የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው/23

ወዳጄ ሆይ !

የዳነች ነፍስ የቆሰለች ሥጋን ማበርታት ትችላለች ፤ የተፈወሰች ሥጋ ግን የቆሰለች ነፍስን ማሳረፍ አትችልምና ለነፍስህ መዳን ቅድሚያ ስጥ ። በምድር ጌታ ፣ በሰማይ ከርታታ ከመሆን ፤ በምድር ከርታታ ፣ በሰማይ ጌታ መሆን ይሻላል ። የከተሞች ውበት የሰው እጅ ሥራ ፣ የገጠሮች ውበት የእግዚአብሔር ሥራ ነው ። የእግዚአብሔርን ሥራ ለማየት ወጣ ባልህ ቍጥር ዓይኖችህ ከአድማስ አድማስ ለማየት ነጻነትን ያገኛሉ ። ያልተበረዘ ማንነትና ሰይጣናዊ ብልጠት የሌላቸውን ሰዎች ታገኛለህና ከከተማ ወጣ ያሉትን ገጠራማ መንደሮች አዘውትርባቸው ።

ወዳጄ ሆይ !

ትልልቅ ዛፎች የጀመሩት ከችግኝ ነውና ትንሽነትህ ትልቅነትህን አልደርስበትም ብሎ አይስጋ ። በትዕግሥትና በጊዜ ውስጥ የማይደረስበት ነገር የለም ። የእውነትን አርማ በማንሣት ግፈኞችን ማስቆም ፣ የድሆች አፍቃሪ በመሆንም የነፍስ ነጻነትን ተለማመድ ። ከዚህ አገር እዚያ አገር ፣ ከምዕራብም ምሥራቅ ይሻል በማለት አትዋትት ። ከሁሉ የሚሻለው ሕይወትን ከነሙሉ ትርጕሟ መቀበል ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

ስብሰባ በተጠራህ ጊዜ የምትናገረውን በጽሑፍና በቁጠባ ተናገር ። የአዳራሽ ግለት ሽቅብ እንድትናገር ያደርግሃልና ተጠንቀቅ ። ያጨበጨበልህ ወደ ቤቱ ሲገባ አንተ ወደ ግዞት ትሄዳለህ ። ራሱን ለማውጣት ጥረት የማያደርግን ማኅበረሰብ የትኛውም ድጋፍ አያነሣውም ። ሰው እንደ አገር ፣ አገርም እንደ ሰው ነውና አገር ራሷን የማጥፋት ወንጀል ትሠራለች ። የአገር ራስን ማጥፋትም የገዥዎች ግፍ ፣ የሕዝቦች ተለያይተው መቆም ነው ። አንድ ካልሆንን እንኳን እንደ መላእክት እንደ አጋንንትም መቆም አንችልም ። የሰይጣን መንግሥት አይለያይም ፣ ሰይጣን ሰዎችን ያለያያል እንጂ እርሱ አይለያይም ። አንድነት ከሌለ ከፍታ የለም ።

ወዳጄ ሆይ !

የፍላጎትህ ጊዜው ሲደርስ ልብህ መጋል ፣ መንፈስህ መደሰት ይጀምራል ። እግዚአብሔር ሲያንኳኳ የእግሩ ኮቴ ያለህበትን አካባቢ ይለውጠዋል ። ከመጠን በላይ የሆኑ ስጋቶች ጥንቃቄን ወደ ፍርሃት ፣ እምነትን ወደ ቅዠት ይለውጡታል ። በዓለም ላይ ሁለት ነገር እንጂ ሦስተኛ የለምና አትጨነቅ ። ቢሆን ይሆናል ፣ ባይሆን ይቀራል ። ስለሚድኑ በሽተኞች ዕለታዊ ምስጋና ፣ ስለ ታመሙትም ዕለታዊ ጸሎት አድርስ ። ተቆልፎባቸው ያሉትን የግፍ ሰለባዎች ለመታደግ በእግዚአብሔር ኃይል ተነሣ ።

ወዳጄ ሆይ !

ግልጥ ያሉ ንግግሮች ግንኙነትን ቀላል ያደርጋሉና ቃላትህን በጣም አታጥብቅ ። ብዙ ዘመን የለመንህበት ጉዳይ ሲፈጸም ፣ የረዳህን እግዚአብሔር ፣ ያገዙህን ወዳጆች ለማመስገን ጊዜና ልቡና ካጣህ ውለታ ቢስ ነህ ። የተዛባ አመለካከትህን ካላጠራህ እንደ መርዝ እየበከለህ ፣ እንደ እርሾ እያቦካህ ይመጣል ። ዕይታህንም ሸውራራ ያደርገዋል ። ከተማው መንደሩ በኪነ ሕንፃ ሲዋብ ፣ ነዋሪው ግን በሥነ ምግባር ሊያምር ይገባዋል ። የተዋቡ ከተሞች የተዋቡ ሰዎችን ይጣራሉ ።

ወዳጄ ሆይ !

መንፈሳዊ ውድቀት የሚባለው በክርስቲያን ሰንበት ምእመናን ለአምልኮተ እግዚአብሔር እየተፋጠኑ አንተ እቤትህ ስትገላበጥ መዋል ነው ። ቀኑን ሲሰጥህ ላልሳሳው እግዚአብሔር ፣ ምስጋና ለመስጠት አትስነፍ ። በዚህ ዓለም ላይ የማይቀርባቸው ቀጠሮዎች አሉ ። የአምልኮ ፣ የወዳጅ ፣ የሐኪም ፣ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ሲሆን ጎበዝ በጉልበቱ ፣ ሯጭ በፍጥነቱ የማይሸሸው ቀጠሮ ዕለተ ሞት ነው ። ሁለት ሺህ ዓመት እየተጠበቀ ያለ ትልቅ ቀጠሮ አለ ። የተቀጠረው መላው የሰው ልጅ ፣ የቀጠረውም ጌታ ክርስቶስ ነው ። ያ ቀጠሮም ዕለተ ምጽአት ነው ። ጌታ ሊመጣ ቀርቧልና ዓለም እየሸሸች ነው ። ለዚያ ቀን በእምነትና በፍቅር ተዘጋጅ ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ