በቅበላ ዋዜማ ምግቡ እንዳይበላሽ እየተባለ ይበላል ። ሰውዬው “ብላ ነገ ጾም ስለሆነ ምግቡ ይበላሻል” እያሉ ብዙ ሲያበሉት፡- “እኔ ቀድሜ ልበላሽ ነው” አለ ይባላል ። ሕፃን ልጅ በቃኝን ስለማያውቅ ያለ ልክ በልቶ ይታመማል ። “አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል” ይባላል ። ምግብን በልክ ያልበላ ሌሊቱን በሙሉ ሲጨነቅ ያድራል ። የሰው ልጅ ዕድገቱም ክብረቱም ይበቃኛል ሲል ነው ። ከብቶች እንኳ አተላ ጠጥተው ሲጠግቡ ጥለው ይሄዳሉ ፣ አልኮል መጠጥ እየጠጣ እያጋባ ተመልሶ የሚጠጣው ሰው ብቻ ነው ። አንበሳ የሚበቃውን ከበላ በኋላ ለሦስት ቀናት ያህል ዕረፍት ያደርጋል ። የተሰጡን አካላት ዕረፍት ይፈልጋሉ ። ጾም ሰማያዊ በረከት ከመስጠቱም በላይ የአካል ሠራተኞችም እንዲያርፉ ያደርጋቸዋልን ። በማረፍ ውስጥ ራሳቸውን ያፀዳሉ ። ለመኪናው ሰርቪስ የሚያስበው ሾፌር እኔም ማረፍና መጠገን አለብኝ ብሎ አያስብም ። ሰዎችን ለማስደሰት ሲሮጥ የሚኖረው አሁን ደግሞ ራሴን ላዳምጥ ብሎ የራሱ የደቂቃ ዕድሜ አይሰጥም ። አንዳንድ ሰዎች በገዛ ቤታቸው ምግብ እየበሉ ሰው ሲመጣባቸው ይደነግጣሉ ። ብቻውን መብላትም የመስረቅ ያህል የሚያሳፍረው ሰው አለ ። ብዙ ብኩኖች ዘመናትን በሩጫ ያሳልፋሉ ፣ ትርፍና ኪሣራቸውን መተመን ግን አልቻሉም ።
በሕይወት ውስጥ ይበቃኛል ማለት ትልቅ እርካታ ነው ። ሰው ሁሉን መያዝ አይችልምና ሁሉን ልጨብጥ ማለትን ፤ ሁሉን አዋቂ አይደለምና ሁሉን ልናገር ማለትን ማቆም አለበት ። ሀብቱም ፣ ሥልጣኑም ፣ ዓለሙም ገዳሙም አይቅርብኝ ማለት ከግምት ላይ ይጥላል ። ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ አይወጣም ። ሁለት አባራሪም አንድ አይዝም ። ይበቃኛል ስንል እርካታን እናገኛለን ። የረካ ያመሰግናል ። ምስጋና ቢስነት ልክን ባለማወቅ የሚመጣ ነው ። ለመሰንበቻው ዓለም ፣ ጠዋት ለማታ ለማያስተማምነው ዕድሜ ያለን በቂ ነው ። ስለ ዕለት ማሰባችን ጤነኛነት ነው ፣ ስለ ዓመት መጨነቃችን ግን የተሸከምነውን ኃላፊ ማንነት አለመገንዘብ ነው ።
ሁልጊዜ የበላያቸውን የሚያዩ ሰዎች ምስጋና ቢስ ይሆናሉ ። ለሁሉም በልኩ እንደሚሰጠው እየረሱ እንደ እገሌ ካልሆንሁ የሚል ውድድር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ደስታ ይርቃቸዋል ። እነርሱ አንድ ናቸው ፣ መሆን የሚፈልጉት ግን እንደ ብዙዎቹ ነው ። ያልተሰጣቸውን ሲፈልጉ የተሰጣቸውንም ያጡታል ። ሰውዬው፡- “እግር የሌለው እስካይ ድረስ ጫማ የለኝም ብዬ አዝን ነበር” ብሏል ። የበታቾችን ስናይ እናመሰግናለን ። “እኔ ምን ሆንኩ (” ብለን ራሳችንን እንገሥጻለን ።
የአሁኑንና የበፊቱን ኑሮአቸውን የሚያወዳድሩ ሰዎች ምስጋና ቢስ ይሆናሉ ። የሚገርመው የድሮ ኑሮአቸው ቀኑ በመርዘሙ ምክንያት ረስተውት እንጂ መልካም አልነበረም ። ዛሬን ለማክፋፋት ፣ በዛሬው ሁነት ላለማመስገን ትላንትናን ቆንጆ ማድረግ ይፈልጋሉ ። በዚህ ምክንያት ከእውነትና ከቅን ፍርድ እየተለያዩ ይመጣሉ ። እስራኤል ስለ መናው ላለማመስገን የግብጽን ሽንኩርት ያደንቁ ነበር ። ግብጻውያን ሥጋ ሲበሉ እነርሱ ሥጋ የበሉ እንዲመስላቸው ሽንኩርት ጠብሰው ይበሉ ነበር ። ይህንን ኑሮ አሁን ካለው ከመናው ጋር አነጻጸሩት ። በርግጥ በዓለም ላይ ነገሮች እየባሱ ፣ አገዛዞች እየጠነከሩ በመምጣታቸው ያለፈውን ማመስገን እየበዛ ነው ።
ያምናን ቀን አማሁት ላፌ ልጓም የለው ፣
መጣ የዘንድሮው እጅ እግር የሌለው ።
ያምናን ሰው አማሁት ላፌ ለከት የለው ፣
የዘንድሮው መጣ እግር እጅ የሌለው ።
ምስጋና ቢስነት ከከንቱ ውድድር ፣ ከእውቀት አልባ ንጽጽር የሚመጣ ነው ። ምስጋና ቢስ ሁሉም ነገር የማይጥመው ፣ ሁልጊዜ ለእኔ ብቻ ይደረግ ባይ ፣ የሚፈልገውን በትክክል የማያውቅ ፣ በአሉታዊ ነገር የተሞላ ፣ ቅንነቱን የተሰረቀ ፣ የተደረገለትን ሳይቀበል ሌላ የሚፈልግ ፣ ለእኔ ትንሹ ተሰጠኝ ብሎ የሚቀና ሰው ማንነት ነው ። ምስጋና ቢስ ነጥቆ በረር ነው ። እግዚአብሔርም ሰዎችም አድርገውለት ለምስጋና የማይመለስ ነው ። አምላካቸውን ተመስገን ፣ ሰዎችን እግዚአብሔር ይስጥልኝ የማይሉ ወገኖች ጉዶች ናቸው ። በብዙ መንገድ የምስጋና ዕዳ አለብን ። ለዛሬው ማንነታችን አስተዋጽኦ የነበራቸውን ረስተናል ። በምርኵዝ የነበረ ሲበረታ ምርኵዙን ጥሎ ይረሳዋል ። ምርኵዝ የሆኑን ሰዎች ግን የሚረሱ አይደሉም ። በዓለም ላይ የመጨረሻው ውሸታም ከሰዎች ምንም አልተቀበልኩም ባይ ነው ።
ምስጋና ቢስነት ደስታን ያሳጣል ። ሰዎች እንዲጨክኑብን ያደርጋል ። ቆሻሻ ነገር ዝንብ እንደሚሰበስብ ምስጋና ቢስነት አጋንንትን ይሰበስባል ። ለሁሉ የሚሰጥ አንድ እግዚአብሔር ፣ በፈቃዱ የሚያኖረን አምላክ አለ ። የተሰጠንን መሆን ጸጋ ነው ። በተሰጠን መደሰት ብልሃት ነው ። ምስጋና ከፈጠረን ጋር የሚያገናኘን ድልድይ ነው ። ምስጋና ቢስነት ድልድዩን ይሰብረዋል ። ስለዚህ ዓለም ገዥዎች ፣ ስለ ፖለቲከኞች ከመጠን በላይ ማሰብ ብስጩና አማራሪ ያደርጋል ። ሁሉን ሊለውጥ ሥልጣን ላለው ቀኑንና አገሩን መስጠት ያሳርፋል ። እስትንፋሳችን በአፍንጫችን ካደረች ተመስገን ማለት አለብን ። ስለ መኖራችን እግዚአብሔር ይመስገን ።
ምስጋና ቢስነት እስራት ነው ። እግዚአብሔር ይፈታል ። እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፡- “እግዚአብሔር የታሰሩትን ይፈታል ።” (መዝ. 145 ፡ 7) ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም.