የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው /1

ወዳጄ ሆይ !
እውነት ብርሃት ናት ፣ ዓይናቸውን የጨፈኑ ግን አያዩአትም ። ጠባብ ቤታቸውን ያልከፈቱ ፀሐይ ብትወጣም በጨለማ ናቸው ፣ ልባቸውን የዘጉም እውቀት ቢኖርም በድንቁርና ውስጥ ናቸው ። አንተ በርህን አልከፈትህም እንጂ ፀሐይስ ወጥታለች ፣ ከአመለካከትህ አጥር አለመውጣትህ እንጂ እግዚአብሔርስ አለ ።

ወዳጄ ሆይ !

ግርማዬ እንዲያስደነግጥ ፣ ሞገሴ እንዲያስመርጠኝ ብለህ ግርማ ወሞገስ ድግምት አትፈልግ ። ትልቁ ግርማና የማይደፈረው የእሳት ቅጥር ፣ ትልቁ ሞገስና ተወድዶ የሚያስወድድ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ዘመዶችህ እንደ ሠራዊት ቢከቡህ በልብህ አትኩራ ፤ እነዚህ ሁሉ ከብበው ያለቅሱልህ ይሆናል እንጂ ሞትን አይመልሱልህም ። ሞትን የሚመልስ ዘመድ አለ ፣ እርሱም የማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

ጨረቃ ብታበራም ዙሪያዋ ጨለማ ነው ። አንተም ሥራዬ ደመቀ ብትል ዘመዶችህ ገና በጨለማ ውስጥ ናቸው ። ጨረቃ በራስዋ አታበራም ፣ አንተም በራስህ አቅም ይህን አላደረግህም ። በፀሐይ ፊት ጨረቃ አትመካምና በእግዚአብሔር ፊት አለኝ ለማለት አትድፈር ። ዓለም አቀፋዊ ሰው ሁኛለሁ ብለህ አትታበይ ፣ የተወለድህበት መንደር በሁከት እየተናጠ ነውና ።

ወዳጄ ሆይ !

እግዚአብሔር በፍጥረት ለሰውነት ፣ በመስቀሉ ለድኅነት ጠርቶሃል ። ሰው ሁኖ ለመኖር ፣ በክርስቶስም አዲስ ፍጥረት ለመባል ግን ምርጫው ያንተ ነው ። አገር ሰላም ቢሆን ያንተ ቤት ሰላም ይሆናል ፣ ቤትህ ሰላም ሁኖ አገር ቢታወክ ቤትህ የአገር አካል ናትና ትታወካለች ። ስለ ቤትህ ሳይሆን ስለ አገርህ አስብ ። የአገር ሰላም ለሁሉ ይተርፋል ። ሰላም በሌለበት አገር ባለጠጋ ከመሆን ሰላም ባለበት አገር ድሀ መሆን ይበልጣል ። ሚሊየን ብሮች በባንክ እያላቸው በረሀብ የሞቱ ካሉ አገራቸው የታወከባቸው ወገኖች ናቸው ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሚያዝያ 5 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ