የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር

/በሮሜ ምዕ. 1፥1 ላይ የተመሠረተ ምክር/
ቤተ ጳውሎስ ማክሰኞ መስከረም 8/2005 ዓ.ም
እግዚአብሔር በንጉሣዊ ጥሪው ለማዳን፣ ለማገልገል፣ መንግሥቱን ለመውረስ ጠርቶናል፡፡ ይህ ጥሪ ክብር ያለው ጥሪ እንደሆነ እናስብ፡፡ የተጠራነው ከታላቁ ቤተ መንግሥት በእግዚአብሔር ፊት ለመኖር ነው፡፡ በማዳን ጥሪው ልጆቹ፣ በመንግሥቱ ጥሪ አምባሳደሮቹ፣ በጸጋው የርስቱ ወራሾች ሊያደርገን ጠርቶናል፡፡ ልጆች የፈለገው ጧሪ ፈልጎ፣ አገልጋዮች የፈለገው አጋዥ ሽቶ፣ ወራሽ የፈለገው ሞት አስግቶት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ክብሩን ሊያጎናጽፈን እንደ ጠራን አንዘንጋ፡፡
በዚህ ዓለም ላይ ጠሪ አክባሪ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ያለ ሕግ ማስገደጃ የምንሄደውም በጥሪው ውስጥ የጠራንን ፍቅርና አክብሮት ስለምናይ ነው፡፡ በእውነት ለእግዚአብሔር ጥሪ ዋጋ እንስጥ፡፡ ሰዎች ለምርቃት፣ ለሠርግ ቢጠሩን ሄደን እንመለከታለን፡፡ ደስታቸውን እንጋራለን፡፡ በእግዚአብሔር ጥሪ ግን ተመልካች የለም፡፡ ሁሉም ተመራቂ፣ ሁሉም ሙሽሪት ነው፡፡ ጥሪውን እምቢ ማለት የእግዚአብሔር ልጅ አልሆንም ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ካልሆንን የዲያብሎስ ልጆች እንሆናለን፡፡ ጥሪውን እምቢ ማለት አምባሳደርነትን መግፋት ነው፡፡ ቀጥሎ የሰይጣን ባሪያ መሆን ነው፡፡ ጥሪውን እምቢ ማለት ገሀነምን መውረስ ነው፡፡ ሕይወትና ክብር ካለው ጥሪ በመዘናጋት እንዳንቀር እንወቅበት፡፡
የተጠራነው ከየትኛው ዋሻ፣ ከየትኛው ሸለቆ፣ ከየትኛው በረሃ፣ ከየትኛው ግዞት ይሆን? የእግዚአብሔር ጥሪ ሕይወትን የሚለውጥ፣ ለመንፈሳዊ ሥልጣን የሚያበቃ፣ ሁሉም አለኝ ብሎ የሚያኰራ ጥሪ ነው፡፡
ልጃቸውን ባሪያዬ ብለው የሚጠሩ “የእኔ ባሪያ” ሲሉ መግለጫ የሌለውን የፍቅር ትንታግ የሚረጩ ብዙ አባቶች ናቸው፡፡ ልጅ የሆናቸው ያለ ፈቃዱ ነው፣ ባሪያ የሆናቸው ግን በፈቃዱ ነው፡፡ እግዚአብሔርም ልጁ ብቻ ሳይሆን ባሪያዬ የሚለውን ይፈልጋል፡፡ በጸጋው ልጆች ሆነናል፣ ባሪያዎች የምንሆነው ግን በመታዘዝ ነው፡፡ ልጅነት ብቻ ሳይሆን ባሪያ መሆን እንዳለብንም ማሰብ ያስፈልገናል፡፡ ባሪያ የራሱ ጊዜና ጥሪት (ሀብት) የሌለው የጌታው የሆነውን ሁሉ የእኔ ብሎ የሚያምን ነው፡፡ እኛም የእግዚአብሔር ባሪያዎች ስንሆን የእኔ ብለን የምናዝበት ጊዜና ጉልበት አይኖረንም፡፡ የእኛ የሆነው ሁሉ የጌታ፣ የጌታ የሆነው ሁሉ የእኛ ነው፡፡

እግዚአብሔር የምንፈልገውን እንዲፈጽም እንጂ እርሱ የሚፈልገውን እኛ ለመፈጸም የማናስብ ነንና ወዮልን! ፈቃዳችንን ብቻ የሚፈጽም የፈጠርነው አምላክ ነው፣ የፈጠረን አምላክ ግን ፈቃዱን እንድንፈጽም ይጠይቀናል፡፡ ዓመፅ በበዛበት በዚህ ዘመን ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይገባናል፡፡ ያመፀብን ቁጣና መቅሰፍት የሚበርደው ለእግዚአብሔር ስንታዘዝ ነው፡፡ የነገሠብን ዝሙትና ርኩሰት፣ ያዋረደን ሱስ የሚዋረደው ለእግዚአብሔር ስንገዛ ነው፡፡
የእምነታችን መሠረቱ መጽሐፍ ነው፡፡ እገሌ ምን አለ? ሰባኪው ምን አለ? አባ ምን አሉ? ሳይሆን መጽሐፍ ምን አለ? ልንል ይገባናል፡፡ መጽሐፍ ካለ አለ ማለት ነው፡፡ አገልጋዮች በመጽሐፍ ቅዱስ ይታረማሉ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በአገልጋዮች አይታረምም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን በታች ናት፡፡ በዛሬው ዘመን ግን ቤተ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ በላይ ናት የሚል አስተሳሰብ የምዕራብ አብያተ ክርስቲያናትን እየገዛ መጽሐፉ የሚከለክለውን ርኩሰት እያፀደቁት ይገኛሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን ሳይሆን ዘመኑን እንድትመስል እየተጨነቁ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ዘመናዊነት ሳትሆን መንፈሳዊነት ናት፡፡ ዘመናዊነት ወረት ነው፤ መንፈሳዊነት ቋሚ ውበት ነው፡፡
ዛሬም እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በአገልጋዮች ይናገረናል፡፡ እግዚአብሔር ተናገረኝ ብሎ የሚጽናና፣ የሚበረታ፣ ከክፉ መንገዱ የሚመለስ ግን እንዳይታጣ ልናስተውል ይገባል፡፡ ብሉን ብሉን የሚሉ ብዙ የቃለ እግዚአብሔር ገበታዎች ተዘርግተዋል፡፡ ይህ ዕድል ነውና ቶሎ ቶሎ መጠቀም ይገባል፡፡ በበጋ ያልሰበሰበ በክረምት ይንከራተታል፣ ተንከራቶም ምንም አያገኝም፡፡
የእግዚአብሔር ቃል በተስፋ የተሞላ ነው፡፡ ተስፋን የሚዋጉ ነገሮች በበዙበት በዚህ ዘመን ከቃሉ ውስጥ ብዙ የተስፋ ነፀብራቆች ይወጣሉ፡፡ የእግዚአብሔር ድምፅ ሲሰማ ወደ ሞት የምትጓዝ ነፋስ ወደ ማደሪያዋ ትመለሳለች፡፡
እኛ ተስፋ የምንሰጠው በሰዎቹ ላይ ያለውን ተስፋ ሰጪ ነገር በማየት ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ለጨለመበት፣ ፍጹም ለወደቀ፣ ለሞተና ለተቀበረ ተስፋ ይሰጣል፡፡ የደረቀው አጥንት በዚህ ተስፋ ይለመልማል፣ ተስፋ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ነውና በርትቶ ይቆማል፡፡ ብርቱ ሠራዊትም ይሆናል፡፡
አንድ ክፉ ነገር ስትሰሙ አንድ የቃሉን ዘለላ ተመገቡ፡፡ ጭንቀታችሁ በቃሉ ፊት የመቆም ኃይል የለውም፡፡
አንዲት ሴት እየወደደቻቸው ከወላጆችዋ ባልዋን መርጣ እንደምትለይ እንዲሁም ክርስቶስን አዲሱን ሙሽራ ይዘን ከመደባለቅ ኑሮ ወደ ጠራው ኑሮ መለየት ያስፈልገናል፡፡ ለተለዩለት እግዚአብሔር አክባሪ፣ ብቻውንም በቂ ነው፡፡ ትልቁ ምክር ከእግዚአብሔር ጋር ኑሩ የሚል ነውና ከእርሱ ጋር እንኑር፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ