የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ማነው የሚያድነን ?

“መድኃኒታችን እግዚአብሔር” 1ጢሞ. 1፡1
እግዚአብሔር ለዘመናት በአዳኝነቱ ምሥጢር ሲገለጥ ኑሯል ። የሰው ልጆች ከበደል በኋላ ብዙ ዓይነት አደጋ እየተጋፈጡ ስለሆነ አዳኝ አስፈልጓቸዋል ። አዳም ከሞት የሚያድን አምላክ ከመፈለጉ በፊት ከሐፍረትና ከፍርሃት የሚያድን መድኃኒት ሽቷል ። አዳምና ሔዋን በበደል እኩል ቢሆኑም እርስ በርሳቸው ተፋፍረዋል ። በደል ከኅሊና ፊትም ስደተኛ ያደርጋል ። እግዚአብሔር ከሐፍረትም ያድናል ። ማፈር በሰውና በእግዚአብሔር ፊት መቆም አለመቻል ነው ። ከዚህ ሊያድን የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው ። የሚያድንበት መንገድም በንስሐ ሲሆን የመቆም ብቃቱም የእርሱ ምሕረት ነው ። ሰዎች በሰዎች ፊት በድርቅና በመቆም ሐፍረትን ሊያሸንፉ ይችላሉ ።”የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ” እንዲሉ ። ሰው ግን በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው በእግዚአብሔር ምሕረት ተሸፍኖ ብቻ ነው ። የተራቆተ ሰው በሰው ፊት ለመቆም ይቸገራል ። በነፍሱ ሐፍረት የሚሰማው ደግሞ በኅሊናውና በእግዚአብሔር ፊት መቆም ያቅተዋል ። አንድ ንጉሥ በምሕረት የለቀቀው ወንጀለኛ ያልበደለ ያህል በነጻነት እንደሚወጣ እግዚአብሔር ይቅር ያለውም በኅሊና ሰላም ይንቀሳቀሳል ። ሰው ራሱን ፣ ሰው ጎረቤቱንና እግዚአብሔርን ያፍራል ። ከዚህ የሚያድነው ግን እግዚአብሔር ነው ። እግዚአብሔር ከሐፍረት ያድናል ።

አዳምና ሔዋን በበደል በወደቁ ጊዜ ፍርሃት መጣባቸው ። ከዚህ በፊት የማያውቁት ስሜት ቢሆንም አሁን ተጫናቸው ። ፈርተው የማያውቁ ፈሩ ፣ በድለው የማያውቁ በድለዋልና በዚህ ቀን ብዙ ክፉ ነገሮችን አወቁ ። እግዚአብሔር ያዘዛቸው ከክፉ እውቀት ሊጠብቃቸው ነው ። ክፉን በትምህርት እንጂ በኑሮ ማወቅ ከባድ ነው ። ፍርሃት ኃጢአት የሚያስከትለውም የኅሊና ስቃይ ነው ። ፍርሃት ሁሉ ግን የሚመጣው በኃጢአት ነው ማለት አይደለም ። ፍርሃት የዓለም አስተዳዳሪ የነበረውን አዳምን በገነት ጫካዎች ውስጥ ደበቀው ። ፈፋ ውስጥ ፣ ገደል ውስጥ ተደብቀው ስለተያዙ ነገሥታትና የጦር አለቆች ብዙ ይወራል ። ያልፈራ ሰው ስለፈሪዎች የሚያወራው እየተዝናና ነው ። አዳም ትልቅ አስተዳዳሪ ቢሆንም በቅጠል ውስጥ ተሸሸገ ። ቅጠል ያመጣውን ፍርሃት ቅጠል አያርቀውም ። ዛሬም ሰዎች ፍርሃት ሲሰማቸው የተለያዩ ቅጠሎች ወይም ሱሶች ውስጥ ይደበቃሉ ። ከጠላት ዛቻ ፣ ከተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋ የተነሣ የሚመጣ ፍርሃት አለ ። ልቡናችን ተገንብቶ መቆም ሲያቅተው የሚመጣው ፍርሃት ካለመጸለይና ቃሉን ካለመሞላት የተነሣ የሚመጣ ነው ። ፍርሃትን የሚወልደው ጠባቂ ወታደር አለመኖር ፣ የከተማ ደጃፍ አለመዘጋት ፣ በሩ አለመቆለፉ አይደለም ። ይህ ሁሉ ባለበት ፍርሃት የሚንጣቸው ወገኖች አሌ የማይባሉ ናቸው ። “እባብ ያየ በልጥ ይደነብራል” እንዲሉ ያለፈው ክፉ ገጠመኝ ፈሪ አድርጎ ያስቀመጣቸው ብዙዎች ናቸው ። ሰይጣን ብዙ ሰዎችን ፈሪ አድርጓቸዋል ። ጠንቋይ የሚያፈቅሩ ከፍርሃት አይድኑም ። እግዚአብሔር ግን ከፍርሃት ያድናል ። ስለዚህ ሐዋርያው መድኃኒታችን ይለዋል ።
እግዚአብሔር ባለማዳን የሚያድናቸው ወገኖች አሉ ። አቤልን ሕይወቱ እንዳይጠፋ አላዳነውም ፣ ስሙ እንዳይጠፋ ግን አድኖታል ። እግዚአብሔር ለዘመናት የጽናት ምሳሌ የሚያደርጋቸው ሰዎች ባለ ማዳን ያዳናቸው ሰዎች ናቸው ። አቤል ወንድሙ ባይገድለውም ይሞት ነበር ። የማይቀረው ሞት ግን የክብር ስም ሁኖለት ይኸው የሰማዕታት ራስ ሁኖ ይኖራል ። እግዚአብሔር ዛሬም እኛን አስችሎ ሌሎችን ያስተምራል ። የእግዚአብሔር የአዳኝነቱ ምሥጢር እጅግ ረቂቅ ነው ። ይህም በይበልጥ የተገለጠው በጌታችን ሰው መሆን ነው ። አዳምና ሔዋንን በእባብ ሥጋ ተሰውሮ ጠላት እንዳሳታቸው ጌታችን ደግሞ የሰውን ሥጋ ለብሶ አድኗቸዋል ። ፍቅር ፣ ጥበብና እውነት በሌሉበት ማዳን ሊኖር አይችልም ።
ለእስራኤል እግዚአብሔር አዳኝነቱን የገለጠው ከፈርዖን ጋር ታግሎ ከግብጽ ሲያድናቸው ነው ። የእነርሱ የቅጣት ዘመን ሲጨርስ የፈርዖን የቅጣት ዘመን ይጀምር ነበር ። አጥፊና ጠፊው እየተገናኘ ቅጣት ይከናወናል ። እስራኤል የኤርትራን ባሕር የተሻገሩት በምሕረት ጥላ ስለሆኑ ነው ፣ ፈርዖን የሰጠመው በራሱ ጥላ ስለነበረ ነው ። እግዚአብሔር የሠራተኞች መብት ተሟጋች መሆኑን የምናውቀው እስራኤል ከግብጻውያን ወርቅና ብር እንዲበዘብዙ ባደረገ ጊዜ ነው ። ያ ወርቅና ብር በምድረ በዳ ላይ ደብተራ ኦሪት ወይም መቅደሱ የተሠራበት ነው ። እስራኤል እንዲያ ሳይረጋጉ አሥራት ማውጣታቸው በተረጋጋ ከተማ አሥራት የሚሰርቁትን ለማሳፈር ነው ።
እግዚአብሔር ከጠላት ያድናል ። እስራኤልን የገዙአቸው የሚጠሉአቸው ናቸው ። የሚጠሉን ሲገዙን ከባድ ነው ። እግዚአብሔር ግን የዘመናትን የባርነት ቀንበር ሰብሮ አዳናቸው ። ተፈጥሮን ሠራዊቱ አድርጎ እየተዋጋ ያዳናቸው እግዚአብሔር ነው ። እግዚአብሔር ሲዋጋ ሁሉም ነገር ይጣላናል ።
እግዚአብሔር የልቅሶ ዘመንን በድል ዝማሬ ለውጦ አገር አልባ የሆኑት እስራኤል ፣ አገር ያላቸውን ሕዝቦች ማስደንበር ጀመሩ ። የደረጀ ሠራዊት ያላቸውና የሺህ ዘመናት የመንግሥት መዋቅር የነበራቸው በእስራኤል ምጽአት መደንገጥ ጀመሩ ። እግዚአብሔር አዳኝነቱ የማይደፈር ግርማ ያላብሳል ።
መዳን በሌላ በማንም የለም ሲባል መዳን በሰዎች ፍልስፍና ፣ ብልሃትና መንገድ አይደለም ማለትም ነው ። /የሐዋ. 4፡12/። መዳን መንግሥትህ ትምጣ ብለን በምንለምነው በክርስቶስ ነው ። መዳን በሌላ በማንም የለም የሚለው ቃል እግዚአብሔርን ላከበሩና ለሚጸልዩልን ቅዱሳን መቃወሚያ ተደርጎ የሚጠቀስ ሳይሆን ክርስቶስን ገድለው ስሙ ሲነሣ ለሚከፉ ሰቃልያነ እግዚእ የተጠቀሰ ነው ። እነዚህ ወገኖች ሌላ አዳኝ የለምና የሰቀሉትን ጌታና አዳኝ ብለው ማመን ነበረባቸው ። መራራ ቢሆንም ለመዳን ይህን ዋጋ መክፈል ነበረባቸው ። ካለንበት ነገር የሚያድነን መድኃኒታችን እግዚአብሔር ነው ። መድኃኒት ለእኛ ሕይወት ሲሆን ለበሽታ ግን ሞቱ ነው ። እግዚአብሔርም ለሚያምኑት የሕይወት ሽታ ፣ ለሚጠፉት የሞት ሽታ ነው ። 2ቆሮ. 2፡14-16 ።
ካለውና ከሚመጣው ክፉ የምታድነን ፣ ከራሳችንም ስህተት የምትጠብቀን መድኃኒታችን አንተ ነህ ።
ክብሩ ይጋርደን !
1ኛ ጢሞቴዎስ /2/
ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ