የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሙሴኒ

                                                             እሑድ የካቲት 27/2008 ዓ.ም.
የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ባርነት የወጡበት አወጣጥና የሰው ልጆች ከሲኦል ግዞት ነፃ የወጡበት አወጣጥ ተመሳሳይነት ወይም ተመጋጋቢነት አለው፡፡ እስራኤል ከግብፅ ባርነት ከመውጣታቸው በፊት ብዙ ተአምራት ተፈጽሟል፡፡ እንዲሁም የሰው ልጆች መዳን በመስቀል ላይ ከመፈጸሙ በፊት ጌታችን ድውይ በመፈወስ፣ እውር በማብራት፣ ሙት በማስነሣት ብዙ ተአምራቶችን ፈጽሟል፡፡ በግብፅ ምድር ላይ የተከናወነው ዘጠኙ ተአምራት እግዚአብሔር ኃይሉን ለፈርዖን የገለጠበት ሲሆን የፋሲካው በግ ግን ለእስራኤል ፍቅሩን የገለጠበት ነው፡፡ እንዲሁም ጌታችን ኃይሉን በተአምራት ቢገልጥም በመታረዱ ግን ፍቅሩን ለእኛ ገልጦልናል፡፡ የፋሲካው በግ እስራኤል ከሞትና ከጭንገፋ የዳኑበት ሲሆን የክርስቶስም ሞት ከዘላለም ጥፋት ያመለጥንበት ነው፡፡
እስራኤል በሙሴ መሪነት ከግብፅ ወጥተዋል፡፡ እኛም በክርስቶስ አዳኝነትና ፊታውራሪነት ከሲዖል አምልጠናል፡፡ እስራኤል ባሕረ ኤርትራን እንደ ተሻገሩ እኛም የሞትን ባሕር ተሻግረናል፡፡ እስራኤል ከፈርዖን አገዛዝ ነፃ እንደወጡ እኛም ከዲያብሎስ ግዞት ነጻ ወጥተናል፡፡ ሙሴ በሲና ተራራ ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት እንደ ጾመ ኢየሱስም ዐርብ ቀንና ሌሊት ጾሟል፡፡ ሙሴ ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ኦሪትን እንዳወጀ እንዲሁም ኢየሱስ ከጾሙ በኋላ የመንግሥትን ወንጌል አውጇል፡፡
 ሙሴ የክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ምሳሌ በባሕርይው አናሳ ነው፡፡ እንዲሁም ምሳሌ የሆነው ሙሴ ከክርስቶስ በግድ ያንሳል፡፡ ሙሴና ክርስቶስ የሚመሳሰሉበት፡
·       ሙሴ ያለ አገሩ በስደት ምድር ተወልዷል፣ እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ባሕርዩ ሰው ሆኗል፡፡ ሰማያዊ አምላክ ምድራዊ ሆኗል፡፡
·       የሙሴ እናት ከቤተመንግሥት እየተከፈላት ልጇን አጥብታለች፡፡ እንዲሁም እመቤታችን ድንግል ማርያም የዓለሙን መጋቢ በማጥባቷ ከሰማይ መንግሥት ክብር አግኝታለች፡፡
·       ሙሴ ከፈርዖን ፊት እንደ ተሰደደ ኢየሱስ ከሄሮድስ ፊት ተሰዷል፡፡
·       ሙሴ የእስራኤል የመጀመሪያው መሪ እንደሆነ ክርስቶስም የቤተ ክርስቲያን መሥራችና ራስ ነው፡፡
·       ሙሴ የብሉይ ኪዳን መካከለኛ እንደነበረ ክርስቶስም የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው፡፡
·        ሙሴ ነቢይ፣ ካህንና መስፍን እንደ ነበረ ክርስቶስም የሦስቱ መዐርጋት ባለቤት ማለትም ነቢይ፣ ካህንና ንጉሥ ነው፡፡
·         ሙሴ መቃብሩ እንዳልተገኘ ክርስቶስም መቃብሩ ባዶ ነው፡፡
 ራሱ ሙሴ ስለ ክርስቶስ፡ ‹‹እግዚአብሔር ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል፤  እርሱንም ታደምጣለህ›› በማለት ትንቢት ተናግሯል (ዘዳ. 18÷16)፡፡ ይህ ትንቢት በክርስቶስ መፈጸሙን በሐዋ.ሥራ 3÷22 ላይ ተጽፏአል፡፡
ምንም እንኳ ሙሴ ለክርስቶስ ምሳሌ ቢሆንም የጌታችን ተግባሩና ኑሮው ግን ከሙሴ ይልቃል፡፡ ሙሴ እስራኤልን ነጻ ያወጣው በግ አርዶ ነው፣ ክርስቶስ ግን ራሱ ታርዶ ነው፡፡ ሙሴ እስራኤልን ነጻ ያወጣው ከጊዜያዊ ጠላት ነው፣ ክርስቶስ ግን ከዘላለማዊ ጠላት ነው፡፡
ጌታችን የጾመው ጾም ወይም ዐቢይ ጾም ብለን የምንጠራው የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ ወይም ሙሴኒ ይባላል፡፡ ሙሴ ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ኦሪትን እንደተቀበለ ጌታችንም ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ወንጌልን ወይም አዲስ ኪዳንን እንደ መሠረተ ለማሰብ ሳምንቱ ሙሴኒ ተብሏል፡፡ ብሉይን ከአዲስ አስማምቶ ማሰብና መተርጎም በእውነት መታደል ነው፡፡ የእግዚአብሔርን የዛሬውን ብቻ ሳይሆን የጥንት ተግባሩንም ማሰብ በረከት ነው፡፡ ይህን የደነገጉ አባቶች የታደሉ ናቸው፡፡
 የጾሙ ዓላማ መንፈሳዊ ሕይወታችንን ለማደስ ነው፡፡ ጾም የሕይወት ፀደይ ነው፡፡ ፀደይ ከወቅታቱ ሁሉ የተለየ እጅግ አስደሳች ወቅት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ባሕረ አሳብ መሠረት በበጋ ወቅት የሚውለው ዐቢይ ጾም 55 ቀኖች አሉት፡፡ የጾሙ መሠረት ጌታችን የጾማቸው 40 ቀኖች ሲሆኑ፣ በመነሻው የመዘጋጃ 7 በመድረሻው የሚገኙት ስምንት የሕማማት ቀኖች ተደምረው ዐቢይ ጾም 55 ቀኖች ያደርሱታል፡፡ ሁዳዴ የሚል ሌላ መጠሪያ ያለው ጾም የሚውለውም በዘወረደ (ቅበላ) እሁድና በትንሣኤ መካከል ነው፡፡
የዐቢይ ጾም ሦስቱ ክፍሎች
1)     የመዠመርያው ክፍል ሙሴኒ ይባላል፡፡ ምሳሌነቱን ከነቢዩ ሙሴ ይወስዳል፡፡ አሰርቱ ቃላተ ኦሪትን ከእግዚአብሔር በደብረ ሲና ከመቀበሉ በፊት እንደጾመው (ዘፀአት 2415-18) እኛም በርሱ ምሳሌነት የጌታን አርባ ቀኖች ለመጾም እንደ ቅዱስ ያሬድ አጠራር ‹‹ሙሴኒ›› ብለን እንጾማዋለን፡፡ በኋለኛው ዘመን 15ኛው ምእት ዓመት ላይ ሕርቃል(610-641) ታከለበት እንጂ መሠረቱ ዘወረደ ሙሴኒ ነው፡፡ ሳምንቱ ሙሴን እንጂ ሕርቃልን እንደማያስብ ምስባኩና ምንባቡ ይገልጻል፡፡
2)     ኹለተኛው ክፍል ጾመ ኢየሱስ ይባላል፡፡ ዐርባ ቀኖች ይጾምበታል፡፡ ከቅድስት ሰኞ ተነሥቶ ከሆሣዕና በፊት እስከሚገኘው ዓርብ ድረስ ይቆያል፡፡
3)     ሦስተኛው ክፍል ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡ ከሆሣዕና ዋዜማ ቅዳሜ እስከ ትንሣኤ ዋዜማ ይጾማል፡፡
 በዚህ የጾም ጊዜ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲን በዜማ ብቻ የምታደርሰው ሥርዓተ ጸሎት ጾመ ድጓና ምዕራፍ በተባሉ የዜማ መጻሕፍት በተዘጋጀው መርሐ ግብር መሠረት ነው፡፡ ዐቢይ ጾም እስኪፈጸም ድረስ በየቀኑ የሚጸለይበት ክፍለ ጊዜም እንዲህ ነው፡
1.      የነግህ ጸሎት /ምስጋና/
2.      የሠለስት ጸሎት /ምስጋና/
3.      የቀትር ጸሎት /ምስጋና/
4.      የተሠዓት ጸሎት /ምስጋና/
5.      የሠርክ ጸሎት /ምስጋና/ ተብሎ የተመደበ ነው፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ