ወዳጄ ሆይ !
ቃል ከሥጋ ጋር ባይዋሐድ የሰው ልጅ አይድንም ነበር ። ያለ ተዋሕዶ መዳን የለም ። ባልና ሚስት ካልተዋሐዱ ልጆችን ማዳን/ማትረፍ አይችሉም ። መንግሥትና ሕዝብ ካልተዋሐዱ አገርን ማሻገር አይችሉም ። አባቶችና ምእመናን ካልተዋሐዱ እየሰጠመ ያለውን ትውልድ መታደግ አይችሉም ። ሥራና ሠራተኛ ካልተዋሐዱ የአገር ጊዜና ገንዘብ መዳን አይችሉም ። መምህርና ተማሪ ካልተዋሐዱ አእምሮ ከጨለማ ሊወጣ አይችልም ። ያለ ተዋሕዶ መዳን የለም ። ተዋሕዶ ተቃርኖ ነው ። ሁለት ተቃራኒ ነገሮች በስምምነት የሚኖሩበት ፣ አንዱ አንዱን ሳያጠፋው አንድ አካል የሚሆኑበት ነው ። ባልና ሚስት ፣ ሕዝብና መንግሥት ያለ መጠፋፋት ሲዋሐዱ ተዋሕዶው የሠመረ ይሆናል ። ቃል የሥጋን ሞት ገንዘቡ አደረገ ፣ መንግሥትም የሕዝብን ሞት ገንዘቡ ሲያደርግ ፣ ባልም የሚስቱን ጉዳት የራሱ እንደሆነ ሲሰማው ያን ጊዜ ተዋሕዶ አለና መዳን ይሆናል ። ሥጋም የቃልን ርስት ወርሷልና አምላክ ሁኗል ። በተዋሕዶም ከፍ ያለው ዝቅ ያለውን ይስበዋል ። የተጎዳውን አዳኝ ያደርገዋል ። ተዋሕዶ ሞትና ክብርን የጋራው ያደርጋል ። ያን ጊዜ ሁለት አካል አንድ አካል ፣ ሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሲሆን በተዋሕዶ ይከብራል ። ተዋሕዶ ክብር ነውና ባዕድ የሚያከብረን ስንዘፍን ሳይሆን ስንዋሐድ ነው ።
ወዳጄ ሆይ !
የቃና ዘገሊላ ሰርገኛ ሥጋን ለብቻ አልጋበዘም ፣ ተአምር አድራጊውን ቃል ተጥሎ አልጠራም ። በተዋሕዶ ቃልና ሥጋ የተዋሐዱትን አንዱን ክርስቶስ ጠራ ። መለኮት በሥጋው በላ ጠጣ ፣ ሥጋም በመለኮት ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ለወጠ ። የሰው ልጅም አንድ ነውና ወደ ግብዣህ ባለጠጋንም ድሀንም እኩል ልትጠራ ይገባሃል ። ማድጋውን የሚሸከምልህ አንዱ ፣ ውኃውን ወይን ጠጅ የሚያደርግልህ ሌላው ነው ። ሁለቱም ግን አንድ ሰው ናቸው ። ከወራጁ ከቀዳህ አቤልና ቃየን ናቸው ። ከምንጩ ከቀዳህ አንድ አዳም ነው ። የሮጠልህንም ፣ የቸረህንም ሁለቱንም እኩል አመስግን ። ጉልበት በገንዘብ አይመነዘርምና የድሀ ልፋት ይረሳል ። ገንዘብ እጅ እግር የለውምና እጅ እግር የሆኑ ድሆችንም ማመስገን አትርሳ ። ከሁሉ በላይ ሰው እኩል ነውና አንድ የሆነውን አካል ወደ መለየት አትግባ ። ባሕርይውም አንድ ነውና የራስህን ጠባይ እንደምትረዳው የወንድምህንም ጠባይ ተረዳ ። አካልን ጋብዘህ ባሕርይን ማስቀረት አይቻልምና ሰውን ከነ ባሕርዩ ተቀበለው ።
ወዳጄ ሆይ !
አባቶች፡- አብና መንፈስ ቅዱስን በልደት አላሳተፍንምና በሞትም አናሳትፋቸውም ይላሉ ። የወልድ የአካሉ ግብር መወለድ ነው ። ስለዚህ ለመወለድ ወደ ዓለም መጣ ። የሥጋን ልደት ገንዘቡ ካደረገ ሞትንም ገንዘቡ ማድረግ አለበት ። አብና መንፈስ ቅዱስ ግን በወልድ ሞት አዳኝ ይባላሉ ። ማዳን የሥላሴ አንዲት ገንዘብ ናትና ። እንዲሁም ከሰማይ እስከ መውረድ ዝቅ ቢሉ ፣ ለመሞትም መስቀል ቢሸከሙ የአካል ግብራቸው ፣ ሰው የመሆን ግዳጃቸው ነውና የአገር መሪዎች ፣ የሕዝብ አስተማሪ አዋቂዎች በደስታ ሊቀበሉት ይገባል ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ማደግም ፣ ታላቅ መባልም የሕዝብ መሆኑን ማመን አለባቸው ። አዋቂዎችና መሪዎች የሚያደርጉትን ሁሉ እንደ ውለታ መቍጠር የለባቸውም ። በምሥጢረ ተዋሕዶ ማዳን የቃል ብቻ ፣ መሞት የሥጋ ብቻ አይባልምና ለአንድ አገር በአንድ አካል የተሠራውን እገሌ ጎሣ ሠራው እገሌ ሊሉ አያስፈልጋቸውም ። የታላቅነት ምስጋና አንዲት ናት ። በዘር በቋንቋ አትከፈልም ።