የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ማን ቀረ ከጸጋ ?

 

 

“ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን ።” ኤፌ. 4፡7። 

 

“ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም” ይባላል ። እግዚአብሔር ሲሰጥ እንቀበለዋለን እንጂ እጅ ጠምዝዘን አንቀበለውም ። እንዲሁ በጸጋ የሚሰጠን ነገር አለ ። በልመና የምንቀበለው ፣ በብርቱ ፍለጋ የምናገኘው ስጦታ አለ ። /1ቆሮ. 14 ፡ 1 ፤ ያዕ. 1 ፡ 5/ በተፈጥሮ የሆነልን ፣ በእምነት የምንቀበለውም ጸጋ አለ ። ሰዎችን በተሰጣቸው ጸጋ እናከብራቸዋለን ፣ የሰጣቸውን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን ። ወታደር ራሱን ለማስከበር ሳይሆን አገሩንና ወገኑን ለመጠበቅ እንዲታጠቅ ጸጋም ለባለጸጎቹ ሳይሆን ለእኛ ጥቅም የተሰጠን ነው ። የፈውስ ጸጋ ያለው ሰው ለታማሚው የበለጠ ጠቃሚ ነው ። እርሱ ግን በክርስቶስ ከፈሰሰለት ሰማያዊ ፍቅር የተነሣ ድውያን ሲፈወሱ ያመሰግናል ፣ ይደሰታል ። ሌሎች በእጁ እየተፈወሱ እርሱ ግን ያልዳነበት ደዌ ይኖራልና በዚህ ትሕትናን ይማራል ። ሰዎች በጸጋው ቢመዝኑትም የግሉን የፍሬውን አናሳነት በማየት በራሱ ያዝናል ። ጸጋ የተሰጣቸውን ሰዎች ለራሳችን ስንል መንከባከብ መልካም ነው ። ድንበር የሚጠብቀው ወታደር ሲነሣ አገር እንዲደፈር ፣ ጠባቂ ከሌለም ዘራፊ ከተማ ሰብሮ እንደሚገባ ጸጋ ያላቸው ሰዎች ሲነሡ የተያዘ ክፋት ይለቀቃል ፣ የታሰረ ደዌ ይፈታል ። ጸጋ ያላቸውን ሰዎች ላጥፋ ብሎ መነሣት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማፍረስ መታገል ነው ። ጸጋ ያላቸውን ሰዎች ብንሰድባቸው ፣ ብናጠፋቸው ጸጋቸውን መውሰድ አንችልም ። የተሰጣቸው ሌባ የማይሰርቀው ነው ። በሕዝብ አስተያየት አልተቸሩምና በሰው ትችት አይራቆቱም ። ታድለው ያገኙት እንጂ ታግለው የማረኩት አይደለም ። በሰው ላይ እንዲህ ያለ ጸጋን የሚያፈስስ እግዚአብሔርን ብናመሰግን ለእኛም ጸጋ ይበዛልናል ። ጸጋ የሚበዛው በትሕትና ነውና ። 

 

በሌለን ጸጋ መታገል ያለንን ጸጋ ማስወሰድ ነው ። ጸጋ እሳት ነውና እሳቱን መቆስቆስ ትተን ፍም በሌለበት እፍ ብንል ይህ ላይነድ ያኛው ይከስማል ። እግዚአብሔር ያማረንን ሳይሆን የሚያምርብንን ጸጋ ይሰጠናል ። አስቀድሞ ሲፈጥረንም የአካልና የሰውነት መዋቅራችን ለሚሰጠን ጸጋ እንዲስማማ ሆኖ የተሠራ ነው ። ከሁሉ በላይም በገዛ ገንዘቡ የሚያዝዘው እግዚአብሔር ነውና ይህኛው ይሁንልኝ ማለት አንችልም ። ሳንጠይቅ ሰው ሆነናል ። ሳንጠይቅ መንግሥተ ሰማያት ተዘጋጅቶልናል ። ለምነን ከተቀበልነው ሳንለምን የተቀበልነው እጅግ ውድ ነው ። ጸጋንም በሚመለከት እርሱ የመረጠውን ሲሰጠን መደሰት ይገባል ። ብዙ ሰዎች ከጸጋቸው መፈናቀል ይገጥማቸዋል ። ይህም በሦስት ነገሮች ነው፡- የመጀመሪያው ጸጋቸውን በማባከናቸው ጸጋቸው ሊወሰድ ይችላል ። ሁለተኛው ፣ ከመዳን ጸጋ ውጭ ዘላለማዊ የሆነ ስጦታ የለም ። ዘላለማዊ የሆነ ድውይ የመፈወስ ጸጋ የለም ። ለምሳሌ በሰማይ ታማሚዎች የሉም ። ሦስተኛው ከጸጋቸው ራሳቸው ይሸሻሉ ። ይኸውም በጸጋቸው ደስታን ሲፈልጉ ያጣሉ ፤ በዚህ ምክንያት አኵርፈው ይቀመጣሉ ። ደስታ ስሜት ነው ፣ ጸጋ ግን እውነት ነው ። ደግሞም ሁልጊዜ በጌታ እንጂ በጸጋችሁ ደስ ይበላችሁ ተብሎ አልተጻፈልንም ። 

 

እኛ የምንጠቀመው ከራሳችን ጸጋ ይልቅ በሰዎች ጸጋ ነውና የሌሎች ጸጋ ለእኔ ነው ብለን ማሰብ አለብን ። ጸጋን የፈለግንበት ጸጋ ስለሌለን አይደለም ። የመጀመሪያው ጸጋ እንዳለን አለማወቃችን ነው ። ሁለተኛው በሰው እጅ ላይ ያየነው ጸጋ ስላጓጓን ነው ። አንዳንዱ ጸጋ ስመ ጥር ሊያደርግ ይችላል ። አሁን የምንከጅለውን ጸጋ የተመኘነው በዓለም ሁሉ ለመዞር ነው ? ባለጠጋ ለመሆን ነው ? አስደማሚ ሰው ለመሆን ነው ? ታይታን ከፈለግን ሰባኪ መሆንን መመኘት አያስፈልግም ። የሚያስፈልገው የፊልም ተዋናይ መሆን ነው ። ዓለምን ለመዞር ከፈለግንም የትንቢት ጸጋ ሳይሆን ጥሩ ሯጭ መሆን ለዚያም ልምምድ ማድረግ መልካም ነው ። ባለጠጋ ለመሆንም ተግቶ መሥራት እንጂ ድዉይ የመፈወስ ጸጋ አስፈላጊያችን አይደለም ። ጸጋን ለግል ዝና ግንባታ መጠቀም እግዚአብሔርን የመካድ ኃጢአት ነው ። ጸጋን መቀበል የእግዚአብሔር እንደራሴ መሆን ነው ፣ አምባሳደር ራሱን የሚያሳይ ሳይሆን አገሩንና መንግሥቱን ወክሎ የሚኖር ነው ። ጸጋም የተቸረው ሰው የላከውን እግዚብሔርን ማሳየት አለበት ። ይህ ፍላጎት ሳይሆን ግዴታ ነው ። እግዚአብሔር ጸጋ የሰጠን ድካማችንን ለመሸፈን ነው ። በጸጋችን ግን የሌሎችን ድካም የምናጋልጥ ከሆነ እግዚአብሔር የለም ብሎ እንደ መካድ ነው ። 

 

እኛ ተኝተን የተቀበልነው ፣ እንዳለን ሳናውቅ ይዘነው የምንዞረው ፣ በሰው ላይ እየከጀልነው ገንዘባችን የሆነ ጸጋ አለ ። ያመኑ የተጠመቁ ሁሉ ጸጋ አላቸው ። ሁሉ ዓይነት ጸጋ የለንም ፣ ከጸጋም ባዶ አይደለንም ። ጸጋን በሚመለከት ሙሉ በሙሉ ድሀ እና ሙሉ በሙሉ ባለጠጋ የለም ። 

 

ጸጋን እንደ ባለጠግነቱ መጠን የሰጠ ፣ ለእያንዳንዳችንም ያለ አድልኦ የናኘ እግዚአብሔር ቡሩክ ነው ! 

 

 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ነሐሴ 18 ቀን 2013 ዓ.ም 

 

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ