የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መጽሐፍ ቅዱስ / ክፍል ዐሥር

                                                              ማክሰኞ፣ ነሐሴ 6 /2006 ዓ.ም.
መጽሐፍ ቅዱስን እናንብብ 
ነቢዩ  ሕዝቅኤል፡- “ይህን መጽሐፍ ብላ … አፍህ ይብላ÷ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ አለኝ፡፡ እኔም በላሁት÷ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ” (ሕዝ. 3፥1-3) ብሏል፡፡ አንድ ሰውም፡- “ሰይጣን ሰዎችን ሙሉ ለሙሉ አሸንፎ ከቊጥጥሩ በታች የሚያውለው መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያነቡና እውነትን ከውስጡ እንዳይፈልጉ ልባቸውን ከዘጋ በኋላ ነው” ብለዋል፡፡ ሌላውም አዋቂ፡- “ከሁሉ የበለጠው ቁጠባ የጊዜ ቁጠባ ነው፡፡ ከሁሉ የበለጠ የጊዜ ቁጠባ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ጊዜን ማሳለፍ ነው” ብለዋል፡፡
እግዚአብሔር የተፈራ ነው፡፡ ቃሎቹም የተከበሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በትሑት ልብና በጸሎት መንፈስ ማንበብ ይገባናል፡፡ ሥጋዊ ማዕድን እንኳ በአክብሮትና በጸሎት ነው የምንመገበው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ዝም ብለን የምንገልጠው ሳይሆን እግዚአብሔር እንዲናገረን ተዘጋጅተን የምንጠብቅበት ሰዓት ነው፡፡ በሥርዓት ከተገለጠ አይጠገብም፡፡ ሁልጊዜም አዲስ ነው፡፡ ለዕውቀት ብቻ ካነበብነው ግን አይገባንም፡፡ ምክንያቱም አምላካችን በመንፈስ የሚገኝ አምላክ ነውና፡፡

አንድ አባት፡- “መጽሐፍ ቅዱስን ከ150 ጊዜ በላይ ዘልቄዋለሁ፡፡ ጠዋት የብሉይ ኪዳን ታሪኮችን፣ ከሰዓት በኋላ የትንቢትና የጥበብ መጻሕፍትን፣ ማታ አዲስ ኪዳንን አነባለሁ፡፡ አሁንም እያነበብኩት ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የተረዳሁት ነገር ቢኖር አንደኛ፡- ደግሜ ባነበብኩት ቊጥር አዲስ ነው፣ ሁለተኛ አንዱን ጥቅስ የተለያየ ምሥጢር ነው የማገኝበት” በማለት ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ እኚህ አባት በልጅነታችን መጽሐፍ ቅዱስን ያስተማሩን አሁን ዕድሜአቸው ወደ ሰማንያ ዓመት የሚጠጋቸው መነኲሴ ናቸው፡፡ በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ተነቦ የሚያበቃ አይደለም፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ እንፈራ ይሆን? የምናነበውስ እንዴት ነው? ከሰዎች ጋር ስንወያይ አስተሳሰባችንን ሳንለቅ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ስንወያይ ግን አስተሳሰባችንን ጥለን ሊሆን ይገባል፡፡ እግዚአብሔር ስፍራ ካልተለቀቀለት ወይም እኛ በምናዝበት ግዛት አይገለጥምና፡፡
ዕውቀት ያሳስታል ብለን እናምን ይሆን? ትክክለኛ እምነት እኮ የትክክለኛ ዕውቀት ውጤት ነው፡፡ ቃሉ፡- “ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፤ አንተም ዕውቀትን ጠልተሃልና” (ሆሴ. 4፥6) ይላል፡፡ ተግባራችን በዕውቀት ላይ መመሥረት አለበት፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ “እወቅ” ይላል (2ጢሞ. 3፥1)፡፡ እግዚአብሔር አውቀነው እንድናመልከው ይሻል፡፡ እግዚአብሔርን ካላወቅነው ተገቢውን አምልኮ እንዴት እንሰጠዋለን? ጌታችን ለሳምራዊቷ ሴት፡- “እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን” በማለት እውነተኛ አምልኮ እግዚአብሔርንና አዳኙን በማወቅ መሆኑን ገልጾላታል (ዮሐ. 4፥22)፡፡ ስለዚህ ዕውቀትን መጥላት አይገባንም፡፡ አንድ አባት፡- “የማይማር መንፈስ አደገኛ ነው” ይሉ ነበር፡፡


ማጠቃለያ
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ እናምናለን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ዓላማና ፈቃድ የተገለጠበት የእውነት ቃል ነው፡፡ ይህም ከዘመናት በኋላ የመጣ አዲስ አሳብ ሳይሆን ከዘመናት በፊት የነበረ የእግዚአብሔር ዕቅድ ነው (ሮሜ. 8፥29)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሥጋና የደም ምክር ሳይሆን የእግዚአብሔር መለኮታዊ ምሥጢር ያለበት የሕይወት መጽሐፍ ነው፡፡ ለጠፉት ሰዎች ወደ እውነተኛው መንገድ ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ መንፈሳዊ ካርታ ነው (ዮሐ. 14፥6)፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ ዘመን በተለያዩ ሰዎች ቢጻፍም ምሥጢሩ ግን አንድ ነው፡፡ ሰዎች ቢጽፉትም ከሰዎች የሆነ ቃል አይደለም (2ጴጥ. 1፥21፡ 1ተሰ. 2፥13)፡፡ እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ቢናገርም (ዕብ. 1፥1) በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ተናገረው ግን አልተናገረም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ውሳኔ ስለሆነ እግዚአብሔር አሻሽሎ በግላችን አይነግረንም፡፡ የማይለወጥ ፀንቶ የሚኖር ቃል ነው (ዘዳ. 12፥32፤ ኢሳ.40፥8)፡፡ የእግዚአብሔርንም ድምፅ የምናረጋግጥበት ማስረጃ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ በዚህ ዘመንም በእርግጠኝነት የሚናገርበት መንገድ ይኽው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡
ቃሉ ያለ መንፈስ ቅዱስ እንደማይሠራ ሁሉ መንፈስ ቅዱስም ያለ ቃሉ አይናገርም (ዮሐ. 14፥26)። ውስጣዊ ነገራችን እንዲያድግ ተአምር አንፈልግ፤ የምናድገው በቃሉ ነው (1ጴጥ. 2፥2፤ የሐዋ.ሥራ 20፥32)፡፡ ቃሉ በእኛ ውስጥ ካለ እጅግ መልካም ነው (ቆላ. 3፥16)፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሰማያትን ያፀና ከሆነ እኛን እንደሚያቆም እርግጥ ነው (መዝ. 32፥6)፡፡ እምነት የሚመጣው ከመስማት ነው፡፡ የምንሰማው የእግዚአብሔርን ቃል ነው (ሮሜ. 10፥17)፡፡ የምናምነውን የሚወስን የምንሰማው ነገር ነው፡፡ የእምነት ምንጩ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በቃሉ እግዚአብሔርን እናምናለን፡፡ እምነታችንን ትክክለኛ የሚያደርገው የምናምንበት ነገር ነው፡፡ እምነት ከእግዚአብሔር ቃል በቀር መሠረት የለውም፡፡ ሰዎች ከልባቸው ሊያምኑ ይችላሉ፡፡ እምነታቸውን ትክክለኛ የሚደርገው ግን ከልብ ማመናቸው ብቻ ሳይሆን ማመናቸው የተመሠረተበት ነገር ነው፡፡
ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝባቸው መስመሮች እምነትና አምልኮ ናቸው፡፡ የሁለቱም መሠረት የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ አምልኮ የእግዚአብሔር ታላቅነትና ፍቅር ሲገባን ለእግዚአብሔር የምናቀርበው አክብሮት ነው፡፡ እግዚአብሔርን ካላወቅን ልናመልከው አንችልም፡፡ ካልተገለጠልንም አንሰግድለትም (ዘፍ. 18፥2)፡፡ እግዚአብሔርን የምናውቀው በቃሉ ነው፡፡ እንደ ቃሉ ካላወቅነው የሚወደውን እምነት ልንይዝና የሚፈልገውን አምልኮ ልናቀርብለት አንችልም፡፡ እግዚአብሔር የቅርብ አምላክ ቢሆንም ያለ መንገዱ አይገኝም፡፡
የእግዚአብሔር ቃል የሚወልድ (ያዕ. 1፥18)፣ የሚያሳድግ (1ጴጥ. 2፥2 )፣ ወደ ሰማያዊ ርስት የሚመራና የሚያደርስ (የሐዋ.ሥራ 20፥32) ቃል ነው፡፡ ለዘላለማዊ ሕይወት የሚያበቃ የቃል ልደት ያስፈልጋል (1ጴጥ. 1፥23)፡፡
በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈው ቅዱስ መጽሐፍ የሰዎችን ሕይወት ለመምራት ብቁ ነው፡፡ በሚያውቀን በእግዚአብሔር መንፈስ ስለ ተጻፈ እውነተኛው እኛነታችን በመጽሐፍ ቅዱስ ተገልጧል፡፡ ነቢዩ ዳዊት፡- “ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ” (መዝ. 138፥16) ያለው ለዚህ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተስፋ፣ የፍቅር፣ የሥነ ምግባር፣ የፍትሕ፣ የመጽናናት መጽሐፍ ነው፡፡
ተስፋ፡- የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ምኞትና ናፍቆት ብቻ ሳይሆን አለኝታና መተማመን የሚገኝበት ነው (ሮሜ. 15፥13)፡፡ እግዚአብሔር አይዋሽምና ተስፋው እርግጠኛ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በዘላለማዊ ኪዳን፣ በተቀደሰ ተስፋ ልብን ያሳርፋል፡፡
ፍቅር፡- መጽሐፍ ቅዱስን በሥራ ላይ ስናውል ከሰዎች ጋር ትርጉም ያለው ግንኙነት ይኖረናል፡፡
ሥነ ምግባር፡- በዓለማችን ላይ በሥነ ምግባር ያጌጡ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ያነበባቸው ሰዎች ናቸው፡፡
ፍትሕ፡- ጌቶች ለሚገዟቸው ሠራተኞቻቸው ባለ አደራዎች መሆናቸውን አስረግጦ የሚናገር መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የመምራት፣ የመፍረድ፣ የመግዛት፣ ማንኛውንም ነገር የማድረግ ኃይል ያለው የሥልጣን ቃል ነው፡፡ አብያተ ክርስቲያናት የመጽሐፍ ቅዱስን የበላይነት እየተጋፉ ነውና ያስፈራል፡፡ የራሳቸውን መገለጥ እንጂ ትልቁን መገለጥ ችላ ብለዋል፡፡
መጽናናት፡- መጽሐፍ ቅዱስ ተነዋዋጭ በሆነው በዛሬው ዓለም ውስጥ አስተማማኝ መልሕቅ ነው፡፡ “በሐሴት ስንሞላም ይሁን ስናዝን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ መቻል ይኖርብናል፡፡ ያለበለዚያ ሕይወትን አቻችለን ለመምራትም ሆነ ለመቋቋም አቅም አይኖረንም፡፡” ጠቅላላው አሳቡ በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ከሌለ ሕይወት አስቸጋሪና መራራ እንደምትሆን መግለጥ ነው፡፡
አዎ መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈ የትምህርት ተግሣጽ የምክር መጽሐፍ ነው (2ጢሞ. 3፥16)፡፡ የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝ ዕድሜው 2000 ዓመት እየተጠጋው ነው፡፡ ጥንታዊ መጽሐፍ ቢሆንም ሁልጊዜ አዲስ ነው፡፡ በእግዚአብሔርም መንፈስ የተጻፈ ነውና ምክሩ አያረጅም፡፡ በቅዱሳን የተፈጸመው የእግዚአብሔር ተስፋ ለእኛ ይሠራልና እውነተኛ ያደርገዋል፡፡ የሰዎችን ብርታታቸውን ብቻ ሳይሆን ድካማቸውንም የሚገልጥ የሐቅ መጽሐፍ ነው፡፡ ከ1400 ዓመተ ዓለም እስከ 96 ዓ.ም በማይተዋወቁ ሰዎች በተለያየ ዘመንና ቦታ በተወለዱ ከ40 በላይ በሚሆኑ ፀሐፊዎች ቢጻፍም እግዚአብሔር በመንፈሱ ይቆጣጠረው ነበርና የሚቃረን አሳብ የለበትም፡፡ በዓለማችን ላይ በትኲረት ለመነበብ ከበቁት መጻሕፍት ሁሉ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ (የተለየው መጽሐፍ) ከ2000 ቋንቋዎች በላይ ተተርጒሞ ይነበባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የመጻሕፍት አባት ሆኖ ያርማል እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በሌላ መጽሐፍ አይታረምም፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በሚል ርእስ በተከታታይ የቀረበው ትምህርት ተፈጸመ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ