የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ማለቂያ የሌለው እኔ

 በአገር ላይ ጦርነት ተነሥቶ ዘጠኝ ባልንጀሮች በአንድነት ዘመቱ ። ጦርነቱ አይሎ ስለ ነበር ስምንቱ ሞተው አንዱ ብቻ በሰላም ተመለሰ ። የጦርነቱ ማየል ፣ የስምንቱ መሞት ፣ የአንዱ በሰላም መመለስ የሰሙ ዘመድ አዝማድ በሕይወት ወደ ተመለሰው ሰው ጋ ሄደው፡- “ለመሆኑ ጦርነቱ እንዴት ነበር ?” አሉት ። እርሱም ኮራ ፣ ደራ ብሎ “ጦርነቱ ያን ያህል አስፈሪና አስከፊ አልነበረም ፣ ዘጠኝ ሆነን ዘምተን እኔ ብቻ ተመልሻለሁ” አለ ይባላል ። 

የባልንጀሮች ፍቅር የሚኖረው አገር ሲኖር ነው ። አገር በሌለበት መፋቀርም የለም ። የባልንጀርነት ፍቅር ዘላቂ የሚሆነው የአገር ፍቅር ሲኖር ነው ። ብዙ ባልንጀሮችና ትዳሮች የአገር ሳይሆን የጎጥ ፍቅር በመምረጣቸው ተለያይተዋል ። አገር ሁሉን የሰበሰበች ጥላ ናት ። አንድነት የሚለው ቃል የሚቀጸለው ብዙዎች በአንድ አሳብ ለመስማማት ሲወስኑ ነው ። የጋራ አሳብ የሌለው ሕዝብ ይወድቃል ። አንድ ሰው አንድ ነው ይባላል እንጂ አንድነት አለው አይባልም ። አንድነት ማጣፋት ሳይሆን ኅብረት ነው ፣ መተባበር ነው ። 

ያደጉ አገሮች ለሕፃናቱ የአገርን ፍቅር ያስተምራሉ ። የቀደሙ አባቶቻቸውን መልካም ታሪክ አጉልተው ያሳያሉ ። እኛ ጋ ስንመጣ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሕፃን የሕንድ ትምህርት ቤት የሚማር ከሆነ የሕንድ ጀግኖችን ታሪክ ይማራል ። በገዛ አገሩ ተሽጦ ያድጋል ። “ድንጋይ መወርወርና አማርኛ መናገር ክልክል ነው” የሚል ትልቅ ማስታወቂያ የለጠፈ አንድ ትምህርት ቤት ከተማችን ላይ እንደ ነበር እናውቃለን  ። የምዕራባውያን ወንጌል ሰባኪዎችም “አገራችን በሰማይ ነው” በሚል ፈሊጥ ብሔራዊ ስሜት እንዳይኖር ብዙ ሥራ ሠርተዋል ። አፍሪካን የወረሩት አገራችን በሰማይ ነው እያሉ እየሰበኩ ፣ ከኋላ ጦር እያስከተቱ ነው ። ራሳችንን ጠልተን እነርሱ የለበሱትን እንድንለብስ ፣ የራሳችንን ታሪክ ደምስሰን ዛሬ እንደ ተፈጠርን ሆነን እንድናምን ብዙ ጥረዋል ። ክፋቱ የተሳካበት ስፍራም ይታያል ። ዛሬ ሁከት ያለባቸው ስፍራዎች ሁሉ ሚስዮናውያን የረገጡት ቦታ ነው ። እነርሱ ግን ሲሰብኩ በሚሰብኩበት አደባባይና አትሮኖንስ ላይ የአገራቸውን ባንዲራ ተክለው ነው ። እኛን አገራችሁ በሰማይ ነው እያሉ ባንዲራ ያስጥላሉ ፣ እነርሱ ግን ከወንጌል ጋር አጣምረው ይሰብኩታል ። በደቡብ ኢትዮጵያ የገቡ ሚስዮኖች “ከአራተኛ ክፍል በላይ መማር ኃጢአት ነው” እያሉ ይሰብኩ ነበር ። አንድ ዶክተር ይህ ስብከት ደርሶባቸው ነበርና የሚስዮኑ ልጅ ስምንተኛ ክፍል በመግባቱ በቸርች ውስጥ ጸሎት ይዘን ነበር ብለውኛል ። “የሰባኪው ልጅ ገሀነም እንዳይገባ በብርቱ እናለቅስ ነበር” በማለት አጫውተውኛል ። ሰማይን የተቀበልነው በምድር አገራችን ላይ ሆነን ነው ። ዛሬ ወንጌል ገባን በሚል ስም ምንም የአገር ስሜት የሌላቸው እንደውም ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አምርረው የሚጠሉ ወጣቶች እያየን ነው ። ስለ አገሩ ስለ ቤተ ክርስቲያኑ የሚናገር ከተገኘ እገሌ ይሸቃቅጣል ፣ ንጹሕ ወንጌል አይሰብክም ይላሉ ። “ኢየሩሳሌም ሆይ ፥ ብረሳሽ ፥ ቀኜ ትርሳኝ ። ባላስብሽ ፥ ምላሴ በጕሮሮዬ ይጣበቅ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ” የተባለው እኮ ስለ ብሔራዊ ስሜት አይደለም ወይ ?” /መዝ. 136 ፡ 5-6 ።/ አገራችን በሰማይ ነው ያለው ጳውሎስ፡- “ብዙ ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት በልቤ አለብኝ ስል በክርስቶስ ሆኜ እውነትን እናገራለሁ ፤ አልዋሽምም ፤ ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል ። በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ሆኑ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና” ብሎ የለም ወይ ? /ሮሜ. 9፡1-3/ ። ነጠላ ለብሶ የሚያስተምረውን እያወገዝን ሱፍ ለብሶ የሚያስተምረውን ካደነቅን የፈረንጅን የኢንዱስትሪ አብዮት እያሟሟቅን አይደለም ወይ ? አገር የምንኖርላት ብቻ ሳይሆን የምንሞትላትም ናት ። 

የአገር ፍቅር የሚገባን ከአገር ስንወጣ ነው ። ፀሐይ የሞቅንባት ድንጋይ ሳትቀር ትናፍቃለች ። የአገር ዋጋ የሚገባን አገር የሌላቸውን ሕዝቦች ስናይ ነው ። ዛሬም አንድ ጥቁር አፍሪካዊ ነጭ ሲያይ ይንቀጠቀጣል ። እመቤቴ ጌታዬ ይላል ። ለነጭ የማይርገበገብ ጥቁር ሲያዩ ራሳቸው ነጮቹ “ኢትዮጵያዊ ነህ ?” ይላሉ ። የነጻነት ዋጋው ትልቅ ነው ። አፍሪካውያን የራሳቸውን ቋንቋ አጥተው የፈረንሣይና የእንግሊዝ ቋንቋ ተናጋሪ ሁነዋል ። እኛ በራሳችን ቋንቋ ስንናገር ይቀኑብናል ። እኛ ደግሞ እንግሊዝኛ ባለመናገራችን ሐፍረት ይሰማናል ። አባቶቻችን ለነጻነት ዋጋ ባይከፍሉ ኑሮ ዛሬ ስማችን የጣሊያንና የሌሎች ሕዝቦች ስም ይሆን ነበር ። ምንም ረሀብተኛ ሕዝቦች ብንሆንም የበታችነት ስሜት እንዳይሰማን አባቶች የከፈሉት ዋጋ ሊታወስ ይገባዋል ። 

ጦርነት የሚያስከፍለውን ዋጋ ስናይ ምክንያቱ ትንሽ ሁኖ እናየዋለን ። የሰው አገር ለመውረር ብለው የሚሞቱ ምክንያትና እውነት ስለሌላቸው ደስታ የላቸውም ። ፍላጎታቸው ቁሳዊ ዘረፋ ብቻ ነው ። ለነጻነታቸው የሚሞቱ ግን እውነትና ምክንያት ከእነርሱ ጋር ናትና በደስታ ይሠዋሉ ። በጽናት የሚያዋጋ እውነትና ምክንያት ነው ። እውነትና ምክንያት የሌለው ትልቅ መሣሪያ ቢይዝም አያሸንፍም ። 

በአገር ላይ አብረው የበሉ የጠጡ ባንጀሮች አገር ስትጠቃ ደግሞ አብረው ሊዘምቱ ፣ ታሪካቸውን በወርቅ ቀለም ሊጽፉ ፣ በአንድ ላይ እንደኖሩም በአንድ ላይ በክብር ሊያርፉ ይገባል ። ነጻነት የሌላቸውን ልጆች ከመውለድ አለመውለድ የተሻለ ነው ። አጋር ልጅዋን በባርነት ሳለች በመውለዷ ምንም የአብርሃም ልጅ ቢሆን ከቤት ተባሯል ፣ አገር ለቆም ሂዷል ። ከትልቅ ሰው ከመወለድ በነጻነት አገር ላይ መወለድ ይበልጣል ። አገር ስሜቱ ጥልቅ ነው ። ጣልያን ያልጨረሰውን አጀንዳ ለመጨረስ ብሔራዊ ስሜቴን ያጠፉ መሪዎች ትውልድን በሱስና በሞራል ውድቀት ተንቀሳቃሽ ሬሳ አድርገውታል ። 

ስምንቱ አልቀው የተረፈው አንዱ ከሆነ ጦርነቱ አስፈሪ ነበር ። ጦርነቱን ግን በራሱ መትረፍ ብቻ የለካው ፣ የባልንጀሮቹ ሞት ያላሳዘነው ያ ሰው ጀግና ነኝ ለማለትና እኔ ከተረፍኩ ቀላል ነው በማለት ዜናውን እንዳነበበ ሰምተናል ። ከራስ ነገር አንጻር ብቻ ቀኑን ፣ ዘመኑንና ሁኔታዎችን መለካት በእውነት አለመታደል ነው ። የችግሩን ብርታት ለመለካት የራስን ደህና መሆን አንዱ ሰሐን ላይ አውጥቶ መመዘን ራስ ወዳድነት ነው ። 

ዛሬ በወንጌል ስም እየተሰበከ ያለው ደረቅ የሥነ ልቡና ፍልስፍና ነው ። ትችላለህ ፣ እምቅ ኃይል ውስጥ አለ የሚለው የወንድነት ትምህርት ነው ። የሳይኮሎጂ ቅኝቶች የሌለ ዓለም የሚፈጥሩና ለፍላፊ የሚያደርጉ ናቸው ። ብዙ ሰው እያለቀም አስፈሪ አይደለም ማለት ፣ ወገን እየረገፈም “ያን ያህል ነው” የሚል ክርስቲያን ማትረፍ እኔነትና ወንጌል መሳይ ስብከቶች ያመጡት ጣጣ ነው ። ጌታ አልዓዛርን እንደሚያስነሣው እያወቀ አልቅሷል ። ከአርባ ዓመት በኋላ ለምትፈርሰው ኢየሩሳሌምም አልቅሶላታል ። የዚህ ሩኅሩኅ ተከታዮች እንዴት ጨካኝ ይሆናሉ ? በመከራ ሰዓት እንኳ ቤተ ክርስቲያን ስትቃጠል ፣ ምእመናን ሲታረዱ እግዚአብሔር ያጽናችሁ ለማለት አለመቻላቸው ያሳዝናል ። እንዲህ ዓይነት ስሜት በውስጣችን ካለ መመርመርና ማውጣት ይገባናል ። ክርስቲያን ለመሆን መጥተን ሰብአዊነትም ከተለየን አስቸጋሪ ነው ። 

የሱነም ሴት ደህና ነው ያለችው ለእግዚአብሔር ሰው ለመንገር እየገሰገሰች ነው ። በሞተ ተስፋዋ ላይ ልጅ የሰጣት እግዚአብሔር በሞተው ልጇ ላይ ሕይወት እንደሚሰጥ ስላመነች ነው ። ለማይመለከተው ሰው ደህና ነው አለች ። የሞት ነገር የሚመለከተው እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ለእርስዋ ኤልሳዕን ማግኘት እግዚአብሔርን እንደ ማግኘት ነበር ። ዛሬ ያለው ስሜት አልባነት ፣ አዘኔታ የራቀው መንፈሳዊነት እንደገና መፈተሸ አለበት ። እኛ ተርፈናል ፣ ስለሞቱት ግን ማሰብ ፣ ምን እንሥራ ማለት ያስፈልገናል ። እኛ ስንጠግብ ሌሎች በረሀብ ቢረግፉም “ያን ያህል ከባድ አይደለም” ማለት ራስ ወዳድነት ነው ። ብዙ ነገሮች እኔ ከሚለው መለኪያ አልወጡምና ማዘን አልቻልንም። የሌሎችን ሞት እያቃለልን የእኛን ጉንፋን እናብራራለን ። ማለቂያ የሌለው እኔ ! 

ጌታ ሆይ ስለ ሌሎች የማስብበትን ፍቅር ስጠኝ ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ