የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምስጋና

ምስጋና ወደ ከፍታ መብረር ነው ። በልባችን ያለውን እግዚአብሔር በሰማያት የምትኖር እንለዋለን ። ምስጋና ወደ ከፍታ የምንበርበት መንኮራኩር ፣ መንፈሳዊ ሠረገላ ነው ። የቅዱሳን ብቃት የምንለውም በተመስጦ መጥፋት ነው ። ይህን ዓለም መተው ፣ ደመናትን ሰንጥቆ ሀገረ ሕይወት መንግሥተ ሰማያት መገኘት ነው ። የተመስጦ ሕይወት የዓለምን ማቁሰል ፣ የሰይጣንን ጭካኔ የምንረሳበት ነው ። ሰማይ እየደረሰ መመለስ የቻለ መራራው ጨርሶ አይመረውም ። በምድር ጀምሮ በምድር መፈጸም ቀኑን ደመናማ ያደርገዋል ። የምስጋና ክንፎች ወደ መንበረ ሥላሴ ያደርሳሉ ። እዚያ ስንወጣ ትልቅ የሆነብን ነገር ሁሉ ትንሽ መረገጫ ይሆናል ። ሁሉም ነገር ከምድር ሲያዩት ትልቅ ነው ። ከሰማይ ሲያዩት ግን ትንሽ ነው ። ምስጋና ወደ እግዚአብሔር መኖሪያ ወደማይዘጋው አደባባይ ፣ ግርዶሽ ወደ ሌለበት ቤት የሚወስድ ነው ። ከጉዳያችን በላይ እግዚአብሔር ጉዳይ ሁኖ የምናመልከው የምስጋና ጣዕም ሲገባን ነው ። ቤተ ክርስቲያን ለምስጋና ብቻ የምታሰለጥናቸው አዋቂዎች አሏት ። በዓለም ላይም የምስጋና ትምህርት ቤት ያላት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ናት ። የዋሸራው ቅኔ ፣ የቤተ ልሔሙ ድጓ ማስመስከሪያ ለስብሐተ ሥላሴ የተዘጋጀ ነው ።  ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት የመዝሙር ዩኒቨርስቲ  ከፍታ የምታስመርቅ ይህች የበረሃ ጥላ የሆነች ቤተ ክርስቲያናችን ናት ። ቀለሙ ዜማው በተመስጦ ይዞ ይጠፋል ። በአንድ ቀለም ማታ የጀመረው ማኅሌት ይነጋል ። በብዙ ግጥም ሳይሆን አንዱን ቀለም ሲያስተነትኑ ፣ ተመስጦው አልለቅ እያላቸው በጨለማ ሰዓት ጀምረው በንጋት ይላቀቃሉ ። ምስጋናው እንደ ጎርፍ ነውና ማኅሌቱ ሲያበቃ ኪዳኑ ፣ ኪዳኑ ሲያበቃ ቅዳሴው ይቀጥላል ። ሰማይንና ቀራንዮን በየዕለቱ የምትጋብዝ በአጭር ቃል የምትቀድስ ቤተ ክርስቲያን ናት ። ማመስገን የራስን ፣ የዓለምን ፣ የክፋትን ግዛት ጥሶ ቀኙ ወደምታዝበት ከተማ መድረስ ነው ።

ተመስጦ ያስፈልጋል ። ትዕግሥትን የምንለማመደው በተመስጦ ነው ። ነገረ እግዚአብሔርን የምናጣጥመው በተመስጦ ነው ። ቃሉን ከሕይወታችን ጋር በቅድስና ስናዋሕደው ፣ በተመስጦ ደግሞ ከመንፈሳችን ጋር እናዋሕደዋለን ። ቃሉ ሲመጣ ቤታችንን ያንኳኳል ፣ ተመስጦ ደግሞ የእግዜርን ደጃፍ ማንኳኳት ነው ። የሚመሰጥ ትውልድ እያጣን ነው ። ስለዚህ መራርነት ፣ ሌላውን ማጥቃት ፣ ጭካኔ ፣ ያልተረጋገጠ እውቀት ፣ የእግዚአብሔር ጠበቃነት እየበዛ ነው ። ምስጋና በማይታዩ ክንፎች ወደ ላይ መብረር ነው ።

እስትፋሳችሁ በአፍንጫችሁ ያደረችላችሁ አመሰግኑ ! ተመስገን ተመስገን !

(የምስጋና ሕይወት ከሚል ያልታተመ ጽሑፍ የተወሰደ)

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ