October 6, 2021 by ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
ማዳን መዳን ነው
“የወንድሙ ሞት ወንድሙን ካልከፋው ፣
ቅበሩት ከደጁ በድኑ እንዲከረፋው ፤”
የሰው ልጅ ከወደቀው አዳም የወረሰው ጠባይ እኔነት ነው ። እኔ ብቻ ልኑር ፣ እኔ ብቻ ይድላኝ ፣ ለእኔ ያልሆነ ዓለም ይደምሰስ ፣ እኔ ከሌለሁ ሁሉም ነገር አይኑር የሚል ራስ ተኮር ሕይወት የአሮጌው ሰው ማንነት ነው ። የሰው ልጅ ራሱን በእኔነት አጥር አስሮ የሚሰቃይ ፍጡር ነው ። የእርሱ ቤተሰብ ፣ የእርሱ ወገን ካልወደቀ ዓለም ሰላም ነው ብሎ የሚያስብ ነው ። በሌሎች ጫማ ውስጥ እግሩን አስገብቶ ማዘንና መጸለይ አይሆንለትም ። ስለተሰቀለው ክርስቶስ መናገር ቀላል አይደለም ። ራሱን ስለሌሎች ሕይወት አሳልፎ የሰጠ ነው ። ክርስትና ሌሎች እንዲኖሩ እኔ ልሙት ከሚል ወግ ወጥቶ እኔ እንድኖር ሌሎች ይሙቱ ወደሚል አስተሳሰብ ከወረደ ከባድ ነው ። ሲጠሩት ቀላል ፣ ሲቆጠሩትም ሁለት ፊደል የሆነው “እኔ” ለብዙ ውጥንቅጦች መነሻ ነው ።
በሌላው ቍስል ያማል ወይ ? ብሎ እንጨት የሚሰድድ ፣ እኔ ቆሜአለሁ አልወድቅም ብሎ የሚያስብ ፣ ከትላንት ዕድለ ቢሶች መማር የማይችል እኔነት ነው ። በሰው ቦታ ሁሉም ሰው መሆኑን እግዚአብሔር በሰጠው ዕድል ሰዎችን ታዝቦአል ። እንዴት እንዲህ ይደረጋል ? ሲል የነበረ ሰው ያንን በእጥፍ ያደርገዋል ። ጊዜውን ሲቀበል በቅን ከመፍረድ በግፍ ይፈርዳል ። /መዝ. 74፡2 / ይህችን ዓለም የሚታደጋት የክርስቶስ ልብ ያለው ነው ። እኔነት ግን በክርስቶስ ልብ ላይ ጦር የሚወረውር ነው ። ክርስቲያን በጨከነበት ዓለም ፣ ዓለማውያን የበለጠ ሊጨክኑ ይችላሉ ። እኔነት እኔን ካልነካኝ ምን አገባኝ ? ባይ ነው ። እኔነት በራስ ዙሪያ መታሰር ነውና ነግ ለእኔ ብሎ አያስብም ። ሕይወት የመዝራትና የማጨድ ሕግ ናት ። ጭካኔን ከዘራን ጭካኔን እናጭዳለን ።
“አሽሟጣጭ ዝናብ ወንዝ ዳር ያካፋል” ይባላል ። ብዙ ደረቅ ምድር ፣ ብዙ በረሃ ፣ ብዙ ዋዕይ ፣ ብዙ ቃጠሎ ባለበት ትቶ ዘባች ዝናብ ወንዝ ዳር ያካፋል ። በሚመሰገንበት ሳይሆን በማያስፈልግበት ቦታ ይዘንባል ። ድሆችን ትቶ ለባለጠጋ የሚደግስ ፣ ደካሞችን ረግጦ የጉልበተኞችን ክንድ የሚደግፍ ፣ ተስፋ ያጡትን ትቶ ለሚዘሉት ምንጣፍ የሚያነጥፍ ፣ የሚያለቅሱትን ቸል ብሎ የሳቅ ኮክቴል ለሚያዘጋጁት መድረክ የሚያሳምር እኔነት የተባለው የሰው ጠባይ ነው ። እኔነት የሌለውን ሰው አይወድም ፣ ላለው ግን ያረግዳል ። የሚያለቅስን አይፈልግም ፣ ለሚቦርቅ መስክ ይደለድላል ። እኔነት የኋላውን የማያስብ ተላላ ነው ። ቀን ከፍቶበት የተሰቀቀበትን ዘመን ረስቶ ቀን ለከፋበት ይጨክናል ። እግዚአብሔር ክፉ ቀንን የሚያሳየን ቀን ለከፋባቸው ሩኅሩኅ እንድንሆን ነው ። ይገባዋል ብለን የፍርድ ማረጋገጫ እንድንሰጥ አልተጠራንም ። “እኔን አድነኝ” ብለን በምናየው በምንሰማው እንድናለቅስ ተጠርተናል ። የሚያለቅሰውን ትተን የሚመታውን ማባበል ፣ ምስኪኑን ረስተን ለጠገበው መዘመር የእኔነት ጦስ ነው ። ራሳችንን የምናጣው ራሳችንን ስናመልከው ነው ። እንኳን የሰው ሞት የውሻ ሞትም ያሳዝናል ። እኔነት ግን ከእኔ ቤተሰብ አልሞተም ብሎ የሞት መረጃ ያስሳል ።
“የእብድ ገላጋይ ድንጋይ ያቀብላል” ይባላል ። ጨዋ ገላጋይ ሰይፍን ማረሻ ፣ ጦርን ማጭድ ያደርጋል ። የእብድ ገላጋይ ግን ማረሻን ሰይፍ ፣ ማጭድን ጦር ያደርጋል ። የእብድ ገላጋይ የበዛበት ይህ ዘመን የሚያበርድ ሳይሆን የሚያጋግል ፣ የሚጸልይ ሳይሆን ጭር ሲል አልወድም የሚል ብዙ ፀላዔ ሰናያትን አፍርቷል ። ቀድመው ባያስተምሩ ዘግይተው እንኳ እንዳያስታርቁ ካህን ደመኛ ፣ መምህራን ጠብ ዘሪ ሁነዋል ። በእብድ ገላጋይ የቤተ ክርስቲያንና የአገር አንድነት ፈተና ውስጥ ገብቷል ። አዎ ያልፋል ። የሚያሳልፈው ክቡር ነገር እንዳለም መረዳት ያስፈልጋል ። የተወረወረው የሚያልፈው ዝቅ ብለን ስናሳልፈው ነው ። እገሌ ሞተ ሳይሆን ይህን ያህል ሰው ሞተ የሚባለው ሰው ቍጥር የሆነበት የእኛ ዘመን ነው ።
ሌላ ትርፍ አገር ያለን ይመስል አንድ አገራችንን ጎድተናታል ። ምዕራባውያን በዐረብ አገራት ላይ ባደረጉት እየቆጨን እኛ የገዛ አገራችን ላይ ጨክነናል ። ስለሚሞተው ስለሚፈናቀለው የሚሰማን እንደ ክርስቲያን ነው ወይ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል ። “ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል” ይባላል ። እንደ ፀጉራም ውሻ መክሳታችን ፣ መጎዳታችን አልታወቀ ይሆናል ። ለማንም በሞቱ ሳይሆን በሕመሙ ብንደርስለት ባለ ትርፍ ነን ። የዕለት ነዋሪ የሆነው ከተሜው ፣ መብላትና መዝፈንን ትቶ ለሚሰደዱትና ለሚሞቱት ወገኖቹ ማዘን ያስፈልገዋል ።
እዚያ የሚሞተው ፣ የሚፈናቀለው ወንድሙ መሆኑ ሊሰማው ይገባል ። ስለሚሞት ሰው ለማመን ሬሳ መገነዝ ፣ ስለሚፈናቀል ሰው ለማዘን ስደተኛ ማነጋገር አያስፈልገንም ። ደግሞም “እንጨት ካልነሡት እሳት አይጠፋምና” ጠብና ጦርን የምንዘራ መሆን አይገባንም ። ስለ እርቅና ስለ ፍቅር አሁንም ደግመን ዋጋ መክፈል ይገባናል ። የሰው ልጅ ኑሮ የተሳሰረ ነውና በሩቅ ያለው ጉዳት እኛንም ዋጋ ያስከፍለናል ። እንኳን የቅርቡ ወንድማችን የሶርያ መፍረስ እኛንም ጎድቶናል ። በምድራችን ላይ ያሉ ስደተኞች አገራቸው ሰላም ሆኖ ቢመለሱ በብዙ እናተርፋለን ። ዛሬ እየዘፈንን የምንናገረው ጠብ ነገ እያለቀስን የምንኖረው ይሆናልና ጥንቃቄ ማድረግ አለብን ።
ለሞተ ሰው ለማዘን የሟቹን ማንነት ማወቅ አያሻንም ። ሰው ሞቷልና የተፈጥሮ ጓዳችንን መውደቅ እያሰብን ማዘን ይገባናል ። የሚፈናቀልን ለመቀበል ማንነቱን መጠየቅ አያሻንም ። እንግዳ ተቀባይ የነበረው አሁን ስደተኛ በመሆኑ ልንቀበለው ይገባል ። የዚህ ዓለም መልክ ተለዋዋጭ ነውና እንዳለን የምንኖር ከመሰለን ሞኞች ነን ። ክፋት ማስቆም ባንችል መቀነስ ይቻላል ። ለዚህም የሁላችን የቅንነት ምላሽ ያስፈልጋል ።
ጌታ ሆይ ያንተን የርኅራኄ ልብ አድለን ።
የብርሃን ጠብታ 12
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 26 ቀን 2014 ዓ.ም.