ጌታችን ከሕፃናት ምስጋናን እየተቀበለ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ ። ከአዋቂዎች ይልቅ ሕፃናት ለማመን ፣ ለማመስገን የተሰጡ ናቸው ። እኛ እናስተምራለን ፣ ሕፃናት ይኖሩታል ። እኛ እመኑ እንላለን ፣ ሕፃናት በትክክል ያምናሉ ። እኛ ይቅር ተባባሉ እንላለን ፣ ሕፃናት ከልብ ይቅር ይባባላሉ ። እኛ ማማረርን እናወግዛለን ፣ ሕፃናት ምንም ምሬት የላቸውም ። ምስጋናን በሚመለከት አዋቂዎች ያጉረመርማሉ ፣ አሁን አስፈላጊ ነው ወይ ? ይላሉ ። በዕድሜ የገፉት በይሉኝታ ይያዛሉ ። ወጣቶች ስሜታውያን ይሆናሉ ። ሕፃናት ግን ከልብ ያመሰግናሉ ። ሕፃናት የዕድሜ ለጋዎች ብቻ ሳይሆኑ የተንኮል ለጋዎች የዋሃንን የሚያመለክት መጠሪያ ነው ። የዋሆች መከራ ሲደርስባቸውም ያመሰግናሉ ፣ የክርስቶስ የመስቀል ወዳጅ በመሆናቸው ዕድለኝነት ይሰማቸዋል ። ደግሞም እንደ ኢዮብ እግዚአብሔር ተወራርዶብኝ ይህን መከራ አመጣ ፣ እንዳላሳፍረው ብለው ይጨነቃሉ ። የዋሆች ስለ መጣው ችግር ብዙ አያወሩም ፣ ስለ መፍትሔ ብቻ ያስባሉ ። ምን በድዬ ነው ? በማለት አይመጻደቁም ፣ እርዳታ ይጠይቃሉ ። የይገባኛል ስሜት የላቸውም ፣ የተደረገላቸው ሁሉ በጸጋ መሆኑን ያምናሉ ። ንጉሥ ዳዊት ክብሩን ጥሎ ሲዘምር ፣ ክብሩን ላከበረው አምላክ ሲሠዋ ሚስቱ ሳትቀር ናቀችው ። የፕሮቶኮል ዓለም ማመስገንንም ማልቀስንም ይከለክላል ። ዳዊት ግን ገደብ የሚያልፈው የእግዚአብሔር ውለታ ድንገት ሰወረው ። በእውነት እንደ ዳዊት ከዘመርን እንደ ሜልኮል የሚያሽሟጥጡ ይገጥሙናል ። ከልመናችን በላይ ምስጋናችን ተቃዋሚ አለበት (2ሳሙ. 6፡20) ።
ዳዊትን ሜልኮል እንደ ናቀችው ፣ ሆሳዕና በአርያም የሚሉትን አመስጋኞች የካህናት አለቆች ተቆጡአቸው (ማቴ. 21፡15) ። ጌታችን ግን ከነቢዩ ከዳዊት፡- “ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ ስለ ጠላትህ፥ ጠላትንና ቂመኛን ለማጥፋት” የሚለውን ጠቀሰላቸው ። (መዝ. 8፡2)። ከምስጋናችን ባሻገር ሁለት ወገኖች ይታያሉ ። የሚንቁንና የሚቆጡን ። የሚንቁን ለዚህ ስምረት ይህን ያህል መገረምና ማመስገን አስፈላጊ ነው ወይ ? ድሮስ ምንም ያላየ የድሀ ልጅ ሁሉ ነገር ይገርመዋል ይላሉ ። ሜልኮል የንጉሥ የሳኦል ልጅ ስትሆን ልዕልት ሁና ያደገች አሁን ደግሞ ንግሥት ናት ። ዳዊት የእረኛው የእሴይ ልጅ ነው ። ስሜታውያን መሆን ተከልክሏል ፣ በስሜት ማመስገን ግን ይገባል ። ስሜታችንንም የሰጠን እርሱ ነውና የሰጠንን ሁሉ ማቅረብ ግድ ይለናል ። ካህናቱ ሌሊትና ቀን ሲያመሰግኑ ፣ ዘማርያኑ ለእግዚአብሔር ክብርን ሲሰጡ የሚቆጣ አለ ። እንቅልፍ የሚነሡን ፣ ጸጥታ የሚያሳጡን ለምንድነው ? ብሎ ውስጡን የሚያደድር ይኖራል ። እንደ ሥራ ፈት የሚያይ ፣ ወደ ቤተ እግዚአብሔር የሚገሰግሱትን የመጋፈጥ አቅም እንደ ሌላቸው ፈሪዎች የሚመለከት ብዙ ትዕቢተኛ ወገን አለ ። ሌሎች ሲያመሰግኑ ስንሰማ እኔ ብዙ ተደርጎልኝ ለምን ዝም እላለሁ ? የሚል መንፈሳዊ ቅንዓት ሊሰማን ይገባል ። በእኛ ሥር ያሉ ሕፃናት እያመሰገኑ እኛ ዝም ስንል ፣ የሥራ ረዳቶቻችን ሰንበት ሲያከብሩ እኛ ጥሰን ስንሄድ ሊሰማን ይገባል ። ስድስት ቀን ሮጠን ያላሳካነውን በሰንበት ሮጠን ልናሳካው ነው ?
ዛሬም እግዚአብሔር ምስጋና የሚያገኘው የተናቁ ከሚመስሉት ሕፃናት ነው ። አዋቂዎችማ ክደው እያስካዱ ነው ። ባለጠጎችማ መንፈሳዊውን ኅብረትና ዝማሬ መጽናኛ ፣ ኑሮን ማስረሻ ብለው ይጠሩታል ። ባለሥልጣናት ከተሾሙ ቀን ጀምሮ ወደ ትውልድ ቀያቸውና ቤተ ክርስቲያን መሄድ ያቆማሉ ። እግዚአብሔር አእምሮውን የባረከለት ፣ የትምህርት ዕድል ያገኘ ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን የወጣ አዋቂ እርሱ ማመስገን ይገባው ነበር ። እግዚአብሔር እንጀራ የቆረሰለት ፣ በረከት የሰፈረለት ባለጠጋ ሌትና ቀን መዘመር ነበረበት ። እግዚአብሔር መገፋትን በሥልጣን ፣ መናቅን በሹመት የለወጠለት ንጉሥ ማመስገን ይገባው ነበር ። እግዚአብሔር ምስጋናን የማገኘው ብዙ ካደረግሁለት ወገን አይደለም እያለን ነው ። እንደ ዘረ ቆርጥም መሬት ፣ በልቶ እንደማይጠረቃ ልጅ አምላክን የሚያሳፍሩ ምስጋና የለሾች ናቸው ። አንዳንድ ሰዎች ለእኔ ያደረገውን ለማን አደረገ? ይላሉ ። ደስ የሚል ቋንቋ ነው ። በመጣንበት አስከፊ መንገድ ላይ ላሉት ቸርነት እያደረግን ለእኔ ያደረገውን ለማንም አላደረገም ካልን ምስጋናችን ከመሥዋዕት ጋር ነውና ያርጋል ። ብቻ አምልኮ ያለ መሥዋዕት አያርግም ።
ማመስገኛችን ብዙ ነው ። መጽናት አቅቶን በተንቀጠቀጥን ቀን የደገፈን እግዚአብሔር ነው ። እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን ወስዶ ዕረፍት የሰጠን ያህዌ ነው ። ደጋግሞ የባረከን ፣ ስንነቃ እንጀራን አጠገባችን ያስቀመጠ ፣ ተኝተን ሳለ ለእኛ ሲጋግር ያደረ አማኑኤል ነው ። አሮጌውን ማንነታችንን ወስዶ አዲስ ያደረገን ፣ በጠላቶቻችን ፊት ዘይት የቀባን እርሱ ክርስቶስ ነው ። ዘመን ሳይቆጠርለት ዘመን የሰጠን ፣ ወደ ራሱ የሳበን ፣ የዕለቱ መልካም ዜናችን እርሱ እግዚአብሔር ነው ። ይህች ፀሐይ የኃይል ባለሥልጣን ቢያስተዳድራት ብዙ በከፈልን ፣ የኃይል ማቆራረጥ በገጠመን ነበር ። ለድሃና ለባለጠጋ ፀሐይን በነጻ የሚያወጣ እርሱ ቸሩ መድኃኔ ዓለም ነው ። ፀሐይ ድሀውን ባለጠጋ ነህ ትለዋለች ፣ የወጣችው ፀሐይ ባለጠጋውን ድሀ ነህ ፣ ይኸው በነጻ ትወስዳለህ ብላ ትመክረዋለች ።
ማመስገን ፣ ሲያመሰግኑ ቆሞ ተመልካች መሆን ፣ አመስጋኞችን መቃወም ሦስት ወገኖችን ያሳየናል ። ዳዊት በእግዚአብሔር ውለታ ተነክቶ ሲያመሰግን የናቀችው ሜልኮል እስክትሞት ድረስ መካን ሁና ነበር (2ሳሙ. 6 ፡ 23) ። አለማመስገን ፍሬ አልባ ያደርጋል ፣ በረከትን ያባክናል ፣ ያንከራትታል ። የካህናት አለቆች የሕፃናቱን ምስጋና ቢቃወሙና ቢገፉ ቤታችሁ የተፈታ ወና ሁኖ ይቀርላችኋል ተባሉ (ማቴ. 23 ፡ 38) ። አለማመስገን ቅጣት አለው ። የአምላክ ግብሩ ምስጋና ነውና ግብር አትሸሽጉ !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 20 ቀን 2018 ዓ.ም.