በዚህ ዘመን ላይ ሰዎች አንድ ነገር ሲፈልጉ ዕረፍት ያሳጡናል፣ ያንን ካገኙ በኋላ ይረሱናል የሚል ትዝብት እየበዛ ነው:: ከዚህ ሁለት ነገሮችን እንማራለን፦ ሰውን ስለ ሰውነቱ መፈለግ እንዳለብንና ላደረገልን ነገር ምስጋን ማቅረብ እንደሚገባን ነው። ማመስገንን የምናገኘው የመጀመሪያው በአስተዳደግ ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን ለተደረገላቸው ነገር እንዲያመሰግኑ ማስተማር አለባቸው። ወላጅ የበደለውን መካስ በጣም ጊዜ ይወስዳል። ሁለተኛው ትምህርት ነው፣ ትምህርት ከጨለማ ለመውጣት፣ ከድንዛዜ ለመንቃት የሚያግዝ ነው። እዚህ ላይ ትምህርት የሚያደንዘውና ጨለምተኛ የሚያደርገው ለበታችነት ስሜት የሚዳርገው አያሌ ሰው አለ። ፈሪሀ እግዚአብሔር ፣ ግብረ ገብ የሌለበት ትምህርት ካለመማር የሚሻል አይደለም።
ሦስተኛው ዕድሜ ምስጋናን ያስተምራል። ትልቅ ሰው ማለት ለተደረገለት ትንሽ ነገር ትልቅ ዋጋ የሚሰጥ ነው። ስልክ ለደወለለት፣ መጥቶ ለጠየቀው፣ ትንሽ ስጦታ ለሰጠው ሰው ዋጋ ይሰጣል። ቁሳዊና ጥቅመኛ ያልሆነ ትልቅ ሰው የሰጡኝ ወርቅ ነው አርቴፊሻል አይልም፣ ዋናው ማሰቡ ነው ብሎ ዋጋ ይሰጣል። ሣር ቢያመጡለት በደስታ ይቀበላል፣ ለምለም ሁኑ ብሎ ይመርቃል። በርግጥም ዋናው ማሰቡ ነው። አራተኛ ለምስጋና የሚያበቃን መንፈሳዊነት ነው፣ መንፈሳዊነት እንኳን ስለ ተጨበጠው ነገር ስለምትመጣዋ ትንሣኤና ሕይወት የሚያመሰግን ነው። መንፈሳዊ ሰው ለእግዚአብሔር ክብር አለው፣ ስለዚህ ሰዎችን ያከብራል። ጊዜያቸውን ለሰጡት ሰዎች ክብረት ይሰጣል። በዓለም ላይ የሄደ ገንዘብ ተመልሶ ይመጣል፣ የሄደ ጊዜ ግን ተመልሶ አይመጣም፤ ጊዜውን የሰጠን ሰው ትልቅ ነገር የሰጠን ነው።
በጽኑ ሕመም ተይዘን የራሳቸውን ጤና ሳያስቡ ያስታመሙንን ሰዎች ረስተናቸዋል። የቅርብ ልጆቻችንና ዘመዶቻችን ሳይደርሱልን ውኃ ያቀበሉንን ዘንግተናል። ዘረኛ ጭንቅላታችን እነርሱን ለማመስገን አይነቃቃም። ከዳኑልኝ ብለው ደማቸውን የለገሱን ሰዎች አሉ፣ ለአገር ለድንበራቸውም ራሳቸውን የሠዉ አሉ። ግን አናመሰግናቸውም። የአገር ድንበር የታጠረው በጀግኖች አጥንት ነው፣ ሰብሏ የሚበቅለው በወታደር ደም ነው። ለእነዚህ ባለ ውለታዎች ግን ክብርም ምስጋናም የለንም።
ስብራታችንን የጠገኑ ወጌሻዎች፣ ከሕመም ለመዳን መድኃኒት የሰጡን አዋቂዎች አሉ። ብዙዎቹ አያስከፍሉንም ነበር ። ትምህርትና መድኃኒት ገንዘብ ከገባባቸው የማዳን አቅም የላቸውም። እነዚያን የበሽታችን ተዋጊዎችን ከዳንን በኋላ እንረሳቸዋለን። ያሳደጉን ሞግዚቶች እኛን ሲያሳድጉ የጋብቻም የመውለድም ጊዜ አልፍባቸዋል ፣ ግን ልጅ ሆነን ልንጦራቸው፣ ወገን ሆነን ልንረዳቸው ፈቃደኛ አይደለንም። አለሁ ብንላቸው ታላቅ ምስጋና ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ነበር። እኛ ተኝተን ደጁን የሚጠብቁ ዘቦችን አናመሰግናቸውም ፣ ሰላምታ ለመስጠት ዝቅ ያልን ይመስለናል ፣ እንደውም ስናያቸው እንበሳጫለን። ሰው ወዳጁን፣ አጋዡን አያውቅም። በሬ ካራጁ እንዲውል ሰውም የሚውለው ከሚሸነግለው ጋ ነው። እኛ ልንሠራ የማንችለውን የሚሠሩልን ሠራተኞች፣ የቤታችንን ቆሻሻ የሚደፉ እነዚያ ምስኪኖች አመስግኑን ፣ አትናቁን እያሉ ናቸው::
ወላጆች የማይቆጠር ነገር አድርገዋል ፣ ያላደረጉት ነገርም ምክንያት አለው። ያልተደረገውን አንድ ነገር የሚያስቡ ልጆች የተደረገውን ሚሊዮን ነገር ማስታወስና ማመስገን አይችሉም። ብዙ የለፉ ሰዎች ልፋቴ ከንቱ ነው የሚል ማጉረምረም ውስጥ ገብተዋል። ምክንያቱ የእኛ አለማመስገን ነው። በልጅነታችን በጣም የሚወዱን፣ እኛን ለመሳም ከሩቅ የሚመጡ ነበሩ። አንዳንዶቹ መካን ናቸው ፣ ምናለ ልጅ ብንሆናቸው ? ብንጠይቃቸው በጣም ደስታ እናገኛለን።
እግዚአብሔር ምስጋና ቢስነትን አይወድም። በዕድሜ ውስጥ እንደምንማረው ገመድ ያስጣልናቸው ፣ ከሞት የተረፉት እኛን ለመግደል ሸምቀቆ ሲስቡ ይታያሉ። ከማመስገን ርቀው ወርቅ ላበደራቸው ጠጠር የሚመልሱ፣ ያልታደሉ ራሳቸውን ለሰይጣን አሳልፈው የሰጡ ሰዎች አሉ። ሳጥናኤል የወደቀው ባለ ማመስገን ነው። የማያመሰግን ሰው ይወድቃል።
አመስጋኞች እንሁን! የተጠና ቃል “አመሰግናለሁ Thank you” ማለት ሳይሆን ከልባችን እናመስግን !
ያልተማሩ የምንላቸው ሰዎች ከእግዚአብሔር የተማሩ አዋቂዎች ናቸው። ለተደረገላቸው ነገር በእንባ ጭምር ያመሰግናሉ ፣ መሬት ላይ ወድቀው ለዚያ ሰው ይጸልያሉ። ምስጋና ለሰጪውም ለተቀባዩም ለሁሉም ኃይል ይሰጣል! ማመስገንን እንልመድ!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 16 ቀን 2018 ዓ.ም.