የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው /11

ወዳጄ ሆይ !

በስሜት ሰውን ተወዳጅተህ አሁን አልቆብህ ከሆነ በጸሎት ፍቅርን ለምን ። በስሜት ማገልገል ጀምረህ አሁን ተባርደህ ከሆነ በጸሎት ኃይልን ጠይቅ ። በስሜት ዘምተህ አሁን ፈርተህ ከሆነ በጸሎት እምነትን ተሞላ ። በስሜት መጽውተህ አሁን ተጸጽተህ ከሆነ በጸሎት ፍቅረ እግዚአብሔርን አስስ ። በስሜት ቆርበህ አሁን ልብህ መንታ ሁኖ ከሆነ በጸሎት ጽናትን ፈልግ ። ላሉብህ ችግሮች ሦስት መልሶች አሉ ። እነርሱም አንደኛ፡- ጸሎት ፣ ሁለተኛ፡- ጸሎት ፣ ሦስተኛ ጸሎት ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

ቤት ስትይዝ ኑሮህ ቀላል እንዲሆንልህ ትጋትንና ሙያን ገንዘብ አድርግ ። ለትንሽ ለትልቁ ባለሙያ መፈለግ ያደክምሃል ። ባለሙያዎች የዕለት ነዋሪዎች ናቸውና ቋሚ ወዳጅነትን ላያከብሩ ይችላሉ ። አንተ ግን ሙያን ተማር ። በወንበር ተቀምጦ ከማዘዝ ወርዶ መሥራት ሰላምና ጤና ይሰጣል ። ውርደት አለመሥራት እንጂ ዝቅ ብሎ መሥራት አይደለም ።

ወዳጄ ሆይ !

ለትውልድ ስለምታስተላልፈው ነገር ተጠንቀቅ ። አንድ ጋኔን ሌላውን ሲያሰለጥን አሥር ጋኔን አድርጎ የማውጣት አቅም አለው ። አንድ ክፉ ነገር ስትዘራም አሥር ክፉ ነገር ይበቅላል ። በዓለም ላይ ክፋትን መዝራት ያንተ ኃላፊነት ሲሆን መሰብሰብ ግን ያንተ ሥልጣን አይደለም ። አንተ ብትጸጸት እንኳ ካንተ የተቀበሉት ያራምዱታል እንጂ አይቆሙም ። መሥራት የምትችልበት ቀን ከሆነ መሥራት የማትችልበት ቀን ይመጣልና ቶሎ ፣ ቶሎ ሥራህን ፈጽም ። መሥራት የማትችልበት ዘመን ከሆነ በጸሎትና በቃለ እግዚአብሔር እየታጠቅህ ንጋትን ጠብቅ ።

ወዳጄ ሆይ !

የቤተሰብ ጸሎት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አትርሳ ። በቤተሰብ ሰዓትም የግል ስልክ መያዝ መራራቅን እንደሚያስከትል እወቅ ። የቤተሰብ ጸሎት ያሰባስባል ። ምግብና ጸሎት በጋራ መደረጉ የቤተሰብ የግዴታ ሕግ ሊሆን ይገባዋል ። ምግብም አብሮ ሲበሉት ያፋቅራል ፣ ጸሎትም ኃይልን ይሰጣል ። አብሮ አለመመገብ የልብ መራራቅን ፣ አብሮ አለመጸለይም መንፈሳዊ ዝለትን ያመጣል ። “መቅሰፍትም ወደ ቤትህ አይገባም” የሚለው ኪዳን ተፈጻሚ የሚሆነው በቤተሰብ ጸሎትም ነው ። መቅሰፍት ሁሉን የሚነካ ችግር ፣ ድንገተኛ የሆነ አዋኪ ነገር ነው ። የቤተሰብ ጸሎት የልጆች አእምሮ እንዲባረክ ፣ በዘመናቸው የጸሎት ሰው እንዲሆኑ ያግዛል ። የቤተሰብ ጸሎት ሰላምን ይሰጣል ፣ ጓዳን ይባርካል ። የቤተሰብ ጸሎት ጣፋጭና አጭር ቢሆን ይመረጣል ።

ወዳጄ ሆይ !

ለጎረቤትህ ትልቅ ዋጋ ስጥ ። “ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት” የተባለውን አትርሳ ። ጎረቤትም በደስታ በኀዘንህ ቀድሞ ይደርስልሃል ። የጎረቤትን ፍቅር ለመጠበቅ ድንበርህን ጠብቀህ መኖር ፣ ወግ ያለው ግንኙነት ብቻ ማድረግ መልካም ነው ። ክፉ ጎረቤትና የጥርስ ሕመም ተመሳሳይ ናቸው ።

ወዳጄ ሆይ !

ከመንፈሳዊ አገልግሎት ከፍ ያለና ደስታ የሚሰጠው ችግረኞችንና ሕመምተኞችን መጎብኘት ነው ። የመጣውን ችግረኛ ከመደገፍ በላይ ወደ ችግረኛው ሂዶ መርዳት ትሩፋት ነው ። ዋጋ መክፈል መሥዋዕትነት ወይም አምልኮ ነው ። ዋጋ ስትከፍል ጸጋ ይበዛልሃል ።

ወዳጄ ሆይ !

እግዚአብሔር ውዳሴን ይወዳል ። ሰው ከሙላቱ ይጎድላልና አመስግነኸው ታፍር ይሆናል ። እግዚአብሔር ግን መሙላት መጕደል የሌለበት ፍጹም ነውና ውዳሴ ጽድቅ ይገባዋል ። ስታመሰግን ነፍስህ እያበራች ትመጣለች ። ደስታህም መፍለቅለቅ ይጀምራል ። ተመስገን በማለት የተዘጋውን በር ማስከፈት ይቻላል ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ