች የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር ማለት ነው፡፡ በሁለት ሰዎች ማለት በሴትና በወንድ ቅላፄ የተዋቀረ መዝሙር ሲሆን የቤተ ክርስቲያንና የክርስቶስን ፍቅር ይገልፃል፡፡
ትንቢት
የትንቢት ክፍሎች ዐሥራ ሰባት መጻሕፍትን ይዘዋል፡፡ ነቢያቱ አንዳንዴ በሁለት፣ ሌላ ጊዜም በሦስት ይከፈላሉ፡፡ በሁለት ሲከፈሉ ዐበይት ነቢያትና ደቂቅ ነቢያት ይባላሉ፡፡ ስለዚህ ዐበይት ነቢያት የሚባሉት ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ናቸው፡፡ ደቂቅ ነቢያት የሚባሉትም ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ ያሉት ነቢያት ናቸው በሦስት ሲከፈሉም ከምርኮ በፊት የነበሩ፣ በምርኮ ዘመን የነበሩ፣ ከምርኮ ዘመን በኋላ የነበሩ ነቢያት ተብለው ይከፈላሉ፡፡
   ከምርኮ ዘመን በፊት የነበሩ፡- ኢሳይያስ፣ ሆሴዕ፣ አሞጽ፣ ሚክያስ፣ ኢዩኤል፣ አብድዩ፣ ዮናስ፣ ናሆም፣ ዕንባቆም፣ ሶፎንያስ፣ ናቸው፡፡
   በምርኮ ዘመን የነበሩ፡- ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ዳንኤል ናቸው፡፡
   ከምርኮ ዘመን በኋላ የነበሩ፡- ሐጌ፣ ዘካርያስና ሚልክያስ ናቸው፡፡
ከምርኮ ዘመን በፊት የነበሩት ነቢያት ሕዝቡን ይገስጹ፣ ያስጠነቅቁ ነበር፡፡ በምርኮ ዘመን የነበሩ ነቢያት ደግሞ ሕዝቡን ያጽናኑ ነበር፡፡ ከምርኮ ዘመን በኋላ የነበሩ ነቢያት ደግሞ የፈረሰው እንዲጠገን፣ የእግዚአብሔር ቤት እንዲለማ ያበረታቱ ነበር፡፡ ከትንቢት ክፍሎች ትርጉም የሚያሻው አርእስት “ሰቆቃወ ኤርምያስ” ሲሆን ትርጉሙም የኤርምያስ ሐዘን ወይም ልቅሶ ማለት ነው፡፡
የብሉይ ኪዳን ሠላሳ ዘጠኙ መጻሕፍት ከ1400-400 ዓመተ ዓለም ከክርስቶስ በፊት ተጽፈዋል፡፡ የመጨረሻውም ነቢይ ሚልክያስ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ የተጻፉ መጻሕፍትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ እና የካቶሊክ ቤ/ክ ተቀብለዋቸዋል፡፡ እነዚህ መጻሕፍት ዲዩትሮካኖኒካል ወይም ተጨማሪ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አሊያም “የብሉይ ኪዳን 2ኛ የቀኖና መጻሕፍት” በመባል የሚታወቁት ናቸው፡፡ እነዚህ መጻሕፍት ከ39ኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጋር በአንድነት የተቆጠሩት ከሰባ ሊቃናት ትርጉም በኋላ ነው፡፡ ሰባ ሊቃናት የሚባሉት ለመጀመሪያ ጊዜ ብሉይ ኪዳንን ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ የተረጎሙ የአይሁድ መምህራን ናቸው፡፡ እነዚህ ሊቃውንት ብሉይ ኪዳንን ወደ ግሪክ ሲመልሱ እነዚህንም መጻሕፍት አብረው መልሰዋል፡፡ መጻሕፍቱ በጥንቱ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ይሰጡ ነበር፡፡ ከባቢሎን ምርኮ በኋላ እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ ስላለው የታሪክ ሂደት እነዚህ መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ የምክርና የጥበብ ትምህርቶችንም ይዘዋል፡፡ ለምሳሌ፡- መጽሐፈ ሲራክንና መጽሐፈ ጥበብን መጥቀስ እንችላለን፡፡
በርግጥ የአይሁድ መምህራን (ረቢዎች) በ90 ዓ.ም. በምዕራብ ኢየሩሳሌም ያምኒያ በሚባለው ቦታ የያምኒያ ጉባዔ ተብሎ በሚጠራው የሊቃውንት ስብሰባ እነዚህን መጻሕፍት እንደማይቀበሉ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ መጻሕፍቱ ግን በኦርቶዶክስና በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡ እንግዲህ የብሉይ ኪዳን ቀጥተኛ ተቀባዮችና ባለ አደራዎች አይሁዳውያን ሲሆኑ የአዲስ ኪዳን ቀጥተኛ ተቀባይና ባለ አደራ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡
-ይቀጥላል-
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ