የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው/15

ወዳጄ ሆይ !

መክሊትህን ጥለህ ሌላ መክሊት አትፈልግ ። በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ የምታገኘው በምትመኘው ሳይሆን በተሰጠህ ጸጋ ነው ። ሁሉም መክሊት ያለውና ምንም መክሊት የሌለው ማንም የለም ። መክሊቱን ያወቀና ያላወቀ ብለን ግን ለሁለት መክፈል እንችላለን ። እያስተማረ የሚኖር እየተማረ የሚኖር ነው ። ማስተማር ያድሳል ። አስተማሪ አያረጅም ። አስተማሪ መርሳትን ያሸንፋል ። ራእይ የሰጡህ ሰዎች ቢኖሩ የሰጣቸው እግዚአብሔር ነውና አክብረህ መያዝ ይገባሃል ። ራእይን ካላቀበሉት ተወልዶ ያላደገ ልጅ ነው ። ሊሰጥ ሲችል በድሀ የሚጨክን ፣ ለባለጠጋ የሚቸር አያሌ ሰው አለ ። መልአክን ሸኝተህ መልአክ አትጠብቅ ። የመላእክት ማኅበር አንድ ነውና አታገኘውም ።

ወዳጄ ሆይ !

የልጅነት ምኞትህን ፣ የወጣትነት ድካምህን ፣ የጉብዝና ዋጋህን ፣ የሽምግልና ጌጥህን አትተወው ። የልጅነት ምኞት ፍቅር ፣ የወጣትነት ድካም ራእይ ፣ የጉብዝና ዋጋ መረጋጋት ፣ የሽምግልና ጌጥ ጨዋነት ነው ። በብርታትህ ያላመጣኸውን ድል በቸርነቱ በሚሰጥህ እግዚአብሔር ታመን ። እግዚአብሔር መስጠት እየቻለ የከለከለህ አንተ መቀበል ስለማትችል ሊሆን ይችላል ። በሁሉም ሰው ላይ ሞት እንዳለበት ፣ በሁሉም ሰው ችግር አለበትና “እርሱ ምን አለበት  ታድሎ” እያልህ ሐሰተኛ መጽናናትን አትፈልግ ። አንድነት የምንፈጥረው ሳይሆን የተፈጠርንበት መልክ ነው ። የሰው ዘር ሁሉ ምንጩ አንድ አዳም ነውና ። አንድነት ወደ ጥንተ ተፈጥሮ መመለስ ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

የዓለማውያን ወዳጅነት የኃጢአት አንድነትን ይፈልጋል ። ካልተባበርካቸው ህልውናህ ወቀሳ ይሆንባቸዋልና ሊያጠፉህ ይነሣሉ ። እውነት በዚህ ዓለም ትመሰክርላታለህ ፣ በሚመጣው ዓለም ትመሰክርልሃለች ።

ወዳጄ ሆይ !

ባለ ራእይና መሪ ስትሆን ላንተም መሪ ያስፈልግሃል ። ራእይህን በዓላማ ፣ ዓላማህን በዕቅድ ፣ ዕቅድህን በደንብ ፣ ደንብህን በክትትል ልታስፈጽመው ይገባሃል ። ወዳንተ የሚመጡት ወሬዎችና ማስረጃዎች ከሆኑት ያልሆኑት ይበዛሉና ወርደህ ማየት ይገባሃል ። የሚቀድመውንና የሚከተለውን መለየት የመሪና የባለ ራእይ ከፍታው ነው ። የባለጠጎችን ንብረት መጠበቅ ፣ የድሆችን ሆድ መንከባከብ የመሪ ግዳጁ ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

የግርግርና የሆታ አፍቃሪ ስትሆን ራስህን ደብቀህ የምትኖር ፣ ወደ ውስጥ የምታወራና የምታለቅስ ሰው ትሆናለህ ። በድካም ያመጣኸውን ገንዘብ ያለ ዓላማ አትበትነው ። “ምኞትና ጎፈሬ ዕለቱን አያድጉም” ይባላልና ዛሬ ካልሆነ ብለህ አትዘን ። ከሚታወቁ ሰዎች ጋር ለመታየት አትከጅል ። በድሀ አቅምህ የባለጠጋ መከራ ይወድቅብሃል ። የድሀ ወዳጅ የሆኑ ሰዎች በስቃይ ስፍራ ያሉ ይመስልሃል ። ልባቸው ግን ደስተኛ ነው ። ፖለቲከኞችና እውቅ ተዋንያን ግን የሚብረቀረቁት የውስጣቸውን ስቃይ ለመሸፈን ነው ። የክርስትናው ጥልቅ ትምህርት ለድሀ ትሰጣለህ ሳይሆን ድሆች ይሰጡሃል የሚል ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

ደግፎ የሚያቆምህ እህል ብቻ ሳይሆን ተስፋ ነውና ሁልጊዜ ተስፋ አድርግ ። ተስፋ በእግዚአብሔር ቃልና በፍቅር ልብ ይገኛል ። ማፍቀር ስታቆም ተስፋ ማድረግም ታቆማለህ ። እምነት ከሌለህ እንኳን ሰማይ መግባት ከቤትህ መውጣት አትችልም ። “አምኜ ተጎዳሁ” አትበል ፤ እምነት ባይኖር በዓለም ላይ ሥራ አይጀመርም ነበርና ። ከታማኙ ጋር እግዚአብሔር አለና የተጎዳው ያልታመነው ሰው ነው ። ያለ እምነት ማወቅ ፣ ማፍቀር ፣ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ