መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ምንኵስና

የትምህርቱ ርዕስ | ምንኵስና

 

እግዚአብሔር አምላክ ጋብቻን ስጦታ አድርጎ እንደሚሰጥ ድንግልናንም ስጦታ አድርጎ ይሰጣል ። ጋብቻ የሰው ነጻ ፈቃድ እንደሆነ ድንግልናም ነጻ ምርጫ ነው ። ጋብቻ ከብዙ ወንዶችና ከብዙ ሴቶች አንዱን ወንድና ሴት የሚመርጡበት ሲሆን ድንግልናም ብዙ ጌቶች ነን የሚሉ ባሉበት ዓለም ለአንዱ ጌታ ለክርስቶስ ራስን ማጨት ነው ። ጋብቻ ቤተሰብ የሚመኝልን ሥርዓት እንደሆነ ድንግልናም መምህራንና አባቶች ሊመኙልን ይችላሉ ። ጋብቻ ቃል ኪዳን እንደሚደረግለት ድንግልናም ቃል ኪዳን ያስፈልገዋል ። ጋብቻ እስከ ሞት ድረስ እታመናለሁ የሚል ቃል ኪዳን እንዳለው ድንግልናም እስከ ሞት ድረስ ለመታመን ቃል ኪዳን የሚደረግበት ነው ። ጋብቻ በምድር ሲቀር ለክርስቶስ እጮኛ የሆኑበት ሕይወት ግን ለዘላለም ይቀጥላል ። ባለት ትዳሮች የቃል ኪዳን ምልክት የሆነውን ቀለበት ያደርጋሉ ፣ ደናግላንም የምንኵስና ምልክት ያደርጋሉ ። አንዳንድ ባለ ትዳሮች ቀለበት አያደርጉም ፣ በልባቸው ግን ቀለበቱ አለ ፣ አንዳንድ ደናግላንም ውጫዊ ምልክት የላቸውም ፣ ውስጣቸው ግን መነኵሴ ነው ። ጋብቻ በሰዎች ፊት የሚደረግ ቃል ኪዳን የሆነው ሌሎችን ተስፋ ለማስቆረጥና እኔ የእገሌ ነኝ ለማለት ነው ፤ ድንግልናም የምንኵስና ቃል ኪዳን የሚደረግለት በዙሪያ ያሉትን ሰዎች ተስፋ ለማስቆረጥና ዝም ለማሰኘትም ነው ። 

ጋብቻ የማኅበራዊ ኑሮ መሠረት ነው ። ደናግል መነኮሳትም የገዳማዊ ኑሮ መሠረት ናቸው ። ምንኵስና የቃል ኪዳኑና የአኗኗሩ ስም ሲሆን ምርጫው ድንግልናዊ ሕይወት ተብሎ ይጠራል ። የድንግልና ኑሮ አዳምና ሔዋን በገነት የኖሩት ነው ። ሕገ መላእክትም ይባላል ። መላእክት አያገቡም አይወልዱምና ። ነገር ግን ለእግዚአብሔር አምልኮ ብቻ ይኖራሉ ። መነኮሳትም ለእግዚአብሔር ብቻ የሚኖሩ ናቸው ። የጌታችን ዘላለማዊ ክህነት ምሳሌ የነበረው መልከ ጼዴቅ ፣ ታላቁ ነቢይ ኤልያስ ፣ ታላቁ ነቢይ ኤርምያስ ደናግላን ነበሩ ። ነቢዩ ኤርምያስ በብላቴናነቱ የተጠራ ሚስትም እንዳያገባ የተከለከለ ነው ። ኤር. 16፡2 ። በአዲስ ኪዳንም ጌታችን አብነት የሆነበት ኑሮ የድንግልና ሕይወት ነው ። እመቤታችንም ለማንም የማይሰጥ ጸጋን የተቀበለች ስትሆን የድንግልና ኑሮ ኖራለች ። የደናግል መመኪያ የምትባለውም ደናግል አልወለድንም ብለው እንዳያዝኑ ድንግል ፈጣሪዋን ስለወለደች ነው ። በዚህም ደናግል ታላቅ ትምክሕት አግኝተዋል ። ታላቅ ብሎ ጌታችን የመሰከረለት ዮሐንስ መጥምቅ ፣ ታላቁ ሐዋርያ ዮሐንስ ወልደ ዘብድዮስ ፣ ታላቁ የዓለም መምህር ጳውሎስ ደናግላን ነበሩ ። ሐዋርያትም ከጴጥሮስ በቀር ደናግል እንደሆኑ እናምናለን ። 

እግዚአብሔር አምላክ ሄኖክን ካገቡት መሐል ፣ ኤልያስን ከደናግላን መሐል ወደ ብሔረ ሕያዋን እንዲወሰዱ ማድረጉ በሁለቱም ሕይወት ቢታመኑ ደስ እንደሚሰኝ ማሳያ ነው ። ጌታችን በተጠመቀ ዕለት ወደ ገዳም ሄደ ። የመነኮሳትን መኖሪያ ሊባርክና የበረሃ አባቶችም እንደሚያስፈልጉ ለመግለጥ ነው ። ከገዳመ ቆሮንቶስ ከወጣ በኋላ በቃና ዘገሊላ ሰርግ ላይ መገኘቱ ጋብቻን ሊባርክና አባወራዎችም ለማኅበራዊ ኑሮ አስፈላጊ እንደሆኑ ለማሳየት ነው ። 

መነኵሴ ማለት ለዓለም ፍላጎት የሞተ ማለት ነው ። ነገር ግን የሚማርና የሚያስተምር ፣ የሚሠራና ድሆችን የሚረዳ ነው ። መነኩሴ ትምህርት ኑሮው ነው ፣ ነገር ግን ሊቅ ተብሎ እንጀራ ለመብላት አይደለም ። ከሁሉም በላይ በሥራ የተወጠረ ነው ። ደመወዝ ግን አይወስድም ፣ ለድሆች ይሰጠዋል እንጂ ። ምንኵስና የሥራ ፈቶች ምርጫ አይደለም ። “ሥራ የፈታ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይስፋ” የሚባለው የሥራን ክቡርነት ማሳያ ፣ ሥራ ለእንጀራ ብቻ ሳይሆን የሰይጣንን ፈተና ለማለፊያም ወሳኝ እንደሆነ የሚገልጥ ነው ። መጽሐፈ መነኮሳትም “በሰነፍ አእምሮ ኃጢአት ይነግሣል” ይላል ። መነኮሳት ትዳርንና ትውልድን የሚያጣፍጡ ጨው ናቸው ። በስድስተኛው ክፍለ ዘመን የነበሩት የኢትዮጵያ ንጉሥ ዐፄ ካሌብ የየመን ክርስቲያኖችን ከመከራቸው ለማሳረፍ በዘመቱ ጊዜ እነርሱን ከታደግሁ ፣ ክርስትናን ካስፋፋሁ ስመለስ እመንናለሁ ብለው ተስለዋል ፣ ዘውድ አስቀምጠውም መንነዋል ። የምንኵስና ሕይወት ሰዎች እንዲህ ብለን መመሥረት አለብን ብለው የጀመሩት ሳይሆን ክርስትናን ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረግ ጥረት ውስጥ የመጣ ነው ። ለዚህም አምላካዊ ቃል መነሻ ነው ። ጌታችን፡- “ፍጹም ልትሆን ብትወድ፥ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፥ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ” ያለው አንዱ የዘመቻ ቃል ነው ። ማቴ. 19፡21 ። ዳግመኛም፡- “ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል።” ብሏል ። ማቴ. 19፡26 ። ካህን ትምህርት ፣ መነኩሴ ገዳም ከሌለው አስቸጋሪ ነው ። ቤተ ክርስቲያን ለገዳማቱ መነኮሳትን ፣ ለመነኮሳትም ገዳማትን ማዘጋጀት ያስፈልጋታል ። ሰዎች የጽሞና ጊዜ ሲፈልጉ የሚያርፉበት ገዳማት በከተማም ሊሠሩ ይገባቸዋል ። መነኮሳት የቤተ ክርስቲያን ወታደሮች ናቸው ። ወታደር በረሃውን ፣ ፖሊስ ከተማውን እንደሚጠብቅ መነኮሳት ወጥተው ወርደው ፣ ካህናት በከተማው ጸንተው ሊያስተምሩ ይገባል ። 

በሰለጠነው ዓለም መናንያን እየበዙ ፣ ዓለምን የሚንቁ ወጣቶች ወደ ገዳማት ሲገቡ በእኛ ግን እየቀነሰ መጥቷል ። አንድ ልብ ሆነው ክርስቶስን የሚያገለግሉ መነኮሳት ያስፈልጋሉ ። ሲኖዶሱንም የሚረከቡት የዛሬ መነኮሳት የነገ ጳጳሳት ናቸው ። የትምህርት ዕድሎችም ለመነኮሳት መሰጠት አለበት ። መነኩሴ ቢሸፍት አንድ ቤተ ክርስቲያን ሠርቶ መርቁልኝ ሲል በመጨረሻ ይገኛል ። ቤተ ክርስቲያን በመነኮሳት ላይ የምታፈስሰው አቅም በትውልድ ህንጸት ላይ ይታያል ። ምንኵስና ተስፋ የማድረግና ከዚህ ዓለም የሚመጣው ዓለም ይበልጣል የማለት እይታ ነው ። እግዚብሔርን ለማገልገል ሰፊ ጊዜ የሚሰጥ ፣ በአንድ ልብ ሁኖ የወንጌልን ሥራ ለመሥራት የሚጠቅም ነው ። ለዚህች ዓለም የሚጋደሉ ስግብግቦችን የመነኮሳት ምርጫቸው ብቻውን ይገሥጻቸዋል ። በጋብቻ ፈተና እንዳለ በምንኵስናም ፈተና አለ ። ሕልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም ። 

ዘመናቸውን ለእግዚአብሔር የሚሰጡ ሠራዊተ ክርስቶስን ያብዛልን ! 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን 

ሐምሌ 29 ቀን 2013 ዓ.ም.

እውነት 9

ለልባችሁ የቀረላችሁን አሳብ እስቲ ግለጡ ። እግዚአብሔር ዘመናችሁን ይባርክ !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም