የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው/16

ወዳጄ ሆይ !

የስብከት አደባባይ የሆኑት ኢየሩሳሌምና መቅደሱ ሰባኪውን አባረሩ ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የስብከት ዐውዱ ከቤተ መቅደሱ ይልቅ የገሊላ ኮረብታና መስክ ነበረ ። አንተም በመቅደሱ ስፍራ ብታጣ ጌታህ ያስተማረባቸውን ኮረብታዎችና ሣር የለበሱ መስኮች አስብ ። ዝናህ ከፍ ባለ ቍጥር ሞትህ ይፋጠናል ። የሁሉ ዓይን ባየህ መጠን የሁሉ እጅ ድንጋይ ይወረውርብሃል ። የማይመጥንህን የሆሳዕና ምስጋና አሜን ብለህ ከተቀበልህ “ይሰቀል” የሚለውን ድምፅ መሸከም ይከብድሃል ።

ወዳጄ ሆይ !

የሥጋ ፈውስ ለነፍስ ፈውስ ማስረጃ አይደለም ። ዐሥር ለምጻሞች ተፈውሰው ለምስጋና የተመለሰው ያ ልዩ ወገን ፣ አንዱ ሰው ነው ። ውለታን የሚያስብ በነፍሱ የዳነ ነው ። ከውለታ ቢስ ሯጮች ውለታ የሚከብደው ሽባ የዳነ ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

ከታላላቅ መደነቆችና ፈውሶች ቀጥሎ ካልተሰወርህ የመቀበሪያህን ጉድጓድ በገዛ እጅህ እንደ ቆፈርህ እወቅ ። ከስድብ ቀጥሎ ምስጋና ቢመጣ ይሻላል ፤ ከምስጋና ቀጥሎ የሚመጣው ስድብ የማይለመድ ይሆናል ። ቆንጆ ነኝ ብለህ ራስህን ስታሳምን ፣ አውቃለሁ ብለህ በድፍረት ስታወራ ፣ እኔ ነኝ ጀማሪና ፈጻሚው ብለህ ስትኮራ ለጊዜው ሁሉ ይቀበልሃል ። በራስህ ከፍ ብለሃልና ውድቀትህ ትንሣኤ የለውም ። ደፋር ተነሣሒ/ንስሐ ገቢ/ እንጂ ደፋር ደንቆሮ አትሁን ። ጌታ ኢየሱስ ማስተማሪያ ስፍራ አጥቶ ባሕር ላይ በተውሶ ጀልባ ተሳፍሮ አስተማረ ፣ ለማስተማር የሚረገጥ መሬት እስክታጣ ብትገፋም ማስተማርህን ቀጥል ።

ወዳጄ ሆይ !

የሌሎች ሞት ያንተ ሞት ነው ። ጌታ ኢየሱስ ዮሐንስ መጥምቅ ሲገደል ለማዘን ጊዜ ፈለገ ። የዮሐንስ ሞት ቀጥሎ የራሱ ሞት እንደሆነ ያውቃልና ። ሌሎች ሲገፉ ዝም ብለህ አንተ ጋ ሲደርስ ብትጮኽ ፣ ያን ጊዜ ግፍ ሕጋዊ ሁኖ ፣ እንደ ጽድቅ ተቆጥሮ ታገኘዋለህ ። ሞት ሲለመድ ሰርግ ይመስላል ። ጩኸትም መፍትሔ ካላገኘ “እሪ በከንቱ” ተብሎ ስም ይወጣለታል ። የበረሃው ዮሐንስ መጥምቅ ሲሞት በከተማ ያለው ጌታችን አዘነ ፣ የራሱንም ሞት አሰበ ። አንተም ዳሩ ሲነካ መሐሉ ዳር እንደሚሆን እንድታስብ ምሳሌ ትቶልሃል ።

ወዳጄ ሆይ !

ከራስህ ጋ ለመሆን ጊዜ ብታጣ ፣ የኑሮ ጥድፊያው ፋታ ቢነሣህ ፣ የተሳፈርህበት ባቡር ፌርማታ የለሽ ሁኖ ቢበርር አሁንም እግዚአብሔርን አስብ ። ጊዜና ስፍራ ያዘጋጅልሃል ። ስትከተላቸው የሚሸሹህ ፣ ስትሸሻቸው የሚከተሉህ ጥላ መሳይ ወገኖች ቢኖሩ ፣ ለቀልድህ እየሳቁ ፣ ለሐቅህ ጆሮ የለሽ ቢሆኑ ዓለም ማለት እንደዚህ ናት ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ