የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው/22

ወዳጄ ሆይ !

ሳይማሩ ያስተማሩህ ወላጆችህ ፣ ተምረህ ማስተማር ያቃተህን ሲወቅሱህ ይኖራሉ ። ሰው በተለያየ መንገድ ይማራል ። ከመጻሕፍት ፣ ከመምህራን ፣ ከተፈጥሮ ፣ ከሕይወት ትግል ትምህርት ይቀስማል ። በጠባብ ክፍል ተምረህ እንደሆነ ፣ በሰፊው ተፈጥሮ የተማሩትን አትናቅ ። በመምህር ተምረህ እንደሆነ ፣ በሕይወት የተማሩትንም አክብር ። በሁሉም የሚያስተምር እግዚአብሔር ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

ስጦታ የልብ መልእክተኛ ነውና ለምትወደው ሰው የምትወደውን ስጦታ ስጠው ። ከአቅምህ በላይ ስትሰጥ ፍቅርን መግዛትህ ነው ። የሚወደው ምንድነው ? ከማለትም የምትወደውን መስጠት ደስታ አለው ።

ወዳጄ ሆይ !

ሥርዓት ተፈጥሮ በጸጥታ የሚጓዝበት ፣ አገር በታሪክ ፣ ቤተ ክርስቲያን በውበት ፣ ቤተሰብ በክብር ፣ ግለሰብ በአርአያነት የሚቆሙበት መንፈሳዊ መልክ ነው ። ሥርዓት የበላይና የበታች የሚግባቡበት ቋንቋ ነው ። ቤተ ክርስቲያን ሺህ ዘመናትን ተሻግራ ዛሬ ላይ ያለችው በሥርዓትም ነው ። የተከበረና ዕድሜ ያለው ቤተሰብም ምሥጢሩ ሥርዓት መኖሩ ነው ። ተወዳጅ ሰብእና አለው የምንለው ሰው ሥርዓት ስላለው ነው ። ስለዚህ ሥርዓትን ውደደው ።

ወዳጄ ሆይ !

ልማዶች ክፉና ደግ ተብለው ለሁለት ይከፈላሉ ። ክፉ ልማዶች ረጅም ዘመን ስላስቆጠሩ ደግ አይባሉም ። የዘመናት ርዝማኔ ደግ ቢያደርግ ሰይጣንና ሥራው ደግ ይሆኑ ነበር ። ክፉ ልማዶችን ስትነቅል ደጉንም አብረህ እንዳትነቅል ተጠንቀቅ ። በጎ ልማዶች አንድ ሕዝብ በአንድ ስፍራ ላይ ብዙ ዘመናት ሳይናወጥ ለመኖሩ ምልክት ናቸው ። መልካም ልማዶችን አውርሳቸው እንጂ በግድ ሰው ላይ እጭናለሁ በማለት ከሰው ነጻ ፈቃድ ጋር አትጋጭ ። ኃያላን ነገሥታት የወደቁት የሰውን ነጻ ፈቃድ እንገዛለን ሲሉ ነው ። ደግ ልማድና ሃይማኖት ተቀባይነት የሚያገኙት በአብዮት ሳይሆን በትምህርት ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

የቡድንተኝነት ስሜት ከእውነት ይልቅ ለአጀቡ ያደላልና ቡድንተኛ አትሁን ። ቡድንተኝነት የሚደሰተው በራሱ ማደግ ሳይሆን በሌላው መውደቅ ነው ። ቡድንተኝነት ያስተሳስራል ፣ ይህ ቋጠሮ የሚቆየው ግን የሚጠሉት እስኪወድቁ ድረስ ብቻ ነው ። የአድማ ፍቅር የሚያድሙበት እስካለ የሚቆይ ነው ። ቡድንተኝነት ለቡድን ጠብ እንጂ ለኅብረት ተግባር አይሆንም ። ሰዋዊ ጠባይን በአራዊታዊ የሚለውጥ ነውና ቡድንተኝነትን እራቀው ። ስትወለድ ሰው ነበርህ ፣ ስትሞትም ሰው ሁን ፤ ሕፃን ተወለደ ተብሎ የጀመርከውን ሕይወት እገሌ ጎሣ ሞተ ተብሎ እንዲፈጸም አትፍቀድ ።

ወዳጄ ሆይ !

እግዚአብሔር በአምልኮቱ ቀናተኛ ነውና በትዳር ጓደኛ ፣ በልጅ ፣ በወዳጅ ፣ በንጉሥ አትታመን ። አምልኮት እገሌ ባይኖር ምን እሆናለሁ ? ማለት ነው ። እግዚአብሔርን እንደሌለ ቆጥረህ ፊት በሥጋት ፣ እገሌ ያልከው ሲሞት በኀዘን ብዛት መጎዳት እርሱ ጣኦት ማምለክ ነው ። ሰው ከፍቅር ውጭ አምልኮትን መሸከም አይችልም ። ሙያዬ ፣ ጉልበቴ እስካለ ብለህም በራስህ አትመካ ። የእግዚአብሔር ቍጣ በምታመልከው ነገር ላይ ጸንቶ ይኖራል ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ