የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መጽሐፍ ቅዱስ / ክፍል ዘጠኝ

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ
                                              ቅዳሜ ነሐሴ 3/ 2006 ዓ.ም
ቃሉ ይተረጎማል
መጽሐፍ ቅዱስ የሚነበብ፣ የሚጠና፣ የሚመረመር ብቻ ሳይሆን ወደ ሕይወታችንም እየተረጎምን የምንማርበት፣ የምንገሰጽበት እንዲሁም የምንመከርበትም ነው፡፡ ሕይወታችንን ካላየንበት፣ ካልተጽናናንበትና ካልተለወጥንበት፣ ለንስሐና ለበጎ ሥራ ካልተነቃቃንበት ትክክለኛ ዋጋውን አያገኝም፡፡ ምክንያቱም የእምነት እንጂ የዕውቀት መጽሐፍ አይደለምና ነው፡፡
የመናው ሕግጋት
የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር ሲወጡ የገጠማቸው በረሃ ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር መናንና ውሃን አዘጋጀላቸው፡፡ እነዚህ የተአምራት ምግቦች ናቸው፡፡ ተአምራት ማለት ማግኘት በሚቻልበት ቦታና ሰዓት ያልተገኘን ነገር ማግኘት በማይቻልበት ሰዓትና ቦታ ማግኘት ነው፡፡ ምግብ የሚገኘው ከምድር ነው፤ ከሰማይ ግን መና ወረደ፡፡ ውሃ የሚገኘው ከምንጭ ነው፤ ከዓለት ላይ ግን ውሃ ፈለቀ፡፡ ወረደና ፈለቀ የሚሉት ቃላት ራሳቸው የተአምራት ማብራሪያዎች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር አውጥቶ በምድረ በዳ ላይ የሚጥል አምላክ አይደለምና ለእስራኤል መናን አወረደላቸው፣ ውሃን አፈለቀላቸው፡፡ መናው የራሱ የሆኑ ሕግጋት እንደነበሩት በዘፀአት 16 ላይ እናነባለን፡፡ የመናው ሕግጋት አራት ናቸው፡-

1.      በየዕለቱ መልቀም
2.     በየማለዳው መልቀም
3.     አለማሳደር
4.     ለሰንበት መልቀም ናቸው፡፡
1-   በየዕለቱ መልቀም
የመናው  የመጀመሪያው ሕግ በየዕለቱ የሚበቃቸውን ያህል መልቀም ነው፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ክንድ በየዕለቱ ያያሉ ማለት ነው፡፡ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ቃል በየዕለቱ መመገብ ይኖርብናል፡፡ ቃሉ የህልውና ጉዳይ እንጂ የአማራጭ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሰው ለመኖር እንጀራ የሚያስፈልገውን ያህል ቃሉም ያስፈልገዋል፡፡ ለሆዱ እንጀራ፣ ለመንፈሱም ቃለ እግዚአብሔር ያስፈልገዋል፡፡ እንጀራ ሆድን እንጂ መንፈስን መሙላት በፍጹም አይችልም፡፡ ዛሬ ያለነው ትላንት በበላነው አይደለም፡፡ ለዛሬ ዛሬ መመገብ ግድ ነው፡፡ እንዲሁም ትላንት ባነበብነውና በሰማነው ቃል አንኖርም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ዕለታዊ ፍላጎት ነው፡፡ ስለዚህ በየዕለቱ መመገብ ያስፈልገናል፡፡ ጌታችን፡- “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” በማለት በኦሪት የተነገረውን ቃል አጽንቶታል (ማቴ. 4፥4፤ ዘዳ. 8፥3)፡፡
በቀን ውስጥ ለመመገብ ቢያንስ ሁለት ሰዓት እንመድባለን፡፡ ለመዋብ ቢያንስ ሠላሳ ደቂቃ እንፈጃለን፡፡ ጋዜጣ ለማንበብና ዜና ለመስማት ቢያንስ አርባ አምስት ደቂቃ እንወስዳለን፡፡ ለመኝታ ቢያንስ ስምንት ሰዓት ያስፈልገናል፡፡ ከሁሉ የሚበልጠውን ቃሉን ለማንበብ ግን ሠላሣ ደቂቃ ጊዜ የለንም፡፡ በአንድ ወቅት ለእስረኞች መጽሐፍ ቅዱስ ለመለመን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ሄድን፡፡ በወቅቱ የነበሩ ኃላፊም፡- “አብያተ ክርስቲያናት የሶፍትና የሳሙና በጀት አላቸው፣ መመሪያቸው የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ግን በእርዳታ ለማግኘት እንጂ ለመግዛት አሳብ የላቸውም፡፡ እናንተም ከሁሉ የበለጠውን መጽሐፍ ለመግዛት በጀት ያስፈልጋችኋል” በማለት መከሩን፡፡ ለቃሉ የሰጠነው ጊዜ፣ የመደብነው በጀት አነስተኛ መሆኑ ዛሬም ድረስ ይሰማኛል፡፡ ለዓለም የመደብነው ጊዜ ሰፊ ነው፤ እርካታው ግን አነስተኛ ነው፡፡ ለጸሎትና ለቃሉ የምንመድበው ትንሹ ሰዓት ግን እርካታው ብዙ መሆኑን ማን በነገረን!


2. በየማለዳው መልቀም
መናው ከመውረዱ በፊት ውርጭ ይመጣና ሰፈሩን ያለብሰዋል፡፡ ያሉበት ስፍራ በረሃ ስለሆነ መና የማር እንጎቻ የሚመስል በመሆኑ በቀላሉ ሊቆሽሽ ይችላልና እግዚአብሔር የውርጭ ገበታ ያነጥፍላቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ መናው በገበታው ላይ ይወርዳል፡፡ ልዩ እንክብካቤ! እነርሱም በማለዳ ተነሥተው መልቀም አለባቸው፡፡ መናው ቀለል ያለ ምግብ፣ የተጣራም ገንቢ ምግብ፣ እንደ ማር እንጎቻም ያለ በመሆኑ ፀሐይ ከወጣ ይቀልጣል፡፡ ስለዚህ በማለዳ መልቀም ነበረባቸው፡፡ እንዲሁም የቀኑን ፕሮግራም ከመንደፋችን፣ ለሥራም ከመጣደፋችን በፊት ባጠቃላይ ፀሐይ ሳይወጣ የዓለም ፕሮግራም ሳይጀመር የቃሉን መና መልቀም አለብን፡፡ በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገር እግዚአብሔርም በቃሉ ሲናገረን በመስማት የቀኑን ቀለብ ልንሰበስብ ይገባል፡፡ ፀሐይ የተባለው የሥጋ ሩጫ ከተጀመረ ግን መናውን መሰብሰብ አይቻልም፡፡ የቀኑን ሩጫ ከመወሰናችን በፊት ቀኑን በቃሉ መክፈት ያስፈልጋል፡፡ ፀሐይ ከወጣ ግን መናው ይቀልጥብናል፡፡ ቀኑን በጉልበት መዋል አይቻልም፡፡ እንዲሁም ቃሉን ሳይመገብ የሚሰማራ ሰው መንፈሳዊ ብርሃኑን መጠበቅ አይችልም፡፡ የማይበላ ሰው ለመታመም ብሎም ለመሞት እንደሚደርስ እንዲሁም ቃሉን የማይመገብ ሰው ወደ ኋላ ለማለት ቀጥሎም ለመካድ ይደርሳል፡፡
3.አለማሳደር
መናውን ዕለት ዕለት መመገብ ይገባል፡፡ ካደረ ይበላሻል፡፡ እንዲሁም የእግዚአብሔር ቃል የሚያዝዘንን በየዕለቱ መፈጸም ተገቢ ነው፡፡ ቃሉ የሚመጣው ራሱን ከሚያስፈጽምበት ኃይል ጋር ነው፡፡ ፈጥነን ከታዘዝን ኃይሉ ይረዳናል፡፡ ቆይ ለነገ ካልን ግን ኃይሉ ይሄድና ትእዛዙ ብቻ ይቀራል፡፡ ደግመን ስንሰማው እንለምደውና ከመታዘዝ እንዘገያለን፡፡ ደጋግመን የሰማነው ቃል እንደ ፈርዖን ልባችንን ያደነድነውና በመጨረሻ ለውድቀት ይዳርገናል፡፡
ሰዎችም ወደ ክርስትና የሚመጡት የቃላችን ምስክርነት ብቻ ሳይሆን የኑሮችን ምስክርነትም ሲስባቸው ነው፡፡ የምንናገረውን ቃል የገዛ ኑሮአችን ከተቃወመ ከተነሡብን ነቃፊዎቻችን በላይ አስፈሪ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተን የምንናገረው ሳይሆን ኖረን የምንናገረው የሕይወት መጽሐፍ ነው፡፡ አጥንተው ቢናገሩ የፖለቲካ ሰዎች ከእኛ በላይ መናገር ይችላሉ፡፡ ቃሉ ግን የሕይወት ምስክርነትን የሚፈልግ ነው፡፡ የኬንያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጆሞ ኬንያታ፡- “ከሁሉ አብልጬ የምወደው መጽሐፍ ቅዱስን ነው፤ ከሁሉ አብልጬ የምጠላው ሰባኪን ነው፡፡ የሚያስተምረውን አያደርገውምና” ብለዋል፡፡
1.   ለሰንበት መልቀም
የእስራኤል ልጆች በሰንበት መናን መልቀም አይችሉም ነበር፡፡ መናን በሰንበት ቢፈልጉም አይወርድም ነበርና በከንቱ ይለፋሉ፡፡ ስለዚህ በስድስተኛው ቀን ለሰባተኛው ቀን ደርበው ይለቅሙ ነበር፡፡ እንዲሁም የእግዚአብሔር ቃል ስጦታና ዕድል ነውና ሁልጊዜ አይገኝም፡፡ ስለዚህ ዛሬ ቃሉ ብሉኝ ብሉኝ ሲል አብዝተን መመገብ ይኖርብናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንኳ የሚከለከልበት ዘመን እንደነበር ያለፈው ዘመን ያስተምረናል፡፡ በኮሚኒዝም ርእዮተ ዓለም ብዙ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ተነጥቀው ወደ ወኅኒ ስለተጣሉ በቃላቸው የሚያስታውሱትን ጥቅስ እየተለዋወጡ ይጽናኑ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በቃል ማጥናት ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑ ያን ጊዜ ታይቷል፡፡ እንዲሁም የቃሉ ረሀብ የሚነሣበት ዘመን ይመጣልና ዛሬ ተግተን ማንበብና መማር ይገባናል (አሞጽ. 8፥11)፡፡
ብዙ ጊዜ ቃሉን ስንሰማና ስናነብ በወቅቱ ካለንበት ሁኔታ ጋር ግንኙነት ያለው የማይመስለንን ነገር ልንሰማና ልናነብ እንችላለን፡፡ ነገር በማስተዋል መመርመር ይገባናል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ለዛሬ የዕለት እንጀራን ሲሰጥ፣ ለነገ ደግሞ የቃል ስንቅን ያዘጋጃልና ተግተን መሰነቅ ይገባናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ባደረግነው ኃጢአት በቃሉ እንወቀሳለን፡፡ በዚህ ነገር ፈጥነን ንስሐ መግባት ይገባናል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ስለሌለንበት ስህተት ሲነገር ስንሰማ ቸለል እንል ይሆናል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር አርቆ ለማጠር ስላልሠራነውም ኃጢአት ይናገራልና ማስተዋል ይገባናል፡፡
                                                                 -ይቀጥላል-
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ