የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው/19

ወዳጄ ሆይ !

ለነፍስ መታደስን የሚያመጣ መልካም ወሬ ፣ ጥሩ መዓዛ ፣ የወዳጅ ፊት ፣ ተፈጥሮን ማድነቅ ፣ ከሁሉ በላይ ስብሐተ እግዚአብሔርን /የእግዚአብሔርን ምስጋና ማድረስ ነው ። ከፊት እየመራ ከኋላ የሚያስከትልህ ፣ በበትር ሳይሆን በድምፁ ጣዕም የሚጠራህ እውነተኛ የበጎች እረኛ ክርስቶስ ነው ። ጌታችን ክርስቶስ ላልበደለ ሰው የሚሰጠውን ጸጋ ፣ ለተጸጸቱ ሰዎችም ይሰጣልና በፊቱ መዋረድን አትፍራ ።

ወዳጄ ሆይ !

እግዚአብሔር የጸጋው መንገድ ፣ የሥራው መሣሪያ እንዲያደርግህ ፣ በእግርህ እንዲደርስብህ ፣ በእጅህ ጦም አዳሪን እንዲያጠግብ ፣ አካልህን ግዛቱ አድርጎ እንዲነግሥብህ በብርቱ ለምን ። እግዚአብሔር ካልገዛህ የማይገዛህ መጥፎ ነገር የለምና ። የሻከሩ ልቦችህ እስኪለሰልሱ ከበደሉህ ሰዎችና ከተጎዳህበት ስፍራ ራቅ ። በጊዜ ውስጥ የማይፈወስ ቍስል የለም ። አንተ የረሳኸውን ጉዳት እንዳያስታውሱ ፣ የረጋውን መንፈስህን እንዳያናውጡ ፣ ያሳነስከውን ጉዳይ ከፍ አድርገው እንዳያቆስሉህ ነገር ከማይቋጩ ሰዎች ጋር አትነጋገር ።

ወዳጄ ሆይ !

የመገዛት መንፈስ ይኑርህ ። ሳጥናኤልን ሰይጣን ያደረገው አለመገዛት ፣ መልአክን መልአክ ያደረገው መገዛት ነው ። መልአክ ሁኖ መፈጠር ሰይጣን ላለ መሆን ዋስትና አይደለም ። በእግዚአብሔር ሰው ሁነህ ተፈጥረሃል ፣ ሰው ሁኖ መኖር ግን ያንተ ምርጫ ነው ። ለወላጆችህ በጉልበትህ ፣ ለአስተማሪዎችህ በእውቀትህ ፣ ለአገልጋዮች በመንፈሳዊነት አገልግል ። በሥጋ የወለዱህን ወላጆች ፣ በትምህርት የወለዱህን አስተማሪዎች ፣ በመንፈስ የወለዱህን አገልጋዮች አትናቅ ። ወላጆችህ ወላጆች የሆኑት በጸጋ እንጂ በብቃት አይደለም ። ሥልጣንን የናቁ ዳታንና አቤሮን መሬት ተከፍታ በቁማቸው መቃብር ወርደዋል ። ሥልጣንን በመናቅ እግዚአብሔር ያድነኛል ብለህ አታስብ ።

ወዳጄ ሆይ !

ሺህ ዛፎች ሲያድጉ ድምፅ አይሰማም ። አንድ ዛፍ ሲወድቅ ግን ድምፁ ይሰማል ። የሰዎችን ዕድገታቸውን አድንቅ ፣ በውድቀታቸው አትደነቅ ። የግል ሕይወታቸውን ለራሳቸው ተውላቸው እንጂ አጽዳቂና ኰናኝ አትሁን ።

ወዳጄ ሆይ !

እንክርዳድን ከስንዴ ለመለየት ማየት ያስፈልግሃል ። መንፈሳዊ ብርሃንህ ጨልሞ የሌሎችን ስህተት አትንቀስ ። እንክርዳድን ከስንዴ የምትለየው ለስንዴው ብለህ ሳይሆን ለራስህ ብለህ ነው ። ሰዎችም ክፉ ግብራቸውን እንዲተዉ ስትጥር ለራስህ ብለህ መሆኑን አትዘንጋ ። ክርስቶስን በግብር እንጂ በእግር ብቻ አትከተል ። ፍቅርህና አክብሮትህ ደረጃ እንዳያወጣ የቤተ ክርስቲያን መሪ ስትሆን እነማን ምን እንደ ሰጡ አለማወቅህ መልካም ነው ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ