የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው/21

ወዳጄ ሆይ !

በሥጋና በነፍስ ትከስራለህና ለእግዚአብሔር ብለህ የሰጠኸውን አትቆጭበት ። ሰዎች ስላንተ የሚሉትን ሳይሆን እግዚአብሔር ስላንተ የሚለውን አድምጥ ። በጸጋ ያገኘኸውን በገንዘብና በውዳሴ ከንቱ አትሽጠው ። እግዚአብሔር በበላይህ የሾመውን አክብረው ። ቃል የእግዚአብሔር ወልድ የከዊን ስሙ ነውና ቃል የገባኸውን ጠብቅ ። ያስፈልገኛል ከምትለው ያስፈልግሃል ተብሎ የተሰጠህ በቂ ነው ። “በዚህ ዘመን ለምን ተፈጠርሁ” አትበል ፤ ዘመንና ስፍራን የመረጠልህ የማይሳሳተው እግዚአብሔር ነው ። ራስህን እንጂ ሰዎችን አትውቀስ ። አንተ በከፈትከው ደጃፍህ ባለጌ “ለምን ገባ?” ብለህ አትበሳጭ ።

ወዳጄ ሆይ !

አንደኛ የመሆን ፍላጎትህ ባካና ፣ ብቸኛ የመሆን ፍላጎትህ ራስህን እንደ ጣኦት እንድታይ ያደርግሃል ። የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጥ ፣ አሥራት በኵራትህን ሳትሰጥ ደስታና በረከት አጣሁ ብለህ አትዘን ። ግብር የማይከፍል አገሩንና መንግሥቱን እንደ ካደ ይቆጠራል ። አሥራት በኵራት የማያወጣም የእግዚአብሔርን አምላክነት ፣ የመንግሥቱን ዘላለማዊነት የካደ ነው ። አሥራት በኵራት ዘር ነው ። ገብሬ ለዘር ሳያስቀምጥ ሁሉንም ከበላ በቀጣይ ዓመት ረሀብተኛ ነው ። አሥራት በኵራት የማያወጣም ወደ ደረቅ ምድር እየተጓዘ ነው ። አንተ መሆን የምትፈልገው ፣ ሰዎች እንዲሆኑ የምትከጅለው ገና ያልተጨበጠ ጉም ነው ። እግዚአብሔር ግን አምላክ የሆነ ፣ ሳይጨምር ሳይቀንስ የሚኖር ነውና ማረፍ በእርሱ ብቻ ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

“ሰውን ማመኔ ጎዳኝ” አትበል ። አንተ ከእግዚአብሔር ጋር ስትቀር ፣ ከዳተኞች ግን ከክዳታቸው ጋር ሂደዋል ። እግዚአብሔርን ልታከብርበት የተቀበልከውን ሀብት ለአጫዋች ለዘዋሪ አትጨርስ ፣ እርሱን ልታመልክበት የሰጠህን ጤናህን በዝሙት አታርክስ ። ገንዘብና ጤና ሳሉ የሚባክኑ አይመስሉም ፣ ከሄዱ በኋላ ግን መመለሻቸው ጠባብ ነው ። በዕድሜ ፣ በእውቀት ፣ በማመን የቀደሙህን አክብር ። አንተ ሳትወለድ በፊት ማንበብ የጀመሩትን አርማለሁ አትበል ።

ወዳጄ ሆይ !

የራበውን ወገን ስታይ፡- “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ” ተብሏል እያልህ ያለ ቦታው አትጥቀስ ። የወደቀ ሰው ስታይ፡- “ከእኛ ዘንድ ወጡ ፣ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም” እያልህ ጭካኔህን ባለ ጥቅስ አታድርገው ። ማዘን ካልቻልህ የሚያዝኑትን ጨካኝ ለማድረግ አትትጋ ። መልካም መናገር ቢያቅትህ ዝም ማለት አያቅትህ ። ቤት በቀላል ፣ አገር በዋዛ የቆመ አይምሰልህ ። ወይ የቤት መሪ ፣ ወይ የአገር መሪ መሆንህ አይቀርምና የነገ መድረሻህ ላይ አትፍረድ ። አንድ ቀን ይህን አደርጋለሁ እያልህ ያልተቆረጠ ቀን አትጥራ ። አንድ ቀን እስከ ዕለተ ምጽአት የሚያገለግል ቃል ነውና በቁርጥ አሳብ ሥራህን ፈጽም ። የሕሊና ፣ የታሪክ ፣ የሕግ ግዳጅ ነውና ግፍን አውግዝ ።

ወዳጄ ሆይ !

በደረሰብህ ክፉ ነገር የምትወደው ወዳጅህ እንዳለበት ባወቅህ ጊዜ ከኀዘን ይልቅ ጥንቃቄን ገንዘብ አድርግ ። ሰውን እቆጣጠራለሁ ብለህ ስትነሣ ፣ ነፋስን እይዛለሁ ብለህ መነሣትህ ነውና ዕድሜህ ታባክናለህ ። ከማሰማራትህ በፊት መስኩን ፣ ከመጀመርህ በፊት ግቡን ፣ ከመዝለልህ በፊት ማረፊያውን ተመልከት ። የሰው ክብር ያለው የሚቀድመውንና የሚከተለውን ሲያውቅ ነው ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ